ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሐብት ለማግኘት ያለን ጉጉት የጭንቀት፣ የመከራ፣ የችግርና የጦርነት ምንጭ ነው” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌለ አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት በሐምሌ 28/2011 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 12፡13-21 ላይ ተወስዶ በተነበበውና  “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’ “እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊውስዱት  ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው፣ በሚለው የሀብታሙ ሰው ሞኝነት በተመለከተ በሚተርከው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ስብከት “ሀብትን ለማግኘት ያለን ከፍተኛ ጉጉት የጭንቀት ፣ የመከራ ፣ የችግር እና የጦርነት ሁሉ ምንጭ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል  (12፡13-21 ላይ ይመልከቱ) የሚጀምረው በሕዝቡ መካከል ቆሞ የነበረ አንድ ሰው የቤተሰቡን ውርስ በተመለከተ ህጋዊ መልስ እንዲሰጠው ኢየሱስን በጠየቀው ጥያቄ ይጀምራል። ነገር ግን እርሱ ማለትም ኢየሱስ ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ አልሰጥም ነበር፣ እናም ከስግብግብነት ማለትም ርስት ከመሰብሰብ እንድንርቅ ያሳስበናል። ሐብትን ለማጋበስ ከሚደረገው ማነኛውም ሩጫ አድማጮቹ እንዲርቁ ለማሳሰብ ፈልጎ ኢየሱስ ብዙ ሐብት በማከማቸውቱ የተነሳ ደህንነቱን እንዳስጠበቀ የሚያስብ እና ደስተኛ ነኝ ብሎ ያምን የነበረውን የአንድ ሞኝ ሐብታም ምሳሌ ይነግራቸዋል። እናም በእዚህ በሉቃስ ወንጌል 12፡13 ላይ የተጠቀሰውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ብታነቡት መልካም ነው። በጣም ብዙ ነገር የምንማርበት መልካም የሆነ ምሳሌ ነው። ሀብታሙ ሰው ለራሱ ሕይወት በሚያቀርበው እቅድ እና እግዚአብሔር ለእርሱ ለሐብታሙ ሰው በሚያቀርበው ሐሳብ መካከል ያለው ንጽጽር ለእዚህ ምሳሌ ሕይወት ይሰጣል።

ሐብታሙ ሰው በራሱ ሕይወት ፊት ለፊት ሦስት የተለያዩ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል፣ እነዚህም “ነፍሴ ሆይ፤ ብዙ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ ይህ ሐብት ደግሞ ለብዙ አመት የሚበቃሽ ነው” በማለት በነፍሱ ፊት ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ “ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ እላታለሁ” (ሉቃስ 12፡19) በማለት ይናገራል። እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረው ቃል ግን የእሱን የሕይወት እቅዶች ፉርሽ ማደረግ የሚችል ቃል ነበር። ከ “ብዙ አመታት” ይልቅ “ዛሬ ማታ፣ ዛሬ ምሽት ትሞታለህ”፣ ከ “ሕይወትና ከደስታ ይልቅ” በምትኩ “ሕይወቱ ዛሬውኑ እንደ ሚነጠቅ” ሕይወቱን በእግዚኣብሔር ፍርድ ፊት እንደሚያቀርብ” ይገልጽለታል። ሀብታሞች ሁሉንም ነገር ማግኘት የፈለጉባቸውን ብዙ የተከማቸ ንብረት በተመለከተ ያለውን እውነታ ሲገልጽ “ታዲያ ይህ ያከማቸኸው አብት ለማን ይሆናል?” በሚል ጥያቄ ይሸፈናል። እኛ ውርስን በተመለከተ ግብግብ እንፈጥራለን፣ ውርስን በተመለከተ በቤተሰብ ውስጥ ብዙ ግጭቶችን እንፈጥራለን። በሞት አፋፍ ላይ በምንሆንበት ወቅት ብዙ ሰዎች ወደ እኛ መምጣት እንደ ሚጀምሩ ከብዙ ታሪኮች መረዳት እንችላለን፣ የልጅ ልጆች ፣ ወይም ልጆች ወደ እኛ በመምጣት “ለእኔ የሚደርሰኝ ምንድነው?” በማለት ያለህን ነገሮች ሁሉ ተቀራምተው ይወስዱታል። በዚህ አግባብ አንተ “ሞኝ” ብሎ እግዚኣብሔር መናገሩ ትክክል ነው፣ ምክንያቱም ይህ ሐብታም ሰው ተጨባጭ ናቸው ብሎ የተማመናቸው ሐብቶቹ ሕልም ሆነው እንደ ሚቀሩ እግዚኣብሔር በመግለጹ የተነሳ ነው። ይህ ሐብታም ሰው ሞኝ የነበረ ሰው ነው፣ ምክንያቱም በተግባር እግዚአብሔርን በመካዱ እና እርሱ ሒሳቡን ከእግዚኣብሔር ጋር ባለማወራረዱ የተነሳ ነው።

