ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ዝም እንድንል በሚያዙን ሰዎች ፊት በድፍረት መናገር እንችል ዘንድ እንዲረዳን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ እንጠይቅ”!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በነሐሴ 22/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ባደረጉት የክፍል ሰባት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው በሐዋርያት ሥራ 5፡12,15-16 ላይ በተጠቀሰውና በሐዋርያት እጅ ብዙ ሰዎች መፈወሳቸውን በሚገልጸው ጭብጥ ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ሐዋርያትም በሕዝቡ መካከል ብዙ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎችን አደረጉ፤ አማኞቹም ሁሉ ‘የሰሎሞን ደጅ’ በተባለው መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር። ከዚህም የተነሣ፣ ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ፣ ቢያንስ ጥላው እንኳ በጥቂቶች ላይ እንዲያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን ወደ ውጭ እያወጡ በዐልጋና በቃሬዛ በመንገድ ላይ ያስተኙ ነበር። በኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች፣ ሕመምተኞችንና በርኵሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ይዘው የሚመጡት ሰዎች አካባቢውን ያጨናንቁት ነበር፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው “ዝም እንድንል በሚያዙን ሰዎች ፊት በድፍረት መናገር እንችል ዘንድ እንዲረዳን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ እንጠይቅ” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 22/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው የቤተክርስቲያኑ ማህበረሰብ ይጠቀሙበት ዘንድ ጌታ እጅግ ብዙ አንጡራ የሆኑ ድንቅ ነገሮችን በመካከላቸው ያኖረው ሲሆን ምንም እንኳን ውጫዊ የሆነ ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየደርሰባቸው እና እየረበሻቸው የነበረ ቢሆንም ቅሉ በተቃራኒው ደግሞ ጌታ ባቀደው መሰረት የማኅበረ አማኙ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨምረ መምጣቱን እንመለከታለን። የእዚህን ሁኔታ አስፈላጊነት ለማሳየት በማሰብ ቅዱስ ሉቃስ (ሐዋ 5፡12) “የሰሎሞን ደጅ’ በተባለው መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር” በማለት ክርስቲያኖች ይሰበሰቡ የነበረበትን ቦታ አሰፍላጊነት ጭምር ገልጾልናል። “የሰለሞን ድጅ” በመባል የሚታወቀው በር እንደ መጠለያ ያገለግል የነበረ፣ ነገር ግን በተጨማሪም የስብሰባ ቦታ እና ለምስክርነት የሚያገለግል ክፍት ማዕከለ ነበር። ይህ ስፍራ በታላላቅ በዓላት ወቅት ኢየሱስ ይመላለስበት የነበረ ስፍራ ሲሆን (ዮሐ 10፡23 ይመልከቱ) ሽባ የነበረው ሰው ከሕመሙ ተፈውሶ ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጎን ለጎን የሄደበት ስፍራ ነው፣ እንዲሁም ጴጥሮስ በኢየሱስ ስም  ማመን በእርሱ ፍውስ እንደ ሚያመጣ ለሕዝቡ የሰበከበት ሥፍራ ጭምር ነው። ስለሆነም ይህ “የሰለሞን በር” በመባል የሚታወቀው ስፍራ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ አማካይነት እኛን የሚገናኝበት፣ ልባችንን የሚነካበት፣ አካላችንን የሚፈውስበት ቦታ ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በእርግጥ ያተኩር የነበረው ሐዋርያት ከሚናገሩት ቃል ጋር መሳ ለመሳ በመሆን የሚከናወኑትን ምልክቶች እና ተአምራት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን በተለይም ደግሞ በልዩ ሁኔታ ለተፈወሱ ሰዎች የሚደረገውን መንፈስዊ እንክብካቤ እና ድጋፍ ይገልጻል።

በሐዋርያት ሥራ 5 ውስጥ የምትገኘው በወቅቱ ትንሽ የነበረችው ቤተክርስቲያን እራሷን “ተንቀሳቃሽ ሆስፒታል” አድርጋ ታቀርባላች የታመሙ ሰዎች የሚፈወሱበት ሥፋር እንደ ሆነች ትገልጻለች። የእነዚህ የታመሙ ሰዎች ስቃይ “ብርም ሆነ ወርቅ” የሌላቸውን ሐዋርያት ቀልባቸውን ይማርካል (ሐዋ. 3 6) ነገር ግን በኢየሱስ ስም ጠንካራ መሆናቸውን ያሳያል። በዓይኖቻቸው ውስጥ፣ በሁሉም ዘመን ውስጥ በሚገኙት ክርስቲያኖች ዘንድ እንደታየው፣ የታመሙ ሰዎች የመንግሥተ ሰማይ መልካም ዜና ተቀባዮች እነርሱ እንደ ሆኑ የገለጹ ሲሆን ክርስቶስ ራሱ ልዩ በሆነ ሁኔታ በእነርሱ ውስጥ የሚገኝ ወንድሞቻችን እንደ ሆኑም ያሳያል።

ከሐዋርያት መካከል ልቆ ይታይ የነበረው ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት ከእነርሱ መካከል “አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም” (ማቴ 16፡18) ብሎ ኢየሱስ በመናገሩ የተነሳ እና እንዲሁም ኢየሱስ ጴጥሮስን “በጎቼን መግብ” (ዩሐ 21፡15-17) ብሎ በሰጠው ተልዕኮ የተነሳ ነው። በበዓለ ሃምሳ ቀን ስብከተ ወንጌል ማድረግ የጀመረው እሱ ነው (ሐዋ. ሥራ 2: 14-41) በኢየሩሳሌም ተደርጎ የነበረውን ጉባሄ የመራው እርሱ ነው (ሐዋ 15, ገላ. 2፡1-10)።

