ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የማርያም ደስታ የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው” አሉ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በነሐሴ 09/2011 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ ያረገችበት የፍልሰታ በዓል ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህንን ታላቅ በዓል በምናከብርበት ወቅት ምልከታችንን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በምትገኝበት በሰማያዊው ቤታችን ላይ በማድረግ በዚያ ልጇ በምገኝበት ሰማያዊ ክብር ላይ አስተንትኖ እንድናደርግ የዛሬው ቀን ስርዓተ አምልኮ ይጋብዘናል።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 09/2011 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በሥጋ እና በነብስ ወደ ሰማይ ያረገችበት የፍልሰታ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት እና እርሳቸው በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን ከስፍራው ለሬዲዮ ቫቲካን ከደረሰው ዜና ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ በእለቱ ስርዓተ አምልኮ በተነበቡት የእግዚኣብሔር ቃላት ላይ ተመርኩዘው ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “የማርያም ደስታ የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 09/2011 ዓ.ም የአውሮፓዊያኒን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የፍልሰታ ማሪያም በዓል አስምልክተው ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደምከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳቺሁ!

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የፍልሰታ በዓል በምናክብርበት በዛሬው ቀን የተነበበልን የቅዱስ ወንጌል ቃል (ሉቃስ 1፡36-56) ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች” (ሉቃስ 1፡46-47) በማለት ትጸልያለች። በእዚህ ጸሎት ውስጥ “ከፍ ከፍ ታደርገዋለች እና ሐሴት” ታደርጋለች የሚሉትን ግሶች እንመልከት። ሐሴት የምናደርገው በሕይወታችን ውስጥ በጣም ውብ የሆነ ነገር ሲከሰት እንዲሁ በውስጣችን ያለውን ደስታ በቀላሉ በመግለጽ ሳይሆን ነገር ግን ነፍሳችንን እና መላው ሰውነታችን ተሳታፊ በሚሆኑበት ሁኔታ በተቀናጀ መልኩ ሐሴት በማድረግ ለመግለጽ እንፈልጋለን። የማርያም ሐሴት የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው። ማን ያውቃል እኛም በሕይወታችን ውስጥ በጌታ ተደስተን ደስታችንን በሐሴት ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ በአንድ ነገር ውጤታማ በምንሆንበት ወቅት ተደስተን ሊሆን ይችላል፣ መልካም የሆነ ዜና ሲያጋጥመን ደስታችንን ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ዛሬ ማርያም በጌታ እንዴት ሐሴት ማደረግ እንደ ሚቻል ታስተምረናለች፣ ምክንያቱም እርሱ “ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልናልና”።

በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙን ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች ደግሞ ታላቅ ነገር ያደረግልንን አካል ከፍ ከፍ እንድናደርግ ያነሳሳናል። በእውነቱ ከፍ ከፍ ማደረግ ማለት ለታላቅነቱን፣ አንድ ታላቅ የሆነን ነገር በእውነቱ ከፍ ማደረግን የሚያመልክት ሲሆን ለታላቅነቱ እና ለውበቱ እውቅና በመስጠት እርሱን ከፍ ከፍ ማደረግ ማለት ነው። ማርያም የጌታን ታላቅነት ከፍ ከፍ ታደርጋለች ፣ በእውነት ታላቅ ነው ብላ አመስግነዋለች። በህይወት ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን መሻት አስፈላጊ ነው ፣ አለበለዚያ ብዙ ትናንሽ ነገሮች እንወሰዳለን። ሕይወታችን ደስተኛ እንዲሆን ከፈለግን፣ በሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ማርያም ታሳየናለች፣ እርሱ ብቻ ታላቅ እንደ ሆነ ታስምረናለች። እነዚህን ታላላቅ የሚባሉ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው ብዙ ጥቅም የማይሰጡ ነገሮችን ለምሳሌም ጭፍን ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ብጥብጥ ፣ ምቀኝነት ፣ ከልክ በላይ በሆነ መልኩ ለቁሳቁሶች ያለንን ፍላጎት . . .  ወዘተ የምንክተልባቸው ብዙ ወቅቶች አሉ። በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ስህተት እንፈጽማለን። ዛሬ ማርያም ጌታ በእርሷ ውስጥ ያከናወናቸውን “ታላላቅ ነገሮች” እንድንመለከት ዛሬ ትጋብዘናለች።

