ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ. ም. የሩስያውን ፕሬዚደንት ክቡር ቭላድሚር ፑቲን ወደ ቫቲካን በተቀበሉበት ወቅት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ. ም. የሩስያውን ፕሬዚደንት ክቡር ቭላድሚር ፑቲን ወደ ቫቲካን በተቀበሉበት ወቅት፣ 

የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ቫቲካንን የሚጎበኙ መሆኑ ተገለጸ።

ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የሩስያው ፕሬዚደንት ክቡር ቭላድሚር ፑቲን ወደ ቫቲካን መጥተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሊያገኙ እቅድ መያዙን የሞስኮ ከተማ ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳሳት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ ይፋ አድረገዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ እንደገለጹት በግንኙነታቸው ወቅት ቅድሚያ ሰጥተው የሚወያዩባቸው ቀዳሚ ርዕሠ ጉዳዮችም ስለ ሰላም፣ ስለ አካባቢ ጥበቃ እና ቀጣይነት ባለው የጋራ ግንኙነቶች ላይ ይሆናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሞስኮ የወላዲተ አምላክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ አክለው እንደገለጹት ሁለቱ መሪዎች በመጭው ሐሙስ ተገናኝተው ከሚያደርጉት ውይይቶች መልካም ፍሬ እንደሚገኝ ሩስያ ሙሉ ተስፋ አላት ማለታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሮቢን ጎመዝ በላከልን ዘገባ አስታውቋል።

ውይይት፣ ሰላም እና የጋራ መኖሪያችን፣

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ፣ ለቫቲካን ሬዲዮ ጣሊያንኛ ቋንቋ ክፍል እንዳስታወቁት የሁለቱ መሪዎች የውይይት አጀንዳ በውል ባይታወቅም፣ በእራሳቸው ግምት፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅግ አንገብጋቢ የሆኑ ወቅታዊ ርዕሠ ጉዳዮች ሰላም እና የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ስለ መንከባከብ እና መጠበቅ የሚሉ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በቫቲካን ውስጥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲ መካከል የሚደረግ ወይይት ለሦስተኛ ጊዜ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል። የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን ያደረጉት ሕዳር 16 ቀን 2006 ዓ. ም. ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማለትም ሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል። ቅድስት መንበር እና የሩስያ ፌዴሬሽን ተመልሰው የጋራ ግንኙነታቸውን ያደሱት በ1982 ዓ. ም. ሲሆን ቀጥለውም ግንኙነታቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማድረስ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የመሠረቱት በ2001 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል።

ሩስያ ለዓለም ሰላም ልታበረክት የምትችለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ ይህ ደግሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሕዝቦች ሰላም ዘወትር ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙበት ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። ስለሆነም መላዋ ቤተክርስቲያን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በቭላድሚር ፑቲን መካከል፣ ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሚደረገው ውይይት ይገኛል ብላ ተስፋ የምታደርገው፣ በሁለቱ መሪዎች ወይም መንግሥታት መካከል ቀጣይነት ያለው ገንቢ የውይይት ሂደት ነው ብለዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የውይይት መንገድ አስተያየታቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ፣ ቅዱስነታቸው በቅድሚያ የሌሎች ሰዎች ንግግር ለማዳመጥ የተዘጋጁ፣ ከሌሎች የሚቀርብላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚፈልጉ፣ ብዙ ከመናረግ ይልቅ ልብን በሚነኩ ጥቂት ቃላት ለማግባባት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሩስያን ይጎበኙ ይሆን?

የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ቫቲካን በሚያደርጉት ባሁኑ ጉብኝታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሩስያን እንዲጎበኙ ግብዣን ያቀርቡ ይሆናል የሚል ግምት በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዳለ የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ፣ በዚህ እጠራጠራለሁ ብለው፣ ምንም እንኳን ከመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን በኩል ግብዣ ሊቀርብ ቢችልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በእንግድነት ተቀብሎ የሚያስተናግደው ከፍተኛ የቤተክርስቲያን አመራር እንደሚሆን ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ አስረድተው ለጊዜው ከሩስያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በኩል የታየ ነገር የለም ካሉ በኋላ የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑትን ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር ሳይወያዩ በግል ተነሳሽነት ብቻ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሩስያን እንዲጎበኙ በማለት የግብዣ ጥሪን አያቀርቡም ብለዋል።

የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት፣

ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲ መካከል የሚደረግ ወይይት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያሻሽል ይችላል ተብሏል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲ መካከል የሚደረግ የዛሬው ወይይት ቅዱስነታቸው ከሩስያው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ፣ ከብጹዕ ወ ቅዱስ ኪሪል ጋር በ2008 ዓ. ም. ከተገናኙበት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል። በወቅቱ ታሪካዊ ግንኙነት የተባለለት ሲሆን በምስራቅ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እና በምዕራብ ካቶሊካዊ እምነት ተከታዮች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ በር መከፈቱ ተነግሯል።

የተባበሩት ሶቭዬት ሕብረት የመጨረሻው መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ እና የአሁኗ ሶቪዬት የመጀመሪያ መሪ የነበሩት ቦሪስ ዬልሲን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሩስያን እንዲጎበኙ መጋበዛቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ሩስያን ባይሆን በቁጥር በርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ምመናን ወደሚገኙባቸው አገሮች ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።                      

02 July 2019, 18:51