ፈልግ

የኡጋንዳ ምዕመናን በሕዳር ወር 2008 ዓ. ም. ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አቀባበል ባደረጉበት ወቅት፤ የኡጋንዳ ምዕመናን በሕዳር ወር 2008 ዓ. ም. ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አቀባበል ባደረጉበት ወቅት፤ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአፍሪቃ ጳጳሳት የወንጌል ተልዕኮዋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አሳሰቡ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ ጉባኤያቸውን በማከናወን ላይ ለሚገኙት፣ የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት በላኩት መልዕክት የአፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት የወንጌል  ተልዕኮዋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማሳሰባቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተሳታፊዎች የላኩት የሰላምታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ሲነበብ የተደመጠው ትናንት እሁድ ሐምሌ 14/2011 ዓ. ም. በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ በሚገኘው የልቤ ኢየሱስ ካቴድራል ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ተቀብለው የላኩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መሆናቸው ታውቋል።  ቅዱስነታቸው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩን ክብረ በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡት የጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክታቸው፣ የአንድነት ጉባኤው ከእግዚአብሔር ዘንድ ለተቀበሏቸው ጸጋዎች በሙሉ እንዲሁም በእርሱ ስም ለ50 ዓመታት በወንድማማችነት መንፈስ አገልግሎትን እንዲያበረክቱ ላስቻላው እግዚአብሔር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እንዳስታወቁት ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ላይ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሆኑት በሙሉ ከእግዚአብሔር በሚያገኙት ሃይል በመታገዝ ሐዋርያት ያከናውኑትን የወንጌል አገልግሎት በጊዜያችንም ለሌሎች በማዳረስ ቀጣይነት እንዲኖረው በጸሎታቸው ማስታወሳቸውን ገልጸዋል። ይህን በማከናወን የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የአፍሪቃን ቤተክርስቲያን ማገዝ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው ማሳሰባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን የላኩ ሲሆን የቤተክርስቲያን እናት የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛን በጸሎታቸው ተማጽነው የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም እና ደስታ እንዲበዛላቸው መመኘታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።     

22 July 2019, 16:40