ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በክርስትና ሕይወት ማደግ፣ ለወንጌል ምስክርነት ራስን ማዘጋጀት እና ለዚህም የማይታጠፍ ውሳኔን ማድረግ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትናንት እሁድ ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖአቸውን አቅርበዋል። በዚህ አስተንትኖአቸውም ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈቃድ እያከናወነች በመጓዝ ላይ የምትገኝ፣ ማንኛውንም ዓይነት የጊዜውን ሁኔታ በፍጥነት በመገንዘብ ምላሽ ለመስጠት የወሰነች ናት ብለዋል። የአስተንትኖአቸው መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው፣ በምዕ. 9. 51-62 ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገውን ረጅም ጉዞ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ መንፈሳዊነትን የተላበሰ ስነ መለኮታዊና የመሲሁ ተልእኮ ፍጻሜን ይተርክልናል። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ውሳኔ እጅግ ጠንካራ እና እርሱንም የሚከተሉት የውሳኔውን ጥንካሬ ከራሳቸው አካሄድ ጋር እንዲያገናዝቡ የተጠኣሩበት ነው። ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስም በዚህ የወንጌል ክፍል ሦስት ዋና ዋና ገጠመኞችን፣ ወይም ኢየሱስ ክርስቶስን እስከ መጨረሻ መከተል የሚፈልጉት ከልብ እንዲያውቁት የሚገባውን ሦስት የጥሪ ዓይነቶችን  ይናገረናል።

የመጀመሪያው ጥሪ፣ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9 ቁጥር 57 ላይ እንደተገለጸው፣ አንድ ሰው ኢየሱስን “ጌታ ሆይ እኔ ወደምትሄድበት ሁሉ ልከተልህ እፈልጋለሁ” የሚል ነው። ይህን ያለው ሰው ቸር እና የዋህ ነው። ነገር ግን ኢየሱስም መልሶ “ቀበሮዎች ጉድጓድ አላቸው። ወፎችም ጎጆ አላቸው። የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ አስጠግቶ የሚያሳርፍበት ስፍራ የለውም” ሲል መለሰለት” (የሉቃ. 9 ቁጥር 58)። ከኢየሱስ ክርስቶስ መልስ የምንማረው፣ ስለ አባቱ መንግሥት ገናናነት በከንቱ ለጠፉት እና ለሚጠፉት የእግዚአብሔር መንጋዎች ለመመስከር ብሎ በተነሳበት ወቅት ማንኛውንም ዓይነት ሌላ መመኪያ እና ከለላ፣ መኖሪያ ቤቱንም ጭምር በመተው ቆርጦ መነሳቱን ነው። በዚህ አቋሙ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለሆንን በሙሉ፣ በዚህ ዓለም ላይ በገሃድ እንድንመሰክር የተሰጠን ተልዕኮ በአንድ ስፍራ ቆሞ የሚቀር ሳይሆን ዘላቂነት ያለው መሆን እንዳለበት ያስታውሰናል። ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በሚያገኘው ሃይል እና ብርታት በዕለታዊ ሕይወቱ ውስጥ ለውጥን የሚያሳይ መሆን አለበት። በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያንም ብትሆን እርሷን በመሠረታት በኢየሱስ ክርስቶስ ዕቅድ መሠረት እንቅስቃሴ ላይ የምትገኝ መሆን አለባት። የተጠራችውም ወንጌልን ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ እንድታዳርስ ነው። ይህም ወንጌላዊው  ሉቃስ በጽሑፉ የገልጸው የመጀመሪያው ዓይነት ጥሪ ነው።

ሁለተኛው የጥሪ ዓይነት በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 9 ቁጥር 59 ላይ እንደተገለጸው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላቀረበለት ጥሪ አንድ ሰው የሰጠው ምላሽ ነው። ይህም ጌታ ሆይ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን ጦሬ እንድቀብር ፍቀድልኝ የሚል ነበር። የዚህ ሰውዬ ጥያቄ ትክክለኛ እና ተገቢ፣ በአሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥም እንደተቀመጠው አባትህን እና እናትህን አክብር የሚለውን ትዕዛዝ መሠረት ያደረገ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ለዚህ ሰው የሰጠው መልስ “ሙታንን ተዋቸው፣ ሙታኖቻቸውን ይቅበሩ፣ አንተ ግን ሂድና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተምር ሲል መለሰለት” (የሉቃ. 9 ቁጥር 60)። ኢየሱስ ይህን በማለቱ ከሁሉም አስቀድሞ፣ ከቤተሰብም አብልጦ ቅድሚያን በመስጠት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መመስከር፣ ወንጌልን የማብሰር ቀዳሚነትን፣ ለዚህም አገልግሎት ራስን ማዘጋጀት፣ ሞትን በማሸነፍ ለዘለዓለማዊ እንድንበቃ ያሳስበናል። ቤተክርስቲያንም ብትሆን ይህን ጥሪ በመገንዘብ የምዕመናኖችዋን ክርስቲያናዊ ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ ቆርጣ የተነሳች መሆኗን ማወቅ ያስፈልጋል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በምዕ. 9 ላይ የገለጸው ሦስተኛው የጥሪ መልስ፣ ሰውየው ምንም እንኳን ኢየሱስን መከተል ቢፈልግም፣ በቁ. 61 ላይ እንደተገለጸው፣ “ጌታ ሆይ እኔ ልከተልህ እፈልግሃለሁ፣ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ” የሚል ነበር። ኢየሱስም “ለማረስ በእጁ እርፍ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ስው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” (ሉቃ. ምዕ. 9 ቁጥር 62)።

ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስን በመከተል ላይ የምትገኝ፣ ማንኛውንም የጊዜው ሁኔታን በፍጥነት በመገንዘብ ምላሽ ለመስጠት የወሰነች ናት። ሦስቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ወይም ፍላጎት በመንፈሳዊ ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገትን ማሳየት፣ ለወንጌል ምስክርነት ራስን ማዘጋጀት እና ይህንንም ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔን ማድረግ፣ በጊዜያዊ ምቾቶች በመታለል እንቢ የምንለው ሳይሆን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመቀዳጀት የሚያስችለንን እና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን የሚያደርገንን ቀዳሚ ዓላማ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን ደግሞ በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነጻ ምርጫ እና እጅግ ውድ ለሆነው ለእግዚአብሔር ጸጋ የሚቀርብ ምላሽ እንጂ ራስን በሰዎች መካከል ከፍ በማድረግ ክብርን ለማግኘት የሚደረግ አይደለም። የክብር ሥፍራን ለማግኘት፣ መልካም ዝናን ለማትረፍ ብለው ኢያሱስ ክርስቶስን የሚከተሉ ሰዎች ወየውላቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ የሚፈልገው እርሱን እንድንወድና በቃሉ እንድንማረክ ነውና። በዚህም በመታገዝ የእኛን እርዳታ የሚፈልጉት በሙሉ በመቀበል አስፈላጊውን እንክብካቤ እንድናደርግላቸው ነው። እርሱ ራሱ ያደርግ የነበረውን እንድናደርግላቸው ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስን በደስታ እንድንከተል፣ የእርሱን መልካም ዜናን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን በፍቅር ማብሰር የምንችልበትን ሃይል በመስጠት የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን” በማለት የዕለቱን አስተንትኖአቸውን ፈጽመዋል።

01 July 2019, 16:13