ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “`አባታችን ሆይ” የሚለው ጸሎት ሁሉንም ጸሎቶች በውስጡ አካቶ የያዘ ነው”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌለ አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት በሐምሌ 21/2011 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 11፡1-13 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ ደቀ-መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባቸው ባስተማረው ጸሎት ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ ለቫቲካን ኒውስ ከደረሰው ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “`አባታችን ሆይ!` የሚለው ጸሎት ሁሉንም ጸሎቶች በውስጡ አካቶ የያዘ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 11፡1-13) ኢየሱስ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንዳስተማረ ቅዱስ ሉቃስ ይተርክልናል። እነርሱ ማለትም ደቀ-መዛሙርቱ የአይሁድን ወግ በጠበቀ መልኩ እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባቸው ቀድሞውኑ ያውቁ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ኢየሱስ ይጸልየው የነበረው ዓይነት “ጥራት” ያለው ጸሎት ለመጸለይ ጉጉት ስለነበራቸው ጸሎት መጸለይ እንዲያስተምራቸው ይጠይቁታል። ምክንያቱም ጸሎት በጌታቸው ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር መሆኑን ማየት በመቻላቸው የተነሳ ሲሆን በእውነቱ እርሱ  በጣም ወሳኝ የሚባሉ ተግባራትን ከመፈጸሙ በፊት ረዣዥም ጸሎቶችን ለማድረግ ብቻውን ገለል ወዳለ ሥፍራ እንደ ሚሄድ ስለሚያውቁ ጭምር ነው። በተጨማሪም ፣ እርሱ በወቅቱ እንደ ነበሩት ጌቶች ሳይሆን የሚጸልየው፣ ነገር ግን ጸሎቱን በሚያደርግበት ወቅት ከአብ ጋር ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት በመፍጠር እንደ ነበረ ጭምር በማየታቸው እና እነርሱም ቢሆኑ በእዚህ ዓይነት ሁኔታ ከእግዚኣብሔር ጋር ቁርኝት በመፍጠር ጣዕም ያለው ጸሎት መጸለይ ይችሉ ዘንድ ኢየሱስ የሚጸልየው ዓይነት ጸሎት ለመጸለይ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው።

ስለዚህ አንድ ቀን ኢየሱስ ገለልተኛ ቦታ ላይ ሆኖ ስያደገው የነበረውን ጸሎት አጠናቆ በሚመለስበት ወቅት “ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረን” በማለት ጠየቁት። የደቀ መዛሙርቱን ግልፅ የሆነ ጥያቄ በሚመልስበት ወቅት ኢየሱስ ጸሎቱን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መግለጫ አልሰጠም ነበር፣ እንዲሁም አንድ ነገር “ለማግኘት” እና ውጤታማ ለመሆን በሚያስችላቸው መልኩ የተቃኘ የአጸላለይ ዘዴ አላስተማራቸውም ነበር። ይልቁንም ተከታዮቹ ከእርሱ ጋር በመሆን ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር ከእግዚኣብሔር ጋር ግላዊ የሆነ ግንኙነት ፈጥረው ሐሳባቸውን በቀጥታ ከእርሱ ጋር መለዋወጥ ይችሉ ዘንድ ምኞት እንዲያድርባቸው ማደረግ የሚችል ጸሎት እንዲለማመዱ ይጋብዛቸዋል። በእዚህ ውስጥ በክርስቲያን ጸሎት ውስጥ አንድ አዲስ ነገር ይከሰታል! ይህም እርስ በርስ በሚዋደዱ ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት ነው ፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ውይይት ፣ በማዳመጥ የተደገፈ እና አንድነትን ለመፍጠር ክፍት የሆነ ጸሎት ነው። ልጅ ከአባቱ ጋር ውይይት የሚያደርግበት፣ በልጆች እና በአባት መካከል የሚደረግ ውይይት ነው። ይህ የክርስቲያን ጸሎት ነው።

