ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በእኛ አማካይነት የተዘረጋው የኢየሱስ እጅ ሰዎች ከወደቁበት እንዲነሱ ያደረጋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በነሐሴ 01/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ባደረጉት የክፍል አምስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው በሐዋርያት ሥራ 3፡3-6 ላይ በተጠቀሰውና “ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤ እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስቲ ወደ እኛ ተመልከት” አለው። ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት አስቦ በትኵረት ተመለከታቸው። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው ሰውየው በእዚያን ወቅት ተፈወሰ”  በሚለው ጥቅስ ላይ ትኩረቱን ያደርገ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “በእኛ አማካይነት የተዘረጋው የኢየሱስ እጅ ሰዎች ከወደቁበት እንዲነሱ ያደረጋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 01/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተከናወነው ስብከተ ወንጌል በቃላት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም ፣ ነገር ግን ስብከተ ወንጌሉን ተጨባጭ እና እውነተኛ እንዲሁም በተግባር በተደገፈ መልኩ ነበር የተከናወነው። በእዚህም መሰረት ሐዋርያቱ የሚያከናውኑዋቸው ተግባራት በሙሉ በቃላት በመመስከር እና ይህንን የቃላቸውን እውነተኛነት ደግሞ በክርስቶስ ስም በሚያከናውኑዋቸው “ተዐምራት እና ድንቅ ምልኮቶች”  አረጋግጠዋል። የተፈጸመውም በእዚሁ መልኩ ነው፣ ሐዋርያቱ ያማልዳሉ፣ ክርስቶስ ደግሞ ይፈጽመዋል፣ ክርስቶስ ከእነሩስ ጋር በመተባበር ይሠራል፣ እነርሱ በቅላት የሚሰጡን ምስክርነት እርሱ ደግሞ በተግባር ተዐምራትን በመሥራት ያጅባቸዋል። ሐዋሪያት ያደረጉት ብዙ ምልክቶች፣ ብዙ ተአምራት የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕሪ የሚገልጹ ምልክቶች ናቸው።

