ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ሆነው፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ሆነው፣  

የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሄደ።

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡዳቢ ከተማ ሰኞ ነሐሴ 20/2011 ዓ. ም. የቋቋመው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተግባራዊነት የሚከታተል ኮሚቴ ትናንት ጳጉሜ 6/2011 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተው የመጀመሪያ ስብሰባ ማካሄዱን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። የኮሚቴው አባላት እንደ ጎርጎሮሳዊው መስከረም 11/2001 ዓ. ም. በሰሜን አሜሪካ፣ ኒዮርክ ከተማ በአሸባሪዎች በተሰነዘረው ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡትጥን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ከጥር 26/28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ፣ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በተሰበሰቡበት ወቅት “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል ሰነድ ማርቀቃቸው የሚታወስ ነው። በሐይማኖት መሪዎች የተረቀቀውን እና ታሪካዊ ነው የተባለው ሰነድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት አል ጣይብ ፈርመው ማጽደቃቸው ይታውሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ጳጉሜ 6 ቀን፣ በጎርጎሮርሳዊው መስከረም 11/2019 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የመጀመሪያ ስባሰባውን ያካሄደው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቋቋመበት ቀዳሚ ዓላማ በዓለም ሰላም እንዲሰፍን፣ የዓለም ሕዝቦችም ተዋደው እና ተፋቅረው በሰላም እንዲኖሩ የሚያግዙ የሰነዱን ሃሳቦች ተግባራዊነት ለመከታተል መሆኑ ታውቋል። የመሰብሰቢያ ቀናቸው በጎርጎሮሳዊው መስከረም 11 እንዲሆን የመረጡበት ምክንያት አሸባሪዎች ሞትን እና ውድመትን በዘሩበት ምትክ ሕይወትን እና ወንድማማችነትን ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት ለመግለጽ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሚቴው አባላት፣

“የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተፈጻሚነት የሚከታተሉ የኮሚቴ አባላት፣ ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ላዚ ጋይድ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ የግል ጸሐፊ፣ ፕሮፌሰር መሐመድ ሁሴን አብደል አዚዝ ሐሰን፣ በግብጽ የአል አዛር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣ መሐመድ መሐሙድ አብደል ሳላም የታላቁ መስጊድ ኢማም የአል ጣይብ የሕግ አማካሪ፣ መሐመድ ካሊፋ አል ሙባረክ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአቡ ዳቢ የባህል መምሪያ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ክቡር ያስር ሰኢድ ኣብዱላ ሃረብ አልሙሃይሪ ደራሲ እና ጋዜጠኛ፣ ዶክተር ሱልጣን ፋይሳል አል ካሊፋ አል ረማይቲ የሙስሊም አባቶች ጉባኤ ጠቅላይ ዋና ጸሐፊ መሆናቸው ታውቋል።

የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር እና ስጦታ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮሚቴ አባላትን፣ ሥራ አስኪያጆችን እና የሥራ ኃላፊዎችን ባገኟቸው ወቅት በቫቲካን ሐዋርያዊ ቤተ መጻሕፍት የተዘጋጀውን “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ጥራዝ በስጦታ መልክ አቅርበውላቸዋል። ቀጥለውም የኮሚቴው አባላትን በሙሉ አመስግነው፣ የወንድማማችነት ሕይወት ገንቢዎች በማለት የማበረታቻ ንግግራቸውን አቅርበው የኮሚቴ አባላቱ የሰላም እና የአንድነት ጎዳና በተጀመረበት በአዲስ ምዕራፍ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ የሰላም እጆችን በመዘርጋት ብቻ ሳይሆን የፍቅር ልባቸውን የከፈቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተሰጡ ሹመቶች፣

የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተፈጻሚነት የሚከታተሉ ኮሚቴ አባላት፣ ከቅድስት መንበር ተወካይ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ኤጅጋር ፔኛ ፓራ ጋር ከተገናኙ በኋላ በቅድስት ማርታ የመሰብሰቢያ አዳርሽ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶን ፕሬዚደንት፣ የታላቁ መስጊድ ኢማም የአል ጣይብ የሕግ አማካሪ የሆኑትን መሐመድ መሐሙድ አብደል ሳላምን ዋና ጸሐፊ አድርጎ የመረጣቸው ሲሆን፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ላዚ ጋይድ፣ ደራሲ እና ጋዜጠኛ፣ ክቡር ያስር ሰኢድ ኣብዱላ ሃረብ አልሙሃይሪን፣ የሙስሊም አባቶች ጉባኤ ጠቅላይ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ዶክተር ሱልጣን ፋይሳል አል ካሊፋ አልረማይቲን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አድርጎ መምረጣቸው ታውቋል። ኮሚቴው ለመልካም አቀባበላቸው እና የማበረታቻ ንግግራቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አመስግነው፣ በተጨማሪም በግብጽ የአል አዛር ታላቁ ኢማም የሆኑትን አል ጣይብን እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአቡ ዳቢ ልዑል፣ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያንን ለማበረታቻ መልእክታቸው እና ለኮሚቴው ለሰጡት ድጋፍ አመስግኗቸዋል።

የመጀመሪያ እርምጃ፣

የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተፈጻሚነት የሚከታተሉ ኮሚቴ አባላት በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር የሚገለጡ እርምጃዎችን የዘረዘረ ሲሁን ከእነዚህም መካከል ከጥር 25 ወይም 27 አንዱን ዓለም አቀፍ “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ቀን ሆኖ እንዲያጸድቀው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሃሳብ የሚያቀርብ መሆኑን አስታውቋል።

በተጨማሪም የአንዳንድ የሌሎች ሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ ለማድረግ የቀረበውን ውሳኔ ማጽደቃቸው ታውቋል። ቀጣዩ የስባሰባ ቀን ዓርብ መስከረም 9/2012 ዓ. ም. እና ቦታውም በኒውዮርክ ከተማ እንዲሆን መወሰናቸው ታውቋል። ትናንት ጳጉሜ 6/2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ያካሄዱት የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በግል ባቀረቡት ጸሎታቸው፣ በኒውዮርክ ከተማ እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር መስከረም 11/2001 ዓ. ም. በአሸባሪዎች በተሰነዘረው ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡትጥን አስታውሰዋል።         

                   

12 September 2019, 16:27