ፈልግ

አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ምርምር የተካሄደ አዲስ መጽሐፍ፤ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ምርምር የተካሄደ አዲስ መጽሐፍ፤  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕዝባዊ የዕድገት እንቅስቃሴዎች ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ።

አንድ ሺህ በሚሆኑ ልዩ ልዩ ማሕበራዊ የዕድገት እንቅስቃሴዎች ላይ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ምርምር ከተካሄደ በኋላ ለሕትመት በበቃው አዲስ መጽሐፍ ላይ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሰፈሩት የመግቢያ ጽሑፍ ላይ፣ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ሁሉ አቀፍ የሆነ ዕድገት እና ለውጥን ለማምጣት የሕዝባዊ ማሕበራት መኖር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አዳዲስ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ለውጦችን ለማምጣት፣ የሕዝባዊ ማሕበራት መቋቋም” በሚል አርዕስት በቫቲካን ማተሚያ ቤት የታተመው እና በደቡብ አሜሪካ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ተዘጋጅቶ ይፋ የሆነው አዲሱ መጽሐፍ በስፓኒኛ ቋንቋ መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። የታተመው መጽሐፍ ከ2006 ዓ. ም. ጀምሮ በተለያዩ የደቡብ አሜሪካ አገሮች የተካሄዱትን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝባዊ የልማት ማሕበራት የተሳተፉበትን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ያገናዘበ መሆኑን የዜና አገልግሎቱ አክሎ አስታውቋል።

ማሕበራዊ ለውጥ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አዲስ በታተመው መጽሐፍ መቅድም ላይ እንደገለጹት፣ በማሕበረሰብ መካከል አስተዋይ ያጡ እና የተገለሉ ሰዎች በቤተክርስቲያን ብቻ የሚታገዙ መሆን የለባቸውም ብለው፣ እነዚህ ሰዎች ድጋፍ ከተደረገላቸው እንደ ሰናፍጭ ዘር ብዙ ቡቃያን ማፍራት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ከማሕበረሰቡ የተገለሉትንም ጭምር የሚያሳትፉ ሕዝባዊ የልማት ማሕበራት፣ ጠንካራ እና ሁሉ አቀፍ ማሕበራዊ እድገትን ማምጣት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። የተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ተጭኖባቸው ለድህነት የተዳረጉ የማሕበረሰቡ ክፍሎች ሁል ጊዜ እንደ ተረጂ መቆጥር እነደሌለባቸው አሳስበው፣ በእድገት ውጥኖች ተሳታፊ ሆነው ከተገኙ ለወደ ፊት ማሕበራዊ ሕይወታቸው ትልቅ አስተዋጽዖን ሊያበረክቱ የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የተለያዩ አማራጮች እንዲኖሩ ለማድረግ ወሳኝ ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በየጊዜው በሚያሰሙት ጩሄት እና ተቃውሞ ለውጥን የሚያመጣ  ተስፋን ሊያስገኙ ይችላሉ ብለዋል። በጉልበት መበዝበዝ እና በድህነት መሰቃየት ለሌላው ወገን የሃብት ማከማቻ መንገድ መሆኑን በትክክል የሚገነዘቡ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣ ለሁሉ አቀፍ ማሕበራዊ ዕድገት ትልቅ ሚናን የሚጫወቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዴሞክራሲን ማሳደስ ያስፈልጋል፣

በዘመናችን የሰው ልጅ የፍርሃት እና የዘረኝነትን አደጋ እየተጋፈጠ እንደሚገኝ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ይህን ለመከላከል እና ለመቋቋም ችሎታ አላቸው ብለው፣ ችሎታቸው የሚመነጨው ዴሞክራሲን ማደስ በሚችል በስነ ምግባር ሃይል የታገዙ በመሆናቸው ነው ብለዋል። ሕዝባዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ሃይልን እና ጥንካሬን የሚያገኙት በጥሩ ሁኔታ የተደራጁ ዜጎች ከሚያበረክቱት አስተዋጽዖ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እያንዳንዱን ዜጋ ያሳተፉት ሕዝባዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የግልን ሳይሆን ማሕበራዊ ጥቅምን ስለሚያስቀድሙ ነው ብለዋል።

የሥራ ፍሬን ከማይጠቅም ባሕል መለየት ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕትመት ለበቃው አዲስ መጽሐፍ ባሰፈሩት የመግቢያ ጽሑፋቸው የሥራ ክቡርነትን ሲገልጹ፣ በሰው ልጅ እጅ እና አእምሮ የሚከናወን መልካም ሥራ ክብር እና ዋስትና ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበው፣ የቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምሕሮ ፈለግን የተከተለ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ጠንካራ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የማሕበረሰቡን የኑሮ ወግ የሚቃረኑ አንዳንድ አዳዲስ ባሕሎችን ለመዋጋት ዋና መሣሪያ እንደሆኑ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣ ማሕበራዊ አንድነት ለማሳደግ የሚረዱ አዳዲስ የሥራ ዘርፎችን የሚፈጥሩ ከሆነ ለማሕበረሰቡ የሚያበረክቱት አገልግሎት ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በሰዎች መካከል ልዩነቶችን የሚፈጥር፣ ለማሕበራዊ ጥቅም ደንታ የማይሰጥ፣ በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች  ውስጥ ለወደቁት የማይራራ ባሕልን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ስብዕናን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

           

20 August 2019, 16:49