ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉባኤ ላይ፣  2019.04.11 ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉባኤ ላይ፣ 2019.04.11 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “ለሴተኛ አዳሪነት ሕይወት የተዳረጉ ሴቶችን ነጻ ማውጣት ይገባል”።

በኢጣሊያ ውስጥ፣ ሪሚኒ ከተማ የሚገኘውን እና ለሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ተዳርገው የነበሩ ሴቶች ተመልሰው እንዲቋቋሙ የሚደረግበትን፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ማዕከልን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሴተኛ አዳሪነት ሕይወት የተዳረጉ እህቶቻችንን ነጻ ማውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል። የሴተኛ አዳሪነትን ሕይወት አስከፊነት ለሚያብራራ እና “ለስቅላት የተዳረጉ ሴቶች” በሚል አርዕስት አዲስ በታተመው መጽሐፍ የቅዱስነታቸው መልዕክት መካተቱ ታውቋል።     

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢጣሊያ ውስጥ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ግብኝቶችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሪሚኒ ከተማ የሚገኘውን እና ለሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ተዳርገው የነበሩ ሴቶች የሚገኙበትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ማዕከልን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በማዕከሉ ውስጥ ሆነው በማገገም ላይ ከሚገኙ ሴቶች አንደበት የሰሙት ያለፈ ታሪክ በእርግጥም “ለስቅላት የተዳረጉበት ሕይወት” ነው በማለት ገልጸውታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የማዕከሉ ነዋሪ ሴቶች ታሪክ ካዳመጡ በኋላ በእነዚህ ሴት እህቶቻችን የተለያዩ ስቃዮችን ላደረሱባቸው በደለኞች ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን መለመን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሕይወት ማዳን እና መልሶ የማቋቋም ሥራ፣

ክቡር አባ አልዶ ቦንአዩቶ በርካታ ዓመታትን ወስደው በጻፉት አዲስ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት፣ በሴተኛ አዳሪነት አስከፊ ሕይወት የተጎዱ ሴት እህቶቻችንን ሕይወት ማዳን እና መልሶ ማቋቋም  እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማሳሰቢያቸው የሴተኛ አዳሪነት ሕይወትን አደገኛነት ሲያስረዱ “ሕገ-ወጥ እና የአሳፋሪ ትርፍ ምንጭ” የወንጀል ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ አዲስ የታተመው በብዙዎች እጅ ገብቶ ለንባብ እንደሚበቃ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ አስከፊ እና ስቃይ የበዛበት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንዲገታ ከተፈለገ በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በስተጀርባ ያለው ታሪክ በስፋት መነገር አለበት ብለዋል።

ሴተኛ አዳሪነት እና ባርነት፣

“ሙስና ብቻውን ሊገታ ማይችል በሽታ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አስከፊነቱን በቤተክርስቲያን ውስጥ በግልም ሆነ በጋራ፣ ልዩ ልዩ ግንዛቤዎችን በመስጠት መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል። መልዕክታቸውን በመቀጠል “ማንኛውም ዓይነት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያሳንስ የወንጀል ድርጊት ፣ ራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለስቃይ የሚዳርግ አስጸያፊ ድርጊት ነው” ብለው ሴተኛ አዳሪነት በጠቅላላው ሴቶች ከስብዕናቸው ወጥተው ወደ ዕቃነት እንዲለወጡ የሚያደርግ ተግባር እንደሆነ ገልጸው ሃሳቡ በማሕበረሰብ ዘንድ መግባቱ በራሱ፣ ማሕበረሰቡ የተሳሳተ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። ሴት እህቶቻችንን ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ነጻ ማውጣት የሁሉም ሰው ሃላፊነት የሆነ የምሕረት መገለጫ ነው ብለዋል። በመሆኑም ማሕበራትም ሆነ ግለሰቦች የእነዚህን እህቶቻችን የስቃይ ጩኸት እየሰሙ ችላ ማለት እንደማይገባ አሳስበው፣ በዓለማችን እየፈሰሰ ካለው ደም እጁን ታጥቦ ነጻ መሆን የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 July 2019, 17:05