ዛሬ የምናከብራቸው “ታላላቅ ነገሮች” ናቸው። ማርያም ወደ ሰማይ ፈልሳለች፣ ትንሽ እና ትሑት የሆነች ማርያም ከሁሉም በፊት ከፍተኛ ክብርን ተቀበለች። እንደ እኛ ፍጡር የሆነች እርሷ በነፍስ እና በሥጋ ዘላለማዊ ትሆናለች። እናቶች ልጆቻቸው ከሄዱበት ቦታ ወደ ቤት እስኪመለሱ ድረስ እንደ ሚጠብቁ ሁሉ እርሷም እኛን በእዚያ በሰማይ ቤት ሆና ትጠብቀናለች። በእርግጥ የእግዚኣብሔር ሕዝቦች ሁሉ እርሷን “የሰማይ ደጃፍ” እያሉ ነው የሚያወድሱዋት። እኛም ወደ ሰማይ ቤት የምንጓዝ ምጻተኞች ነን። ዛሬ ማርያምን ቀና ብለን ወደ ሰማይ እንመለከታለን፣ በእዚያም የእኛ መዳረሻ የሆነውን ግባችንን እናያለን። አንድ እንደኛ ፍጡር የሆነች ከሙታን ወደ ተነሳው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እንደ ተወሰደች እናያለን፣ ያቺ እንደኛ ፍጡር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳኛችን እናት በመሆን ከጎኑ ትቀመጣለች። በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ አዲሱ አዳም የሆነው ክርስቶስ አዲሲቷ ሔዋን ከሆነችው ማርያም ጋር በጋራ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ እናያቸዋለን፣ እኛም በእዚህ ምድር ምጻተኞች ሆነን በምንኖርበት ጊዜ ለእኛ ታላቅ የሆነ መጽናናትን እና ተስፋን ይሰጠናል።

የማርያምን የፍልሰታ አመታዊ በዓል በምናክብርበት በአሁኑ ወቅት ለሁሉም የሰው ልጆች በተለይም በጥርጣሬ እና በሐዘን ለተሰቃዩ እና ዓይኖቻቸውን ወደ ታች ወደ ምድር አቀርቅረው ለሚገኙ ሰዎች ጥሪ ያቀርባል። ቀና ብለን ክፍት የሆነውን ሰማይ እንመልከት፣ ፍርሃት ሊያድርብን በፍጹም አይገባም፣ በጣም ሩቅ የሆነ ሥፍራም አይደለም፣ ምክንያቱም በሰማይ ደጃፍ ላይ የምትጠብቀን አንድ እናት አለችና። የሰማይ ንግሥት የሆነቺው እርሷ የእኛም እናት ናት። እርሷ ትወደናለች፣ ፈገግታዋንም ታሳየናለች፣ ትንከባከበናለችም። እያንዳንዷ እናት ለልጆቿ የተሻለውን ነገር እንደ ምትፈልግ እና እንደ ምታስብ ሁሉ “በእግዚአብሔር ፊት ውድ ነህና ፣ እናንተ የተፈጠራችሁት ትንንሽ የሆኑ የአለም ነገሮችን ለመፈጸም አይደለም፣ ነገር ግን እናንተ የተፈጠራችሁት ለሰማይ ታላቅ ደስታ ነው” በማለት ተናገረናለች። አዎን! ምክንያቱም እግዚአብሔር አስደሳች ነው እንጂ አሰልቺ አይደለም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጃችንን ይዛ እንድትመራን እንፍቀድላት። በእያንዳንዱ ቀን መቁጠሪያችንን በእጃችን ይዘን የመቁጠሪያ ጸሎት በምናደርግበት ወቅቶች ሁሉ ሕይወታችን ወደ ላይ አንድ እርምጃ እንዲራመድ እናደርጋለን ማለት ነው።

በእውነተኛ ውበት እንማረክ፣ ትናንሽ ወደ ሆኑ ነገሮች አንግባ፣ ነገር ግን የሰማይ ታላቅነትን እንምረጥ። ቅድስት ድንግል እና የሰማይ ደጃፍ የሆነቺው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደስታ እና በመተማመን እውነተኛ የሆነውን የሰማይ ቤታችንን ብቻ በእየለቱ መመልከት እንችል ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን የገባል።

15 August 2019, 12:53