ስለዚህ መለኮታዊው ጌታ በምድር ላይ በነበረው ተልእኮ ለእነርሱ “አባታችን ሆይ!” የተሰኘውን እጅግ ክቡር የሆነውን ጸሎት ይሰጣቸዋል። እርሱ የአብ ልጅ መሆኑን እና የእኛም ወንድም መሆኑን  የሚገልጸውን ምስጢር ከገለጠ በኋላ፣ በዚህ ጸሎት ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር እንድንገባ ያደርገናል፣ በእዚህ ላይ አጽኖት መስጠት እፈልጋለሁ፣ ኢየሱስ “አባታችን ሆይ!” የሚለውን ጸሎት በሚያስተምረን ወቅት እግዚአብሔር አባት መሆኑን ወደ ሚገልጽ መንፈስ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል፣ እንዲሁም ከታች ወደ ላይ በቀጥታ ከእርሱ ጋር በመገናኘት አባት እና ልጅ በመተማመን መንፈስ የሚያደርጉትን ዓይነት ውይይት ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ያሳየናል። አንድ አባት ከልጁ ጋር፣ አንድ ልጅ ደግሞ ከአባቱ ጋር የሚያደርገውን ዓይነት ጸሎት እንድናደርግ ይጋብዘናል። “አባታችን ሆይ!” በተሰኘው ጸሎት ውስጥ  የምንማጸናቸው ነገሮች ማለትም ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፣ የእለት እንጀራችንን ስጠን፣ ይቅር በለን እና ከክፉ ነገር ሁሉ አድነን ብለን የምንማጸናቸው ነገሮች ሁሉ በአንድያ ልጁ መምጣት እውን የሆኑ ነገሮች ናቸው። እነዚህን ነገሮች የምንጠይቃቸው ደግሞ እጆቻችንን ዘርግተን ነው። አብ በወልድ ያሳየንን ስጦታዎች ለመቀበል እጃችንን እንዘረጋለን። ጌታ ያስተማረን ጸሎት እያንዳንዱን ጸሎት አጠቃሎ የያዘ ጸሎት ነው፣ እናም ከወንድሞቻችን ጋር በመተባበር ወደ አባታችን ልንጸልየው የሚገባን ጸሎት ነው። አንዳንድ ጊዜ ጸሎት በምናደርግባቸው ወቅቶች ውስጥ የትኩረት ማነስ ስሜቶች የሚከሰቱ ሲሆን ብዙ ጊዜ “አባት” በሚለው የመጀመሪያ ቃል ላይ ቆም በማለት ትኩረት የመስጠት ፍላጎት እናሳያለን፣ በልባችን ውስጥ ሳይቀር ያ የአባትነት ፍላጎት ይሰማናል።

ከእዚያም በመቀጠል አንድ በመከራ ውስጥ የሚገኝ ሰው በጸሎት ደጋግሞ መጠየቅ እንደ ሚገባው ኢየሱስ ያሳስባል። ልጆች ከሶስት እስከ ሶስት ዓመት ተኩል እድሜ ሲሞላቸው ምን እንደሚያደርጉ ትዝ ይለኛል፣ የማይገባቸውን ነገር መጠየቅ ይጀምራሉ። የእዚህ ዓይነቱ ተግባር ደግሞ እኔ በመጣሁበት ባሕል ውስጥ፣ ተስፋ አደርጋለሁ በእናንተም ባሕል ውስጥ ሳይቀር “ለምን ተብሎ የሚጠይቅበት እድሜ” በመባል ይታወቃል። ልጆች አባታቸውን በሚመለከቱበት ወቅት “አብዬ ለምን? እንዴት? . . . ወዘተ” በማለት ለነገሮች ማብራሪያ ይሰጣቸው ዘንድ ይጠይቃሉ። እዚህ ጋር ጥንቃቄ ማደረግ ይገባናል፣ አባት ለቀረበለት ጥያቄ ማብራሪያ መስጠት ሲጀምር፣ አጠቃላይ ማብራሪያውን በሚገባ ሰምተው ሳይጨርሱ ሌላ ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራሉ። እዚህ ጋር ምን ይከሰታል? ሕጻናት ነገሮችን በገሚስ መስማት እና መረዳት ሲጀምሩ በነገሮች ላይ እርግጠኞች መሆን አይችሉም። የአባታቸውን ትኩረት ብቻ ለመሳብ በማሰብ “ለምን እንዲህ ሆነ” በማለት ይጠይቃሉ። እኛ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ በሚገኘው “አባታችን” በሚለው የመጀመሪያ ቃል ላይ ቆም ብለን  ሕፃናት በነበርንበት ወቅት እኛም የአባታችን እይታ በእኛ ላይ ይሆን ዘንድ በማሰብ በመማጸን እንጀምራለን። “አባታችን” ማለት በራሱ “ለምን” እንደ ማለት የሚቆጠር ሲሆን በእዚህ መልኩ ደግሞ አባታችን ወደ እኛ ይመለከታል።

“አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ከኢየሱስ ጋር ሕብረት በመፍጠር እና በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን መጸለይ እንችል ዘንድ እንድትረዳን ጸሎተኛ የሆነችውን የእናታችንን የእመቤታችን ቅድስት ማርያምን አማላጅነት መማጸን የገባናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 July 2019, 16:16