ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከአማዞን ቀደምት ሕዝቦች ጋር በተገናኙበት ወቅት   ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከአማዞን ቀደምት ሕዝቦች ጋር በተገናኙበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በአማዞን ደን ላይ እየተቃጣ ያለው ውድመት መቃወም ያስፈልጋል” አሉ

በላቲን ቋንቋ “Laudato Si” በአማርኛው ውዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በግንቦት 24/2015 ዓ.ም አንድ ሐዋርያዊ መልእክት ይፋ ማደረጋቸው ይታወቃል። በዚህ በላቲን ቋንቋ “Laudato Si” ውዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርእስት ሐዋርያዊ መልእክታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን እንከባከብ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ የዛሬ 4 አመት ገደማ ያፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በዓለማችን ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ መንስሄ ምድራችንን ያለ አግባቡ በመበዝበዛችን፣ ከባቢ አየርን ሊበክሉ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን፣ ጋዞችን ወደ አከባቢ በመልቀቃችን በመሳሰሉ ጉዳዮች የተከሰተ እና የጋራ የመኖርያ ቤታችንን አደጋ ላይ የጣለ ክስተት በመሆኑ ክስተቱን ለመግታት ባለድርሻ አካላት የራስቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል የሚል ጭብጥ ያለው ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ሆነ ይታወሳል።

የእዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ መልእክት ዋና ዓላማ በመደገፍ የተለያዩ የሲቪክ ማሕበራት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ ተመሥርተው በእዚህ ዓላማ ዙሪያ ላይ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን የእዚህ ማኅበር አባላት ደግሞ በእዚህ በላቲን ቋንቋ “Laudato Si” ውዳሴ ለአንተ ይሁን በተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክት ውስጥ የተጠቀሱትን ፍሬ ሐሳቦችን ተቀብለው በተግባር ላይ እያዋሉ የሚገኙ ብዙ ግለሰቦች እና ማኅበራት እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች እና ማኅበራት በግል እና በቡድን በመሆን የአከባቢ ጥበቃ በማደረግ ላይ እንደ ሚገኙ ይታወቃል። በጣሊያን በቁጥር ከስዐር በላይ የሚሆኑ ማኅበራት የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ማኅበራት ማትሪቼ በመባል በምትታወቀው የጣሊያን ግዛት ውስጥ  በሰኔ 29/2011 ዓ.ም ተገናኝተው በማኅበራቸው ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ተገልጹዋል።

በእዚህ ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጹሑፍ መልእክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን ይህንን የቅዱስነታቸውን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

እ.አ.አ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተባት፣ በደረሰው ከፍተኛ ውድመት የተነሳ በርካታ ሰዎች ብዙ ዋጋ በከፈሉባት በመካከለኛው ጣሊያን በምትግገኘው ማትሪቼ በመባል በምትታወቀው ከተማ ውስጥ ለተሰበሰባችሁ “የLaudato Si” (ውዳሴ ለአንተ ይሁን) ማኅበር አባላት ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ። የጋራ በሆነው የመኖሪያ ቤታችን ላይ አውዳሚ በሆነ መልኩ እየተቃጣ ያለውን አደጋ ለማስታወስ እና የተዛባ አጠቃቀም የሚለውን መሪ ቃል መርጣችሁ በአእምሮዬ ውስጥ ሁልጊዜም ተቀርጻ በመትገኘው በማትሪቼ እያደረጋችሁት የምትገኙት ስብሰባ በእዚያ ለሚኖሩ ሕዝቦች ተስፋ የሚያጭር ተግባር ነው። በእዚህ አስጨናቂ እና አሰቃቂ ሁኔታ እና መልሶ የመገንባት ተግባር ድክመት እና መዘግየት በሚታይበት በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አጋርነታችን እና ቅርበታችንን መግለጽ ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅበን ነገር ግን ማነኛው በአከባቢ ላይ የሚደርሰው አደጋ እና ውድመት በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ የሚያደርገው እና ዋጋ የሚያስከፍለው ድሃ የሆነውን የማኅበርሰብ ክፍል እንደ ሆነ በከፍተኛ ደረጃ እና ግልጽ በሆነ መልኩ ለመግለጽ ካለን ፍላጎት የተነሳ ጭምር ነው። በአካባቢያቸው ላይ የተከሰቱት ቁስሎች እራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ እጅግ በጣም ርካሽ በሆነ መንገድ በሰውነት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። ላውዶቶ ሲ (ውዳሴ ለአንተ ይሁን) በሚለው ሐዋርያዊ መልእክቴ ውስጥ “ሰው ራሱ በአዲስ መልክ ተአድሶ ካላደረገ በስተቀር ከተፈጥሮ ጋር ያለንን ግንኙነት በአዲስ መልክ አድሰን መጀመር ካልቻልን ስነ-ምህዳር ሊኖር አይችልም” በማለት ጠቅሼ ነበር። ባለፈው ዓመት ፕላኔታችንን አፍኖ ይዞ ሰለሚገኘው የፕላስቲክ ቆሻሻ ጉዳይ በተመለከተ ከተነጋገርን በኋላ ዛሬ ደግሞ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ስለሆነው እና በመቃብር ጫፍ ላይ ስለሚገኘው ሰለ አማዞን እና ሰለሕዝቦቹ ማሰብ ይገባል። በሚቀጥለው ጥቅምት ወር ይህንን በተመለከተ የብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚደረግ ሲሆን ይህንን ጉዳይ ማቀላጠፍ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ በቅርቡ መሠራቱ ይታወሳል።

