ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የቤተክርስቲያን ተልእኮ ቅዱስ ወንጌል ማወጅ እና መመስከር ነው” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካና በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 30/3011 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል (10፡1-12, 17-20) ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ ሰባ ሁለቱን ሐዋርያት ሁለት ሁለት አድርጎ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት። እንግዲህ ሂዱ፤ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ኰረጆ ወይም ከረጢት፣ ወይም ጫማ አትያዙ፤ በመንገድ ላይም ለማንም ሰላምታ አትስጡ” ብሎ በተናገረው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ከእግዚኣብሔር ጋር አብሮ በመጓዝ ብቻ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 30/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ያሰሙትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 10፡1-12, 17-20) ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዐስራ ሁለቱ ደቀ-መዛሙርት ባሻገር ተጨማሪ 72 ሐዋሪያቱን ሲልክ እናያለን። ሰባው ሁለት ቁጥር ምን አልባት ሁሉንም አገራት የሚወክል ቁጥር ሊሆን ይችላል። በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ 72 ቁጥር በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን 72 የተለያዩ አገራትን እንደ ሚወክል ይገልጻል (ኦዘፍ. 10፡1-32)። ስለዚህ ይህ አገላለጽ የቤተክርስቲያን ዋነኛው ተልዕኮ ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ የማዳረስ ተልዕኮ እንዳለባት ያሳያል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን በላከበት ወቅት ““መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት!” (ሉቃ 10፡2)።

ይህ የኢየሱስ ጥያቄ ሁልጊዜ ተቀባይነት ያለው ነው።  “የመከሩ ባለቤት” እግዚአብሔር ሲሆን የእርሱ የመከሩ ሥፍራ ወደ ሆነ ወደ ዓለም ሠራተኞቹን ይልክ ዘንድ ሁልጊዜ መጸለይ ይኖርብናል። እያንዳንዳችን በተከፈተ ልብ እና ሚስዮናዊ በሆነ መንፈስ ልንጸልይ ይገባል፣ ጸሎታችን ለእራሳችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ብቻ ለመጠየቅ ማዋል የለብንም፣ ነገር ግን ለሁላችን ለጋራ ፍላጎቶቻችን መጸለይ ይገባናል፣ አንድ ጸሎት ትክከለኛ የክርስቲያን ጸሎት ነው የሚባለው ሁሉን አቀፍ ጸሎት ሲሆን ብቻ ነው።

ኢየሱስ 72ቱን ሐዋርያት በላካቸው ወቅት ተልእኮውን የሚገልጽ ትክክለኛ መመሪያዎችን ይሰጣቸዋል። የመጀመሪያው “ሂዱ” የሚለው ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ጸልዩ” የሚለው ነው፣ ከእዚያን በመቀጠል ደግሞ “በእጃችሁ ኰረጆ ወይም ከረጢት” . . . ወዘተ አትያዙ፣ “ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ አስቀድማችሁ፣ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ” . . .  ወዘተ፤ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ፣ በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው፣ ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ. . .  ከእዚያም ከተማውን ለቃችሁ ሂዱ” በማለት ይልካቸዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች ተልዕኳው ጸሎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንደ ሚገባ ያሳያል፣ ተጨባጭ ሊሆን ይገባዋል፣ ተጓዥ የሆነ ተልዕኮ ሊሆን የገባዋል፣ ከነገሮች ጋር ያለንን ቁርኝት ማስወገድ እና በድህነት መንፈስ የሚደረግ ተልዕኮ እና የእግዚኣብሔር መንግሥት መቅረቡን በሚያመለክት መልኩ ፈውስን በማምጣት ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንዲቀይሩ ማስገደድ ሳይሆን የእግዚኣብሔርን ቃል በትህትና በመመስከር እና በማወጅ ሊከናወን የሚገባው ተልዕኮ ነው፣ በተጨማሪም ይህ ግልጽነትና ወንጌላዊ ነጻነት እንዲወጣ በማድረግ የደህንነትን ምንጭ የሆነውን ቃል በእርግማን እና በማውገዝ ሳይሆን ያለእንቢታ በኃላፊነት ይቀበሉ ዘንድ ማደረግን ያጠቃልላል።

በእዚህ አኳን የሚደረግ ተልዕኮ ቤተክርስቲያን በደስታ የተሞላች እንድትሆን ያደርጋታል። ይህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል የተጠናቀቀው በምን ሁኔታ ነበር? “ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመለሱ” በማለት ነበር። ይህ ከተልዕኮ ስኬት የመነጨ ጊዜያዊ የሆነ ደስታ አይደለም፣ በተቃራኒው “ስማችሁ ግን በመንግሥተ ሰማይ ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ” በማለት ኢየሱስ በተናገራቸው የተስፋ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ደስታ ነው። በዚህ አገላለጽ ውስጥ ውስጣዊ ደስታን እና የእርሱ ልጅ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል በእግዚአብሔር መጠራታችንን በመገንዘባቸው የሚገኘውን ነቀፋ የሌለበት ደስታ ነው። የእርሱ ደቀ መዝሙር በመሆናችን ብቻ የሚገኝ ደስታ ነው። ለምሳሌ ዛሬ በእዚህ አደባባይ ላይ የተሰበሰብን እያንዳንዳችን ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት የተሰጠንን የመጠሪያ ሥም ማሰብ እንችላለን፣ ያ መጠሪያ ሥም "በላይ በሰማይ” በሚገኘው በእግዚአብሔር አብ ልብ ውስጥ ተጽፎ የገኛል። እናም የእያንዳንዱን ደቀመዝሙር ሚስዮናዊ፣ ከጌታ ኢየሱስ ጋር የሚራመድ፣ ጌታ ለራሱ ሳይሰስት ራሱን በሙሉ ለሌሎች አሳልፎ እንደ ሰጠ ሁሉ ከእዚህ ሁኔታ በመማር ራሱን በሙሉ ለሌሎች ለመስጠት የተዘጋጀ፣ ከራሱ እና እርሱ ካለው ሐብት ንብረት ጋር ያለውን ቁርኝት መስበር ለቻሉ ሰዎች ሁሉ የሚሰጥ ነጻ የደስታ ስጦታ ነው።

ሁላችንም በቅድሚያ የክርስቶስ ደቀመዛሙርትን ተልዕኮ በሁሉም ስፍራ በተሳካ መልኩ ይከናወን ዘንድ፣ እያንዳንዳችንን እግዚአብሔር እንደሚወደን፣ እኛን እንደሚያድነን እና የእርሱ መንግሥት ተካፋዮች እንድንሆን እንደ ሚፈልግ እንድናውጅ የተሰጠን ተልዕኮ በተገቢው ሁኔታ ማከናወን እንችል ዘንድ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጥበቃ እና ድጋፍ እንማጸናለን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
07 July 2019, 17:09