ዛሬ እኛ ቀደም ሲል በሰማነው የፈውስ ታሪክ ውስጥ አንድ የተፈጸመ ተአምር እናገኛለን፣ ይህ የፈውስ ታሪክ ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተፈጸመው የመጀመርያው የፈውስ ታሪክ ነው። ይህ ታሪክ ግልፅ የሆነ የሚስዮናዊ ዓላማ አለው፣ እሱም እምነትን ማነሳሳት ነው። ጴጥሮስ እና ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ የእምነት ልምድ ማዕከል ነው ተብሎ ወደ ሚታሰበው ቤተ መቅደስ ለመጸለይ ይሄዳሉ፣ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ጠንካራ ግንኙነት ነበራቸው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በኢየስሩሳሌም ቤተመቅደስ ውስጥ ሆነው ይጸልዩ ነበር። ወንጌላዊ ሉቃስ ይህ ተአምር የተፈጸመበትን ሰዓት መዝግቦ ይዞ ነበር፣ ሕዝቡ ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ሕብረት መግለጫ ምልክት የሆነው መስዋእት በሚያቀርቡበት ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ እንደ ነበረ ይገልጻል፣ በተመሳሳይ ሰዓት ክርስቶስ “ለአንዴ እና ለመጨረሻ” ጊዜ ራሱን አሳልፎ የሰጠውም በእዚህ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ነበር። ወደ ቤተመቅደሱ የሚወስደው በር “ውብ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከተወለደበት ቀን አንስቶ ሽባ የነበረ አንድ ሰው ምጽዋት ይጠይቃቸዋል። ታዲያ ያ ሽባ የሆነ ሰው በእዚያ በር አጠገብ ለምን ተቀመጠ? የተቀመጠበት ምክንያት የሙሴ ሕግ (ዘለዋዊያን 21: 18 ላይ ይመልከቱ) የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች ለእግዚኣብሔር መስዋእት ማቅረብ እንደ ማይችሉ ስለሚከለክላቸው ሲሆን በእዚህም የተነሳ በቅጥር ግቢው በር ላይ ለመቀመጥ ተገዶ ነበር። ከተወለደበት እለት አንስቶ ዓይነ ስውር የነበረው አንድ ሰው ጋር ኢየሱስ በተገናኘበት ወቅት ሕዝቡ ኢየሱስን “ይህ ሰው እውር ሆኖ የተወለደበት ምክንያት እርሱ በሠራው ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” (ዮሐንስ 9፡2) በማለት የጠየቁትን ጥያቄ እናስታውሳለን። በዚያ አስተሳሰብ መሠረት፣ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲኖር የራሱን አሉታዊ ተጽኖ አሳድሩዋል። በኋላም ወደ ቤተመቅደሱ እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር። በእዚህም የተነሳ በብዙዎቹ የሕብረተሰብ ክፍል የተገለሉ ሲሆን በእዚህ የተነሳ ደግሞ በእየቀኑ ምጽዋት ለመለመን ተገደዋል። ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት አልቻለም፣ በበሩ ፊት ለፊ ተቀምጡዋል። ባልታሰበ ሰዓት ጴጥሮስ እና ዮሐንስ በእዚያ በር ማለፍ ይጀምራሉ። እርሱ እነርሱን ባየ ጊዜ እንደ ተለመደው ምጽዋት ይጠይቃቸዋል፣ እነርሱ ግን ለአፍታ ቆም ብለው ወደ እርሱ ትኩር ብለው እየተመለከቱ፣ እርሱም ለየት ባለ መልኩ እነርሱን እንዲመለከት እየጠየቁት አንድ ለየት ያለ ስጦታ እንዲቀበል ይጋብዙታል። ይህ ሽባ የነበረው ሰው ጴጥሮስን በሚመለከትበት ወቅት ጴጥሮስ ““እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” (ሐዋ 3፡6) በማለት ይነግረዋል። ሐዋርያት ከእርሱ ጋር ግንኙነት መሥርተዋል ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን ለመግለጥ የሚወደው በእዚህ መንገድ ነው፣ በግንኙነቱ ውስጥ ፣ ሁል ጊዜ በውይይት ውስጥ፣ ሁል ጊዜም በትዕግስት ፣ ሁል ጊዜም በልብ ተነሳሽነት: - የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር ግንኙነት የሚያደርግባቸው መንገዶች ናቸው፣ ከሰዎች ጋር በእውነተኛ መንገድ የምንመሰርታቸው ግንኙነቶች በፍቅር ሊጠንቃቀቁ ይችላሉ።

