ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሞዛምቢክ ሕዝብ እርቅ እና ሰላም ጥረት እንዲሳካ ጸሎት አቀረቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከነሐሴ 29 ቀን ጀምሮ ወደ ሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው፣ የመጀመሪያ መዳረሻ አገር በምትሆን በሞዛምቢክ እርቅ እና ሰላም እንዲወርድ የሚደረገው ጥረት የተሳካ እንዲሆን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪ የአገሩ ሕዝብም ከእርሳቸው ጋር በጸሎት እንዲተባበሩ የሚያሳስብ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። በሞዛንቢክ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀው መሪ ቃል “ተስፋ፣ ሰላም እና እርቅ” የሚል መሆኑን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉባቸው የአፍሪቃ አገሮች ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ መሆናቸውን የሐዋርያዊ ጉዞአቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።  ቅዱስነታቸው ወደ ማዛምቢክ ሲደርሱ ከከፍተኛ የሀገሪቱ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች እና ከአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር የሚገናኙ ሲሆን ከአገሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትንም የሚያቀርቡ መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአገሩ ብሔራዊ ቋንቋ በፖርቱጊስ፣ ዓርብ ነሐሴ 24/2011 ዓ. ም. በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት፣ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በቅርብ ሊያገኙ የማይችሏቸውን  የገጠራማው አካባቢ ሕዝቦችን በጸሎታቸው የሚያስታውሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ወደ ብዙ ሥፍራዎች መድረስ ባይችሉም የውቂያኖስ መናወጥ ባስከተለው አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ቢያንስ 600 የሚሆኑ ሰዎችን እና በአደጋው ምክንያት አሁንም ችግር ላይ የሚገኙትን ቤተሰቦች በጸሎታቸው የሚያስታውሱ መሆናቸውን በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።     

እርቅ እና ሰላም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ሞዛምቢክን እንዲጎበኙ በማለት ግብዣን ያቀረቡት የአገሩን ፕሬዚደንት እና የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን አመስግነው፣ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የእርቅ እና የሰላም ጥረት የተሳካ እንዲሆን መላው የአገሩ ሕዝብ በጸሎት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። በሞዛምቢክ ሆነ በመላው አፍሪቃ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወንድማዊ እርቅን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በሞዛምቢክ እርቅ እና ሰላም እንዲመጣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያደረገችውን የረጅም ጊዜ ጥረቶችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በአገሪቱ የታጠቁ ቡድኖች መሪዎችን ከመንግሥት ጋር በማደራደር ረገድ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ያበረከተው ከፍተኛ ጥረቶች መኖሩን አስታውሰው፣ በነሐሴ ወር 2011 ዓ. ም. በአገሩ የፍሬሊሞ መንግሥት እና በታጣቂ ሬናሞ እንቅስቃሴ መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚስችል የሰላም ስምምነት መደረጉንም አስታውሰዋል። በሞዛምቢክ ከ1969 – 1984 ዓ. ም. በተደረገው ሃይለኛ የእርስ በእርስ ጦርነት ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች መሞታቸው እና እስካሁንም የንጹሐን ዜጎች ሕይወት በከንቱ የሚጠፋበት አመጽ ሲከሰት መቆየቱ ይታወቃል።

ለካቶሊካውያን ምዕመናን፣

ሞዛምቢክ በእርስ በእርስ ጦርነት በነበረችበት፣ በ1980 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ሞዛምቢክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣ በዚያን ወቅት እርሳቸው የዘሩት የሰላም ዘር ፍሬን እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል። ከነሐሴ 29/2011 ዓ. ም. ጀምሮ በሞዛምቢክ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከአገሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር በመሆን ለሰው ልጆች ሰብዓዊ ክብር እና እኩልነት፣ በተለይም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ ልብን በመክፈት በጋራ የወንጌል ምስክርነትን የሚያሳዩበት እንደሆነ ገልጸዋል።   

ምስጋና እና ጸሎት

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በአፍሪቃ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ እና በጸሎትም የሚተባበሩትን በሙሉ አመስግነው እግዚአብሔር የሞዛምቢክን ሕዝብ እንዲባርክ፣ የእመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጥበቃ ተማጽነዋል። 

30 August 2019, 15:35