በአማዞን ደን ላይ እየተቃጣ ያለው ውድመት በፕላኔታችን ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ መልኩ እየተከሰተ የሚገኝ አሳዛኝ ተግባር ነው፣ ጭፍን የሆነ አስተሳሰብ እና ፍትህ እንዲዛባ የሚያደርግ ተግባር ነው፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያዛምደው ሰንሰለት እየተበጠሰ መሆኑን የሚያሳዩ ተግባሮች ናቸው። እባካችሁን ማህበራዊ ፍትህና ስነ-ምህዳር ጥልቅ የሆነ ትስስር ያላቸው መሆናቸውን አንዘንጋ! በአማዞን ውስጥ እየተከናወነ ያለው ነገር በፕላኔታት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፣ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች በገዛ አገራቸው ውስጥ የባዕድ አገር ዜጎች ሆነዋል፣ የራሳቸውን ባህል እና ልምዶች አጥተዋል፣ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተፈጥሮን በመጠቀም ምድራችንን መንከባከብ ያስፈልጋል። ሰው በዚህ ጥፋት ፊት ለፊት ቆሞ በግድዬለሽነት መንፈስ ተመልካች ሆኖ መቆየት አይችልም፣ የድሆችን የስቃይ ድምጽ መልሶ ማስተጋባት ይኖርብናል።

አምላክን ማመስገን

ከፍጥረታት መልካም ገጽታ በመነሳት እና በተለይም ደግሞ የፍጥረታት ሁሉ የበላይ አለቃ እና ጠባቂ በሆነው በሰው ልጅ መፈጠር የተነሳ ፈጣሪን ማመስገን ተገቢ ነው። በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ እና በአዲስ መልክ በታደሰ መልካም ስሜት እና ልክ እንደ ሕጻናት ዓይኖቻችንን በመክፈት በዙሪያችን ያለውን ውበት እና የሰው ልጅ ፍጥረትን ማድነቅ ይገባናል። ምስጋና የአስተንትኖ ውጤት ነው፣ አስተንትኖ ማድረግ እና ምስጋና ማቅረብ ደግሞ ክብር እንድንሰጥ ያደርጉናል፣ ክብር መስጠት ደግሞ ፍጥረታትን እና የፍጥረታትን ሁሉ ፈጣሪ ለሆነው ከፍተኝ የሆነ ክብር እንድንሰጥ ይገፋፋናል።

ቅዱስ ቁርባን

የቅዱስ ቁርባንን ባሕሪይ መላበስ ደግሞ ዓለምና በዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች እና ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ራስን በስጦታ መልክ በማቅረብ ሁሉንም እንዴት ተሸክሞ መኖር እንደ ሚቻል እንድናውቅ ያደርገናል። ሁሉም ነገር በነፃ ለእኛ ተሰጥቶናል፣ የተሰጠንም እንድንበዘብዝ እና እንድንውጣቸው ሳይሆን ነገር ግን እኛም በተራችን በስጦታ መልክ ለሌልች እንድናካፍል እና ለሁሉም ከሁሉም በላይ የሆነውን የደስታ ስጦታ ምንጭ ይሆን ዘንድ ማደረግ ይኖርብናል።

ምነና

ማንኛውም አይነት አክብሮት የሚጀምረው ጥብቅ ከሆነ ከአንድ መናኝ ባሕሪይ የተቀዳ በሚመስል መልኩ በሚያሳየው ስነ-ስረዓት ሲሆን ይህም ማለት ደግሞ አንድ የተሻለ መልካም ነገር ለማግኘት እና ለሌሎች መልካምነት በማሰብ የራስን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። የምነና ሕይወት ባሕሪይ እኛን ወደ ጥፋት የሚወስደንን ባሕሪይ እንድናስወግድ በማደረግ የተሻሉ ተጨማሪ ነገሮችን እንድንመኝ በማደረግ ካለን እርስ በእርስ እንድንከፋፈል በማነሳሳት ከስነ-ምህዳር ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናጠናክር እና አክብሮትና ትህትና እንዲኖን ያደርጋል።

የሉውዳቶ ሲ (ወዳሴ ለአንተ ይሁን) ማህበረሰቦች ዓለምን ማደስ የሚችል ዘር እንደምትሆኑ፣ ሕይወትን ወደ ፊት ማራመድ እንደምትችሉ፣ የተፈጥሮ ውበት ተጠብቆ እንዲቀጥል እንደ ምታደርጉ፣ በተቀናጀ መልኩ ሁሉም ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ በጋራ ይኖሩ ዘንድ የሚያስችል አዲስ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተል ማኅበርሰብ እንደ ምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።

እጅግ በጣም አመሰግናችኋለሁ፣ ከልብ የመነጨ ቡራኬዬ ይድረሳችሁ። እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ።

06 July 2019, 16:05