ኢየሱስ በተልዕኮ ወቅት ሲያደርገው እንደ ነበረው ዓይነት ጴጥሮስም የእርሱን ፈለግ ተከትሎ በቃሬዛ ላይ በነበሩ ሕመምተኞች እና በስቃይ ላይ በሚገኙ ሰዎች መካከል ይመላለስ ነበር (ማቴ 8፡17, ኢሳ 53፡4)። በገሊላ ክፍለ አገር ውስጥ የዓሣ አጥማጅ የነበረው ሰው ከአሁን በኋላ የዓሣ ሳይሆን የሰዎችን ልብ እንዲያጠምድ እና እንዲስብ ተጠርቱዋል የክርስቶስ ተልዕኮን እንዲያስቀጥል ተመርጡዋል። ጴጥሮስ በታመሙ እና በተሰቃዩ ሰዎች መካከል ይመላለሳል ተግባሩን ግን ክርስቶስ እንዲፈጽም ለእርሱ ይተዋል። ይህንን ተአምር በቃላት እና በተግባር የሚገልጸው ክርስቶስ ሲሆን ጴጥሮስ የሚናገረውን ነገር ክርስቶስ በተግባር ያረጋግጥለታል፣ ምስክርነቱንም ያጸናል። የእግዚአብሔር አካል የተገለጠበትን በጴጥሮስ የሚኖረውን ክርስቶስ ያሳያል፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጅ ማደሪያ የሆነቺው ማርያም “እንዳልከኝ ይሁንልህ” ለሚለው ቃሉዋ ምስጋና ይግባውና የሰው አካል የእግዚአብሔር ማደሪያ ሆነ፣ በምስጢረ ጥምቀት የእግዚኦኣብሔር ቤተመቅደስ ሆነ (1 ቆሮ 6፡19)። የአማኞች አካል በእምነት ሕይወት ውስጥ እንደ አንድ ባእድ የሆነ አካል ተደርጎ የሚቆጠር ሳይሆን ነገር ግን ከእግዚአብሄር እና ከሌሎች ጋር ህብረት እንዲኖር ፣ በአብ መልክ እና አምሳል የተፈጠረ እና የልጅነት ውበት እንዲገለጥ ተደርጎ የተፈጠረ ነው።

የጌታን ሥራ የፈፀመው ጴጥሮስ ነው (ዮሐ 14 12 ተመልከት) በእምነት ክርስቶስን እየተመለከተ ክርስቶስ እራሱን ይመለከታል። በጌታው መንፈስ ተሞልቷል ፣ ጴጥሮስ በበሽተኞች መካከል ያልፋል እናም እርሱ ምንም ሳያደርግ የእርሱ ጥላ ይፈውስ ነበር፣ የልብ እርፈት ይሰጣል፣ የታመመውን በማዳን ሕይወት የሚሰጥ ድህንነትን የሚያረጋግጥ እና ክብራቸውን መልሰው እንዲጎናጸፉ የሚያደርግ ነው። በእዚህ ሁኔታ እግዚኣብሔር ለታመሙ ሰዎች ያለውን ርኅራኄ እና ቅርበት ይገልጻል። የጴጥሮስ ጥላ ከሙታን የተነሳውን የክርስቶስን ብርሃን ያንጸባርቃል፣ ሕሙማን ከተፈወሱ በኋላ ለእግዚኣብሔር ክብር በመስጠት እግዚኣብሔርን ያመሰግኑ ነበር። የቤተክርስቲያን መገለጫ የሆነው ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ የእርሱ ጥላ በቤተክርስቲያን ላይ ያርፋል ቤተክርስቲያንን ያበራል፣ በምድር ላይ ባሉ ልጆቹ ላይ ያርፋል ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዲመለክቱ ይረዳል።

የጴጥሮስ የፈውስ እርምጃ ሐዋርያትን ለእስራት የዳረገ እና ምስጢራዊ በሆነ መልኩ ከእስር ቤት ነጻ የወጡበት፣ ከእንግዲህ ወዲህ በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ያገዱዋቸውን የሰዱቃውያንን የጥላቻ ስሜት ያነሳሳል። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለክርስቲያናዊ ሕይወት ቁልፍ በሆነ መልኩ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይሻላል” (ሐዋ. 5፡29) በማለት መልስ ሰጠ፣ ያለምንም መዘናጋት፣ ያለ መዘግየት፣ ያለ ስሌት እግዚአብሔርን ማዳመጥ ይሻላል፣ ለእርሱ መታዘዝ ደግሞ ለእርሱ ጋር ቃል ኪዳን የምንገባበት እና በመንገዳችን ላይ ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር የመገናኘት ችሎታ ከፍ ያደርጋል።

እኛን ዝም ለማሰኘት በሚጥሩ ሰዎች ፊት ለፊት ያለምንም ፍራቻ በድፍረት መናገር እንድንችል፣ ለሕይወታችን እንኳን ሳንሳሳ በድፍረት መናገር እንድንችል ይረዳን ዘንድ የመንፈስ ቅዱስን እገዛ እንጠይቅ። ከጎናችን አፍቃሪ እና አጽናኝ የሆነው ጌታ መኖሩን እርግጠኛ እንድንሆን እንዲረዳን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ እንጠይቅ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 August 2019, 12:50