ፈልግ

የቪንሴንት ወላጆች፤ የቪንሴንት ወላጆች፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ደጋፊ ለሌላቸው እና የአልጋ ቁራኛ ለሆኑት አረጋዊያን እንጸልይ ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ሐምሌ 3/2011 ዓ. ም. በዘጠኝ ቋንቋዎች ባስተላለፉት የቲዊተር ማሕበራዊ መገናኛ መልዕክታቸው እንዳሳሰቡት ዳግፊ አጥተው በሕመም ላይ ለሚገኙት አረጋዊያን እንድንጸልይላቸው አሳስበውል። ሕይወትን ከፈጣሪው ያገኘ እና  ሰብዓዊ ክብርን በሚገባ የተገነዘበ አንድ ማሕበረሰብ የሰው ነፍስ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለ ምንም ማዳላት መንከባክብ ይኖርበታል። የሕክምና ባለሞያዎችም ቢሆኑ ከፈጣሪው በተሰጣቸው እውቀት በመታገዝ የሰውን ልጅ ሕይወት በመንከባከብ እና አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ለማቆየት መጠራታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ይፋ የሆነው በፈረንሳይ አገር፣ ከ2000 ዓ. ም. ጀምሮ ከደረሰበት ከባድ የመኪና አደጋ ለመፈወስ ሕክምናን ሲከታተል ለቆየው አንድ ታካሚ ከሕኪሞች በኩል ይቀርብለት የነበረው አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ፣ የሚበላ እና የሚጠጣ በመከልከል ለሞት በተቃረበበት ወቅት መሆኑ ታውቋል።

ፈረንሳይ የተባበሩት መንግሥታት ጥያቄን አትቀበለውም፣

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መብትን በማጤን የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት ያቀረበውን የስድስት ወር ጊዜ የዕድሜ ማራዘም ጥያቄን የፈረንሳይ መንግሥት ችላ ማለቱ ታውቋል። የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መብትን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸደቀውን ስምምነት የፈረንሳይ መንግሥት የተቀበለው ቢሆንም በአንቀጽ 25 የተቀመጠውን ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ የለብኝም በማለት የፈረንሳይ መንግሥት አስታውቋል።

ሕመም ለሚያስከትለው ስቃይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣

በመኪና አደጋ የአካል ጉዳት የደረሰበት እና በፈረንሳይ አገር ሕክምናውን በመከታተል ላይ የሚገኝ የቪንሴንት ወላጆች ሐኪሞች ልጃቸውን ለሞት ዳርገውታል በማለት ክስ መመስረታቸው ታውቋል። በዘመናዊ የሕክምና አሰጣጥ ሕይወትን ለሞት መዳረግ ወላጅ እናትን ኣና አባትን ምን ያህል እንደሚያሰቃይ፣ ከዚህም አልፎ ተርፎ አላስፈላጊ የሆኑ የቃላት ልውውጥን ወደ ጎን በማድረግ፣ ሕመም ለሚያስከትለው ስቃይ ትኩረት መስጠት የሚገባ መሆኑ ተገልጿል።

የንቀት ባሕልን መዋጋት ያስፈልጋል፣

ከደረሰበት የመኪና አደጋ ለማገገም ሕክምናን በመከታተል ላይ ለሚገኝ ቪንሴንት የፈረንሳይ ሕኪሞች ካለፈው ከግንቦት 12 ቀን ጀምሮ ምግብ እና ውሃን ማቅረብ ለማቋረጥ የወሰኑ ቢወስኑም ከፍርድ ቤት በቀረበው ይግባኝ መሠረት ውሳኔአቸው ውድቅ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲውተር ማሕበራዊ መውገናኛ በኩል በላኩት መልዕክታቸው ደጋፊን በማጣት የአልጋ ቁራኛ ሆነው በስቃይ ላይ ለሚገኙት በሙሉ እንድንጸልይ ማሳሰባቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የእግዚአብሔር በረከት የሆነውን ነፍስ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻ መንከባከብ ያስፈልጋል ብለው ሰዎች አንዱን ከሌላው አሳንሶ የመመልከት ወይም የመናቅ ባሕልን መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የእያንዳንዱ ሕመምተኛ ሕይወት በከፍተኛ አክብሮት ሊታገዝ ይገባል፣

