ፈልግ

ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የተደረመሰው የጄኖቫው ሞራንዲ ድልድይ፣ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የተደረመሰው የጄኖቫው ሞራንዲ ድልድይ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ የጀኖቫ ከተማ ነዋሪዎችን በመልዕክታቸው አጽናንተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ኢጣሊያ፣ ለጄኖቫ ከተማ ነዋሪዎች መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፣ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በተከሰተው የድልድይ መደርመስ አደጋ የሞቱትን 43 ሰዎችን በማስታወስ መሆኑን፣ የቫቲካን ዜና ዘጋቢ አሜደዎ ሎሞናኮ የላከልን ዜና አመልክቷል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት ይፋ የተደረገው በከተማው በሚታተም “ሰኮሎ ዲቻኖቨ” ወይም 19ኛው ክፍለ ዘመን በመባል በሚታወቅ ጋዜጣ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለጄኖቫ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ከባድ ሐዘንን ጥሎ ያለፈው የድልድይ መደርመስ አደጋ፣ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች ቤተሰቦች እና በአደጋው ምክንያት መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ ለተገደዱት በሙሉ አስደንጋጭ ክስተት እንደነበር ቅዱስነታቸው በከተማው ጋዜጣ ላይ በታተመው መልዕክታቸው አስታውሰዋ። የአደጋውን አሳዛኝነት ከልብ በመገንዘብ፣ ለአደጋው ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው፣ በአደጋው ለቆሰሉት እና ለተፈናቀሉት እንዲሁም ለመላው የጀኖቫ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ጸሎታቸውን ያቀረቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ከሁሉም በላይ መጸለይ ያስፈልጋል፣

ይህን የመሰለ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በቃላት መግለጽ የማይቻል መሆኑን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከአደጋው በኋላ ከማልቀስ፣ ከማዘን እና የእጆቻችንን ሥራ ዋጋ ቢስነት ከመመልከት ባሻገር ሌላ ምንም ማለት አንችልም ብለው፣ ከሁሉም በላይ ማድረግ የምንችለው ጸሎት ማቅረብ ብቻ ነው ብለዋል።

ማስታወስ ያስፈልጋል፣

ጄኖቫን ባስታወሱት ቁጥር ሁሉ የከተማውንም ወደብ እንደሚያስታውሱት የተናገሩት ቅዱስነታቸው ወላጅ አባታቸው የወጡበት ከዚሁ ከተማ መሆኑን አስታውሰው፣ ነዋሪው ሕዝብ በተከሰተው አደጋ ምክንያት የከተማቸውን ስም የሚያስጠሩ በርካታ ታሪኮች መዘንጋት እንደሌለበት በመልዕክታቸው አሳስበዋል።

እግዚአብሔር አይጥለንም፣

ብዙ ስቃይን በመቀበል የሞተውን ኢየሱስ ክርስቶስን መዘንጋት የለብንም ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እርሱ ለስደት እና ለውርደት ተዳርጓል፣  ክፉኛ በመደብደብ፣ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደል ተደርጓል ብለዋል። ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር መልስ አለው ያሉት ቅዱስነታቸው በሐዘናችን ጊዜ መጽናኛችን፣ በችግራችን ጊዜ የቅርብ አለኝታችን፣ ይህን የሚገልጽልን በቃላት ሳይሆን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ እኛ በመላክ በመሆኑ ጥያቄዎቻችንን እና ሐዘናችንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ማቅረብ ይኖርብናል ብለዋል። እኛ ደካሞች እና ሐጢአተኞች ሆነን ብንገኝም፣ ከአባቱ ዘንድ ምህረትን ለማስገኘት ሲል ተሰቅሎ የሞተልን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞትም ተነስቶ በመካከላችን ይገኛል፣ የዘወትር ደጋፊያችን መንፈስ ቅዱስም ከእኛ ጋር አለ ብለው፣ ፈጽሞ ሳታቋርጥ በመጎናጸፊያዋ የምታቅፈን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታችን በሰማያት አለችልን ብለዋል።

ተስፋን መቁረጥ አይገባም፣

በሰሜን ኢጣልያ፣ የጄኖቫ ከተማ ክርስቲያን ምዕመናንን በመልዕክታቸው ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሐዘናቸውን እና ችግሮቻቸውን የምትጋራ ቤተክርስቲያን እንዳለቻቸው አስረድተው፣ ድክመቶቻችንን እና ሰብዓዊ ማንነታችንን እያወቅን በመጣን ቁጥር፣ ማሕበራዊ አንድነታችንን እና ቤተሰባዊነታችንን መረዳት እንችላለን ብለው “ምንም እንኳን ከባድ ሐዘን እና መከራ ቢደርስባችሁም ተስፋን መቁረጥ የለባችሁም” ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 August 2019, 16:59