ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ ራሳችንን ለራስ ወዳድነት አሳልፈን መስጠት የለብንም ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትናንት እሁድ ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖአቸውን አቅርበዋል። በዚህ አስተንትኖአቸው “ራሳችንን ለራስ ወዳድነት አሳልፈን መስጠት የለብንም” ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የሚናገረን፣ በሉቃ. 10፣25-37 እንደተጻፈው የደጉ ሳምራዊ ምሳሌን ነው። በዚህ የወንጌል ክፍል አንድ ሕግ አዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው። ኢየሱስም፣ በሕግ የተጻፈው ምን እንደሆነ እንዲያነብ በማሳሰብ እንዲህ ሲል መለሰለት።  “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” አለው (ሉቃ. 10፣27)። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው በሰዎች መካከል የተለያዩ ትርጉሞች ይሰጠው ነበር እና የሕግ አዋቂው መልሶ ኢየሱስን “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በምሳሌ መለሰለት። ምሳሌውም በሉቃ. 10,29 ላይ የተገለጸ ሲሆን ይህን ድንቅ ምሳሌ ከሉቃ. 10, ከቁ. ጀምሮ ያለውን እንድታነቡ አደራ እላለሁ። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ በምዕራፍ 10 ላይ የተገለጸው እና ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ምሳሌያዊ ንግግር በሌላ ሥፍራም ከተጠቀሱት ድንቅ ምሳሌዎች መካከል አንዱ እና የክርስትና ሕይወት ተምሳሌት ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን በምን መልኩ መምራት እንዳለበት የሚያመለክት ምሳሌ ነው። ምሳሌውንም ስላቀረበልን ወንጌላዊውን ቅዱስ ሉቃስ እናመሰግነዋለን።

የዚህ ወንጌል ክፍል ዋና ተዋናይ፣ በዘራፊዎች ተደብድቦ የወደቀውን አንድ ሰው ሊረዳ የቀረበ ደጉ ሳምራዊ ነው። አይሁዳዊያን ራሳቸውን በእግዚአብሔር የተመረጡ አድርገው ስለሚቆጥሩ ሳምራውያንን እንደ ባዕድ አድርገው እንደሚቆጥሯቸው እናውቃለን። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሳምራዊ የታሪኩ ቀዳሚ ተዋናይ አድርጎ ሲያቀርበው ያለ ምክንያት አልነበረም። ሳምራዊውን ያቀረበበት ምክንያት፣ እውነተኛ አምላካቸውን ባያዉቁትም፣ ወደ ምኩራብም ገብተው የማያውቁ ቢሆንም የተቸገረን፣ የወደቀን በማየት የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ፣ መልካምን ሠርተው በማለፍ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖሩ መሆናቸውን ለማስረዳት እና ሳምራዊያንን እንደ ባዕዳን ለሚቆጥሩት አይሁዳዊያን ትምህርት እንዲሆናቸው ስለፈለገ ነው። 

ሳምራዊው ባለፈበት ተመሳሳይ መንገድ፣ ከእርሱ ትንሽ ቀደም ብሎ አንድ ካህንና ቀጥሎም አንድ ሌዋዊ    አልፈው ነበር። ነገር ግን የወደቀውን ሰው እያዩ ገለል ብለው አለፉት። ምናልባትም ደሙ እንዳያበላሻቸው ፈርተው ይሆናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚፈልጉ ከሆነ “በሌሎች ሰዎች ደም እንዳትበከሉ ተጠንቀቁ” የሚል ትዕዛዝ አላቸውና።

ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ምንም እምነት የሌለውን ሳምራዊ ሰው የመልካም ሥራ ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል። እኛም ብንሆን በአካባቢያችን ወይም በማሕበረሰባችን መካከል እምነት የሌላቸው፣ ነገር ግን ለሌሎች መልካም ሥራን በማበርከት የሚታወቁት ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። ኢየሱስም እምነት የሌለውን ሰው ምሳሌ እንዲሆነን መርጧል። ይህም ሰው ወንድሙን በሙሉ ልቡ እና በሙሉ ሃይሉ እንደራሱ አድርጎ በመውደድ፣ ምንም እንኳ እግዚአብሔርን ባያውቀውም ፈቃዱን ፈጽሞ ተገኝቷል። ይህን በማድረጉ ምክንያት ትክክለኛ መንፈሳዊነትን እና እውነተኛ ሰብዓዊነትን በተግባር አሳይቷል።

ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ኢየሱስ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው” ብሎት ወደጠየቀው ወደ ሕግ አዋቂው ሰው ተመልሶ “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ብሎ ጠየቀው። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕግ አዋቂውን ጥያቄ እና የሁላችንም አስተሳሰብ ጭብጥ በመለወጥ፣ ባልንጀራችን በጎ ሥራችንን የምናበረክትለት ሰው ሳይሆን፣ በእርግጥም ባልንጀራዉ ማን መሆኑን ለይቶ ማወቅ የሚችለው ያ ጉዳት የደረሰበት ሰው መሆኑን እንድናስተውል ስለ ፈለገ ነው። በሉቃ. 10. 37 ላይም እንደተገለጸው ባልንጀራው ያ የራራለት ሰው መሆኑን ኢየሱስ ለሕግ ዐዋቂው በሰጠው መልስ አረጋግጧል። መልሱም “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” የሚል ነበር፣ ።

ርህራሄን ማሳየት መቻል የክርስትና ሕይወታችን መሠረታዊ ጉዳይ ነው። እርዳታን ለሚፈልግ ሰው የማትራራ ከሆነ፣ ልብህ የማይጨነቅ ከሆነ አንድ ያልተስተካከለ ነገር አለ ማለት ነው። ልብ ልንል ይገባል። ራሳችንን ለራስ ወዳድነት አሳልፈን መስጠት የለብንም። ርሕራሄን ማሳየት መቻል የአንድ ክርስቲያን የማንነት መግለጫ፣ በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መገለጫ ነው። የእግዚአብሔር አብ ርህራሄ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጦልን እንመለከታለን። አንድ ሰው መንገድ ላይ ወድቆ ካገኘሄው፣ ምናልባት ስለ ጠጣ ሰክሮ ይሆናል ከማለት ይልቅ በእርግጥ ብዙ ከመጠጣት ሰክሮ ከሆነ፣ ወይም ልቤ ለተቸገር ሰው ከመጨነቅ ይልቅ ደንድኖ ወይም ቀዝቅዞ ከሆነ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። የዚህ ጥያቄ መደምደሚያ ምህረትን ማድረግ ለሰው ልጆች የሚደረግ የእውነተኛ ፍቅር መገለጫ መሆኑን ያመለክታል። ምሕረትን በማድረግ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እና የእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር እንዲገለጥ እናደርጋለን። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ (ሉቃ. ምዕ. 6.36)። እግዚአብሔር አባታችን መሐሪ ነው፣ ምክንያቱም ርህሩህ ነውና። ርህራሄውንም በችግራችን ጊዜ ወደ እኛ በመቅረብ፣ ለበደላችን፣ ለመጥፎ ሥራዎቻችን እና አስተሳሰቦቻችን ምሕረትን በማድረግ ለእኛ ያለን ርህራሄ በተግባር ማሳየት ይችላል።

ከሁሉም በላይ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር ያለን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያለን ፍቅር እውነተኛ እንዲሆን፣ የርህራሄ ልብ እንዲኖረን እና በርህራሄ እንድናድግ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋዋን ትስጠን”።  

15 July 2019, 16:35