በፈረንሳይ አገር ሕክምናውን በመከታተል ላይ የሚገኝ ወጣት ቪንሴንትን በማስታወስ ያለፈው ዓመት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለት ስሞታዎችን ማቅረባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዚህን ወቅት በእንግሊዝ አገር በከባድ ሕመም ላይ የሚገኘውን ሕጻን አልፌይ ኢቫንን ማስታወሳቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሬጂና ቼሊ ማረሚያ ቤት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በፈረንሳይ እና በእንግሊዝ አገር በከባድ ሕመም ላይ የሚገኙትን ቪንሴንት ላምበርትን፣ ሕጻኑን አልፌይ ኢቫንን እና ሌሎችን በከባድ ሕመም በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን በሙሉ በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ማለታቸው ይታወሳል። እነዚህ ሕመምተኞች የሚገኙበት ሁኔታ አስጊ እና ከባድ ስቃይ ያለበት መሆኑን አሳስበው ከወላጆቻቸው እና ከሕክምና ባለሞያዎች ተገቢው ሰብዓዊ ክብር እንዲሰጣቸው አሳስበው በጸሎታችንም እንድናግዛቸው አደራ ማለታቸው ይታወሳል።

እግዚአብሔር የሕይወታችን ብቸኛ ባለቤት ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 10/2010 ዓ. ም. ባቀረቡት የዕሮብ ዕለት ጠቅላላ አስተምሮአቸው፣ በሕክምና ላይ የሚገኙትን ወጣት ቪንሴንት ላምቤርትን እና ሕጻን አልፌይ ኢቫንን በማስታወስ ባቀረቡት አቤቱታ የሕይወታችን ብቸኛ ባለቤት እግዚአብሔር መሆኑን አስረድተው ግዴታችንም የእግዚአብሔር ስጦታ ሆነው ነፍሳችን ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ አስፈላጊውን እንክብካቤን መስጠት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የሰዎች ሽንፈት፣

የቀደሙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መንገድ የተከተሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር በሚያስተላልፉት ግልጽ መልዕክታቸው፣ በሕይወት መጨረሻ ሰዓት ላይ የሚገኙት ሕሙማን በሐኪሞች በመታገዝ በፈቃዳቸው የሚቀበሉት የሕይወት ፍጻሜ የሰውን ልጆች ሽንፈት ያመለክታል ብለው ከእግዚአብሔር የቀረበልን ጥሪ በከባድ ሕመም ላይ ሆነው የሚሰቃዩትን ለሞት እንዲበቁ ማድረግ ወይም ማገዝ ሳይሆን ተስፋን በመስጠት እስከ ሕይወት ፍጻሜ ሰዓት ድረስ እንክብካቤን መስጠት መሆኑን በመልዕክታቸው አሳስበዋል።      

ቅድስት መንበር: የታመመን ሰው መመገብ እና ማጠጣት መዘንጋት የሌለበት ግዴታ ነው፣

በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት የብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ እና በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል በመልዕክታቸው፣ በሰብዓዊ መብት ላይ የምንፈጽመው ትልቁ የመብት ጥሰት ምግብን እና ውሃን መከልከል እንደሆነ አስገንዝበው በተለይም የታመመን መመገብ እና ማጠጣት ከሕክምና አገልግሎቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል። የሕመም ስቃይን ካልጨመረ ወይም ሌላ እክል ካልፈጠረ በቀር የሕይወት ማቆያ መንገድ ነው ብለው ይህ በመሆኑ የሕክምና ማዕከላት የታመመን መመገብ እና ማጠጣት መዘንጋት የሌለባቸው ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል።   

11 July 2019, 15:54