ወንጌላዊው ይህንን ምሳሌ የደመደመው “ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው” (ሉቃስ 12፡21)  በማለት ነገሮችን ግልጽ በሆነ ሁኔታ በማስቀመጥ ነው። ይህ ሁላችንም በጥንቃቄ እንድንመለከተው የሚጋብዘን ማስጠንቀቂያ ነው።  ቁሳቁሶች አስፈላጊ ናቸው፣ ጠቃሚም ናቸው! ነገር ግን እነርሱ በሐቀኝነት ለመኖር እና በጣም ችግረኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመካፈል እንድንኖር የሚረዱን መንገዶች መሆን ይኖርባቸዋል። ሀብት ልብን ማሰር እና በሰማይ ካለው እውነተኛ እና ውድ ሀብት ሊለየን እንደሚችል ኢየሱስ በእዚህ ረገድ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይጋብዘናል። ቅዱስ ጳውሎስ ዛሬ በሁለተኛው ንባቡ ይህንን ያስታውሰናል። እንዲህም ይላል “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን” (ቆላሲያስ 3፡1-2)።

ይህን እኛ እንረዳለን - ከእውነታው መራቅ ማለት ሳይሆን፣ ነገር ግን እውነተኛ ዋጋ ያላቸውን ፍትህን ሕብረትን፣ ለሎችን ተቀብሎ ማስተናገድን፣ ወንድማማችነትን፣ ሰላምን፣ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚያረጋግጡ መልካም ነገሮችን ሁሉ መፈለግ ማለት ነው። በዓለማዊ መንፈስ የተሞላ የሕይወት ዘይቤን መከተል የሚያመልክት ሳይሆን ነገር ግን ዓላማ ላለው እና እውነተኛ የሆነውን የቅዱስ ወንጌልን ዘይቤ የተከተለ ሕይወት መኖር ማለት ነው፣ ይህም ማለት እግዚአብሔርን በፍጹም ነፍሳችን መውደድ ፣ ባልንጀራችንን ኢየሱስ በወደደው መልኩ መውደድ፣ ሌሎችን ማገልገል እና ለሌሎች አገልግሎት ራስን ማዘጋጀት ማለት ነው። ለቁሳቁሶች ያለን ስግብግብነት፣ ቁሳቁሶችን የማጋበስ ከፍተኛ ፍላጎት፣ ልብን አያረካውም ፣ ይልቁንም የበለጠ ረሃብን ያስከትላል! ስግብግብነት እንደ አንድ ጥሩ ከረሜላ ነው፣ አንድ ጊዜ ወስደህ ከበላኸው በኋላ “ውይ! እንዴት ጣፋጭ ነው፣ ብለን ከተናገርን በኋላ ሌላ ተጨማሪ ወስደህ ትበላለህ፣ አሁንም ማቆሚያ በሌለው መልኩ እየወሰድክ ትበላለህ። ስግብግብነት ይህንን ይመስላል፣ በፍጹም እንድትጠግብ አያደርግህም። ስለእዚህ ጥንቃቄ ማደረግ ይገባናል! የእውነተኛ የደስታ ምንጭ የሚሆነው ደግሞ በፍቅር ሕይወት ጎዳና ላይ መራመድ እና እውነተኛ በሆነ መንገድ ፍቅርን መግለጽ ሲቻል ብቻ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ቁሳዊ ነገሮችን እና ሀብትን ለማግኘት ያለን ከፍተኛ ጉጉት የጭንቀት ፣ የመከራ ፣ የችግር እና የጦርነት ምንጭ ነው። በጣም በርካታ ጦርነቶች የሚፈጠሩት በስግብግብነት መንፈስ የተነሳ ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ኃላፊ በሆኑ ሐብቶች እንዳንደናቀፍ ትርዳን በእየእለቱ የቅዱስ ወንጌል እሴቶችን በተማኝነት መመስከር እንችል ዘንድ በአማልጅነቷ እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 August 2019, 16:28