ቤተመቅደስ ሐይማኖታዊ ማዕከል ከመሆኑ በተጨማሪ ፣ የምጣኔ ሀብት እና የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግበትም ስፍራ ነበር፣ በእዚህ የተነሳ ነቢያት እና ኢየሱስ ራሱም ብዙ ጊዜ ጉዳዩን ወቅሰውት ነበር (ሉቃስ 19፡45-46)። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ብዙን ጊዜ በማስብበት ወቅት በአንዳንድ ቁምሳናዎች ውስጥ ቅዱሳን የሆኑ ምስጢራት አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ለገንዘብ ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጥ እናያለን! እባካችሁን! ደሃ የሆነች ቤተክርስቲያን ይሰጠን ዘንድ እግዚኣብሔርን እንጠይቀው። ያ ሽባ የነበረ ለማኝ ሰው ከሐዋርያቱ ያገኘው ገንዘብ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ የሆነውን የናዝሬቱን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነበር ያገኘው። ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢየሱስን ስም ጠራ ፣ ሽባውን በሕያዋን ስፍራ እንዲቆም አዘዘ፣ ቆሞ ይህንን በሽተኛ ይነካዋል፣ ከእዚያም በእጁ ይዞ ያነሳዋል፣ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ቅዱስ ዮሐንስ ክሮዞስቶም “የትንሣኤ ተምሳሌት” በማለት ይገልጸዋል። እናም የቤተክርስቲያን ሥዕላዊ መግለጫ እዚህ ላይ ይታያል ፣ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች በምታይበት ወቅት  ዐይኖቿዋን የማትጨፍን፣ ትርጉም ያለው ግንኙነት ለመፍጠር ያስችላልት ዘንድ፣ የወዳጅነት ድልድይ እና አንድነትን ለመፍጠር ያስችላት ዘንድ የሰዎችን ፊት አትኩራ የምትመለከት ቤተክርስቲያን ልትሆን ይገባታል። የሁሉም እናት የሆነች፣ እጅዋን ዘርግታ ሰዎችን ከወደቁበት የምታነሳ እና አብራቸው የምትጓዝ፣ ሰዎች ደስተኛ እና የተፈወሱ እንዲሆኑ የምታደርግ፣ ሰዎች ደስተኛ እንዲሆኑ እና ከእግዚኣብሔር ጋር እንዲገናኙ የምታደርግ ቤተክርስቲያን ድንበር የለሽ ቤተክርስቲያን ልትኖር ይገባል። ይህ “ሰዎችን ቀርቦ ሰላም በማለት፣  በአክብሮት የተሞላ እና ርህራሄን የሚያሳይ” በጥበብ የተሞላ ጓደኝነት በመፍጠር፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ሰዎችን የምታበረታታ ቤተክርስቲያን መገንባት ያስፈላጋል። እነዚህ ሁለት ሐዋርያት ሽባውን ሰው የተገናኙት በእዚሁ መልኩ ነው፣ ትኩር ብለው ተመለከቱት፣ እኛንም “ተመልከተን” አሉት፣ እጃቸውን ዘረጉለት፣ ተነስቶ እንዲቆም አደረጉት ከእዚያም ፈወሱት። ኢየሱስ ለእኛ ሁላችን የሚያደርገው እንዲሁ ነው።  በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ወቅት፣ ኃጢአት በምንሠራበት ወቅት፣ ሐዘን ውስጥ በምንገባበት ወቅት ሁሉ ይህንን ልብ ማለት ይገባናል። “ወደ እኔ ተመልከት” እኔ እዚህ ከአነተ ጋር ነኝ የሚለው ኢየሱስ ከአጠገባችን ይኖራል። ኢየሱ የሚዘረጋልንን እጅ እንያዝ፣ ወደ ላይ እዲያነሳን እንፍቀድለት።

ሐዋርያው ጴጥሮስ እና ሐዋርያው ዮሐንስ ምንም እንኳን ይህ ተአምር የተከሰተበት ሁኔታ አስፈላጊ ቢሆንም ከእርሱ ይልቅ እኛን በዋነኘንት የሚያስተምሩን ከሙታን ከተነሳው ጌታ ጋር እውነተኛ የሆነ ግንኙነት እንዴት መመስረት እንደ ሚቻል ያስተምሩናል። እኛ ግን ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሚለው “ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” (2ቆሮ 6፡10) እንደ ሚለው እንሆናለን ማለት ነው። የእኛ ሁሉ ነገራችን ተዓምራቶችን የሚያደርግ፣ የኢየሱስን ስም የሚገልጸው ቅዱስ ወንጌል ነው።

እኛ ሁላችን በሕይወታችን ውስጥ ይዘነው የምንገኘው ሐብት ምንድነው? የእኛ እውነተኛ ሐብት፣ የእኛ ውድ የሆነ ንብረት ምንድነው? ሌሎችን ባለጸጋ ማድረግ የምንችለው በምን መንገድ ነው? በሕይወታችን ውስጥ ስለሰጠን ፍቅር፣ በምስጋና መንፈስ የተሞላ ምስክርነት መስጠት እንችል ዘንድ፣ የማስታወስ ስጦታ ይሰጠን ዘንድ የእርሱን ጸጋ እንጠይቅ። ይህንን ልብ እንበል፣ እጆቻችን ሁልጊዜም ቢሆን ሌሎችን ከወደቁበት ለማንሳት የተዘረጋ ይሁን! በእኛ እጅ አማካይነት የተዘረጋው የኢየሱስ እጅ ሌሎች ሰዎች ከወደቁበት እንዲነሱ ያደረጋል።

 

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ
07 August 2019, 09:43