ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በ1959 ዓ. ም. በቅ. ጴጥሮስ አደባባይ የብርሃነ ትንሳኤን መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ወቅት፣  ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በ1959 ዓ. ም. በቅ. ጴጥሮስ አደባባይ የብርሃነ ትንሳኤን መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ወቅት፣  

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ጳውሎስ 6ኛ፣ እውነተኛ ክርስቲያን፣ ገር እና ለውጥ ፈላጊ የነበሩ መሆናቸው ተገለጸ።

የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ፣ ኦዜርቫቶረ ሮማኖ ዳይሬክተር አቶ ሞንዳ በጋዜጣው ርዕሠ አንቀጽ እንደገለጹት፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ውስጥ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎች የለውጥ አራማጅ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቀድሞ ስማቸው ጆቫኒ ባቲስታ ሞንቲኒ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ስማቸው ጳውሎስ 6ኛ ተብለው የተጠሩ፣ የዛሬ 41 ዓመት፣ ማለትም በሐምሌ 30/1970 ዓ. ም. ያረፉ መሆናቸው ይታወሳል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነታቸው ዘመን በሆነው በሃያኛው ክፍለ ዘመን፣ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ግንዛቤ በውስጥም ሆነ በውጭ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ፣ በተለይም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከጀመሩበት ከስድስት ዓመታት ወዲህ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ መቀራረብን በተግባር ሲገልጹ ቆይተዋል፣ በመግለጽም ላይ ይገኛሉ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤን መርተዋል፣ የሕዝቦችን እድገት እና ልማት የሚመለከቱ ሐዋርያዊ መልዕክቶችን ይፋ አድረገዋል፣ ረጃጅም የሆኑ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉዞዎችን አካሂደዋል፣ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ውህደት የሚመሩ ጉባኤዎች እንዲካሄዱ ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ያከናወኗቸውን በርካታ ሌሎች ሐዋርያዊ ሥራዎችን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ችግሮች የተበራከቱበትን የሃያኛውን ክፍለ ዘመን የጨለማ ዓመታትን እና የቀዝቃዛ ጦርነት ዓመታትንም መዘንጋት የለብንም።

የፖለቲካ አቅጣጫ፣

መጨረሻዎቹን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታትን የተመለከትን እንደሆነ፣ ከተለያዩ የስነ ማሕበር ጠበብት ጋር ካካሄዱት ውይይት እንደምንረዳው፣ ከእነዚህም መካከል ከስነ ማሕበረሰብ ጠበብት ከሆኑት ከጁሴፔ ደ ሪታ ጋር ጣሊያን እና መላውን አውሮጳ ስላጋጠመው የፖለቲካ ቀውስ፣ የምዕራባዊያንን የፖለቲካ ቀውስ ለማስወገድ ካቶሊካዊ ምዕመናን የተጫወቱትን ሚና በተመልከተ በርካታ ውይይቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል። ከስነ ማሕበረሰብ ጠበብት ከሆኑት ከአቶ ጁሴፔ ደ ሪታ ጋር ውይይቶች ሲደረጉ፣ ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ መነሳቱ አይቀርም ነበር። በሃያኛው ክፍለ ዘመን፣ ከ1917 - 1925 ዓ. ም. ድረስ በነበሩ ካቶሊካዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ታሪክ ውስጥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ተሳትፎ ሰፊ እንደነበር አቶ ጁሴፔ ደ ሪታ ብዙ ጊዜ ተናግረዋል። ከአቶ ጁሴፔ ደ ሪታ ጋር ብቻ ሳይሆን በኢጣልያ ታዋቂ ከሚባሉ፣ በቁጥር 25 ከሚሆኑ የማሕበረሰብ እና የፖለቲካ ጠበብት ጋር ውይይት እና ቃለ መጠይቆች መደረጋቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ከማህበራዊ ኢንቨስትመንት ጥናት ማዕከል መስራች ጋር የተደረገው ውይይት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን የኦዜርቫቶረ ሮማኖ የተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ አዘጋጅ አቶ ሞንዳ ገልጸዋል። ኢጣሊያ ከወደቀችበት የማሕበራዊ እና የፖለቲካ ቀውስ ለመውጣት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ድርሻ ወይም እገዛ ሰፊ እንደነበር የገለጹት አቶ ሞንዳ፣ በተለይም ኢጣሊያን ከደረሰባት የጦርነት አደጋ ለማውጣት፣ ምንም እንኳን በቂ ድጋፍን ያገኘ ባይሆንም፣ በ ደ ጋስፓሪ የሚመራ የክርስቲያን ደሞክራሲ ፓርቲ መቋቋሙንም አቶ ሞንዳ ገልጸዋል። በዚያ ረጅም የችግር ወቅት፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ጋር የቅርብ ግንኙነት ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዱ አልዶ ሞሮ መሆናቸውን አቶ ሞንዳ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በአንድ ወቅት በላቴራን ቅዱስ ዮሐንስ ባዚሊካ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ስለ አልዶ ሞሮ መልካምነት፣ ገርነት፣ ጥበበኛነት፣ ግልጽነት እና ወዳጅነት መናገራቸውን አስታውሰው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት ከመወሰዳቸው ከሦስት ወራት በፊት፣ በ1970 ዓ. ም. ሕዝቡ ከገባበት ችግር እንዲወጣ በማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን መለመናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞናዳ ተናግረዋል።

እውነተኛ ክርስቲያን፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በተመለከተ ከብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሪ ባሴቲ ጋር ረጅም ውይይት መደረጉን የገለጹት አቶ ሞናዳ፣ ካርዲናል ባሴቲ በውይይታቸው አማካይነት፣ በዛሬ ዘመንም ጣሊያንን የሚያጋጥማትን የተለያዩ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማቃለል የለውጥ አራማጅ እና ገር፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች መኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ገርነት በእምነት ላይ የተመሠረተ፣ መልካም ባህሪን የሚከተል መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ አስረድተዋል። የለውጥ አራማጅ መሆን ደግሞ በዓለማችን እየተስፋፋ ያለውን የብቸኝነት፣ የወገንተኝነት፣ በሰዎች ላይ ልዩነትን በመፍጠር የፍርሃት እና የማግለል አዝማሚያን ለመዋጋት ስለሚረዳ ነው ብለው ወደ ፊት ሊከሰቱ የሚችሉትን ማሕበራዊ ቀውሶች አስቀድሞ የማወቅ ችሎታም ሊኖረን ይገባል ብለዋል። የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር እና የክርስቲያን ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባል የነበረውን ብጹዕ ጆርጆ ላ ፒራን አስታውሰው፣ ይህ ወጣት በገርነቱ፣ በእውነተኛ ክርስቲያንነቱ እና በለውጥ አራማጅነቱ፣ ዛሬ የምናስታውሳቸውን፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን መምሰል ይችላል ብለዋል። እሁድ ነሐሴ 30/1970 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ያቀረቡትን የመልዓከ-እግዚአብሔር ጸሎት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ክርስቲያናዊ ጥሪያችንን በተግባር ፈጽመን የምንገኝ፣ በወንጌሉ ቃል በመመራት አካሄዳችንን እንድናስተካክል፣ የምስጢረ ጥምቀት ቃላችንን የምንጠብቅ መሆን ይገባል ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛም ይህን ፈጽመው የተገኙ መሆናቸውን መላዋ ቤተ ክርስቲያን ትመሰክርላቸዋለች ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
07 August 2019, 15:05