ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የሕይወት ጨለማን ማብራት ይቻለን ዘንድ የእምነት መብራት ማብራት ይኖርብናል!”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌለ አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት በነሐሴ 05/2011 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 12፡32-48 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችም ምሰሉ” በሚለው ነቅቶ ስለ መጠበቅ በሚያወሳው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ጨለማ ለማብራት ይቻለን ዘንድ የእምነትን መብራት ማብራት ይኖርብናል” ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ውስጥ (ሉቃስ 12፡32-48 ይመልከቱ) ኢየሱስ ደቀ-መዛሙርቱን በቋሚነት ነቅተው ይጠብቁ ዘንድ ያሳስባቸዋል። ለምን? በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጉዞ ለመረዳት ይቻል ዘንድ ነው፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ወደ ሕይወታችን ውስጥ ይገባል። እናም ነቅተን ለመኖር የምንችልባቸውን መንገዶች በማሳየት “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን” (ሉቃስ 12፡35) ይለናል። ይህ ቅድመ ሁኔታ ነው። በመጀመሪያ “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ” የሚለው ሐረግ በራሱ ለጉዞ የሚደረገውን ዝግጅት የሚያመለክት ሲሆን በአጠቃላይ ጉዞ ለማደረግ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅን ያመለክታል። ምቾት በሚሰጡን ነገሮች እና ደህንነታችንን በሚያረጋግጡ ምቹ በሆኑ ግንቦች ውስጥ ተከልሎ መኖር እና ሥር መሰረታችንን በእነዚህ ነገሮች ላይ እንዳናደርግ የሚያሳስበን ሲሆን ነገር ግን ከእነዚህ ነገሮች ተላቀን በሕይወታችን ውስጥ ወደሚቀጥለው እግዚአብሔር ወደ ሚመራን ግብ በመራመድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔር በሕይወታችን ውስጥ ይመላለስ ዘንድ በእምነት እና በትህትና ራሳችንን ለእርሱ ክፍት ማደረግ ማለት ነው። በዚህ አስቸጋሪ የሕይወት ጉዞ ውስጥ ስህተት እንዳንሥራ ጌታ ሁል ጊዜ እጃችንን በመያዝ ከእኛ ጋር አብሮ ይጓዛል። በእውነቱ ፣ በእግዚአብሄር የሚታመኑ ሰዎች የእምነት ሕይወት እንዲሁ ዝም ብሎ ቀጥ ብሎ የቆመ ነገር ሳይሆን ተንቀሳቃሽ የሆነ ነገር መሆኑን ይረዱታል። የእምነት ሕይወት-ጌታ ራሱ በየቀኑ ወደ ሚያመለክተው ወደ አዳዲስ ደረጃዎች የሚወስድ ቀጣይ ጉዞ ነው። ምክንያቱም እርሱ አስገራሚ፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጽም፣ እውነተኛ የሆኑ አዳዲስ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ እንዲከሰቱ የሚያደረግ ጌታ ነው።

በቀዳሚነት የነበረው ቅድመ ሁኔታ “በአጭሩ ታጥቃችሁ ጠብቁ” የሚለው ሲሆን ከእዚያ በመቀጠል ደግሞ የሌሊት ጨለማን ማብራት ይቻል ዘንድ “መብራትችሁ የበራ ይሁን” ይለናል። የሕይወትን “ሌሊቶች” ብርሃን ማብራት የሚችል እውነተኛ እና የበሰለ እምነት እንዲኖር ተጋብዘናል። ሁላችንም ብንሆን በሕይወት ሂደታችን ውስጥ የጨለሙብን መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ነበረ እናውቃለን። የእምነት አምፖሎቻችንን ለማብራት እንችል ዘንድ ከኢየሱስ ጋር ከልብ በመጸለይ እና ቃሉን በማዳመጥ ሕይወታችንን በእምነት ብርሃን ሁል ጊዜ መመገብ ይጠይቃል። ከእዚህ ቀደም ብዙን ጊዜ ደጋግሜ የተናገርኩትን አንድ ነገር ዛሬም ቢሆን በድጋሚ ለማንሳት እፈልጋለሁ፣ አንዲት ትንሽ የሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በኪሳችሁ እና በቦርሳችሁ ውስጥ አድርጋችሁ በመሄድ አንብቡት። ይህም ከኢየሱስ እና ከቃሉ ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድትገናኙ ይረዳችኋል። በጸሎት እና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘ ይህ መብራት ለሁሉም ሰዎች መልካም አገልግሎት ይሆን ዘንድ እንድናውለው በአደራ ተሰጥቶናል፣ ስለሆነም ማንም ሰው የራሱን ድነት ብቻ በእርግጠኝነት አይመለከትም፣ የሌሎች ሰዎችን ድነት ጭምር የመለከታል። አንድ ሰው የራሱን ውስጥ ብቻ በራሱ ኃይል ማብራት ይችላል ብሎ ማመን በራሱ ቅዤት ነው። እውነተኛ እመንት ራሱን ለሌሎች ክፍት ያደርጋል፣ ከወንድሞቹ ጋር መልካም የሆነ ሕበረት ይፈጥራል፣ በተለይም ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነትን መፍጠር ያለመክታል። እናም ኢየሱስ ይህንን አመለካከት በሚገባ እንድንገነዘብ ለማድረግ ከሠርጉ ሲመለስ የጌታውን መምጣት የሚጠባበቁትን አገልጋዮች ምሳሌ (ሉቃስ 12፡36-40) በመናገር ነቅተን የምንጠብቀበትን ሌላ መንገድ በመጠቆም፣ በመጨረሻው ቀን ከጌታ ጋር ለመገናኘት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን መጠበቅ እንደ ሚገባን ያመለክታል። እያንዳንዳችን በእዚያ የመጨረሻ ቀን ከእርሱ ጋር ፊት ለፊት መገናኘታችን አይቀሬ ነው። እያንዳንዳችን በመጨረሻው ቀን ከኢየሱስ ጋር የምንገኛኝበት ቁርጥ ቀን እንዳለን መዘንጋት አይኖርብንም። ኢየሱስ “ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ 1፡37-38) በማለት ይናገራል። በእነዚህ ቃላት ጌታ ሕይወት ወደ ዘላለማዊነት የሚደረግ ጉዞ መሆኑን ያስታውሰናል፣ ስለዚህ “ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን” (ዕብ 13፡14) የሚለውን በፍጹም ሳንዘነጋ ለእኛ የተሰጡን መክሊቶች ፍሬ እንዲያፈሩ ማደረግ ይኖርብናል። በዚህ አተያይ፣ እያንዳንዱ ጊዜ ውድ ይሆናል፣ ስለሆነም በእዚህ ምድር ላይ በምንኖርበት ወቅት ሁሉ ለሰማይ ቤት ያለንን ከፍተኛ ናፍቆት በመግለጽ ልንኖር ይገባናል፣ እግሮቻችንን በእዚህ ምድር ላይ በማደረግ፣ በእዚህ ምድር ላይ በመጓዝ፣ በእዚህ ምድር ላይ ሆነን በመሥራት፣ በእዚህ ምድር ላይ ሆነን መልካም የሚባሉ ተግባራትን በማከናወን፣ ልባችን እና አእምሮዋችን የሰማይ ቤትን እንዲናፍቁ ማደረግ ይኖርብናል።

ይህ ታላቅ ደስታ ምንን እንደሚያካትት በትክክል መረዳት አንችልም፣ ሆኖም ኢየሱስ ጌታቸው በተመለሰበት ሰዓት እና ወቅት ነቅተው ያገኛቸውን አገልጋዮቹን “እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል” (ሉቃ 12፡37) ብሎ ጌታው የተናገረው ቃል በእኛም ላይ እንደ ሚተገበር ለመገመት ይቻላል። የሰማይ ቤት ዘላለማዊ ደስታ በዚህ መንገድ ይገለጣል፦ ሁኔታው ወደ ጌትነት ይቀየራል፣ እናም አገልጋይ የሚባል ሰው አይኖርም፣ እግዚአብሔር እኛን ለማገልገል ራሱን ለእኛ ያቀርባል። አሁን ኢየሱስ ለእኛ እያደረገ የሚገኘው ጉዳይ ይህ ነው፣ ኢየሱስ ስለ እኛ ይጸልያል፣ ኢየሱስ ወደ እኛ ይመለከታል፣ ስለእኛ ወደ አባቱ ጸሎቱን ያቀርባል፣ ኢየሱስ አሁንም ቢሆን እኛን እያገለገለን ይገኛል፣ እርሱ የእኛ አገልጋይ ነው። እናም ይህ ትክክለኛ ደስታ ይሆናል። በመጨረሻው ዘመን በምህረት ከተሞላው ከእግዚኣብሔር ጋር መገናኘታችንን ማሰቡ በራሱ በተስፋ ይሞላናል፣ ንጹህ እና ነቀፋ የሌለብን ሆነን ለመገኘት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድንተጋ ያነሳሳናል። የበለጠ በፍትሐዊነት እና በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ ዓለም እንድንገነባ ያነሳሳናል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ጥረታችንን በእናታዊ አመላጅነቷ እንድትደግፈው ልንማጸናት ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 August 2019, 13:01