ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለሰኔ ወር ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ “ለቀሳውስት እንጸልይላቸው” የሚለው መሆኑ ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ መልእክት ይፋ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ለሰኔ ወር 2011 ዓ.ም ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ለቀሳውስት ጸሎት እንዲደረግ የሚጋብዝ የጸሎት ሐሳብ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት በማኅበረሰባችን ውስጥ የተለያየ መንፈሳዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ ለሚገኙ ካህናት እንጸልያላቸው ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው እንደ ገለጹት “ሁሉም ቀሳውስት ፍጹም አይደሉም፣ ነገር ግን ብዙ ቀሳውስት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ መስዋዕትነት በመክፈል ሕይወታቸውን በትህትና እና በደስታ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እያዋሉት እንደ ሆነ” በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው እነርሱ ለሕዝቦቻቸው በጣም ቅርብ በመሆን እያንዳንዳቸው በትጋት ለመስራት ፈቃደኛ ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው ስላሳዩት መልካም አብነት እና እየሰጡት ስለሚገኘው ምስክርነት ልናመሰግናቸው ይገባል ብለዋል።

“ሕይወታቸውን በቆራጥነት እና በትህትና መንፈስ እንዲሁም በኅብረት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለይም ደግሞ ድሆችን ማገልገል ይችሉ ዘንድ ለቀሳውስት እንጸልይላቸው” ብለዋል።

ካህን ማነው?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስድስት ዓመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ቀሳውስትን በተመለከተ በርከት ያሉ አስተያየቶችን መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመጋቢት 6/2014 ዓ.ም ከሮም አገረ ስብከት ካህናት ጋር በተገናኙበት ወቅት ካህናት የመልካም እረኛ ባሕሪይ መላበስ እንደ ሚገባቸው መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን አንድ ካህን “ምሕረት አድራጊ እና በርኅራኄ የተሞላ፣ ለሕዝቡ ቅርብ የሆነ እና ሁሉንም በቅንነት የሚያገለግል” መሆን ይገባዋል ማለታቸው ይታወሳል። እንደ ጎርሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሰኔ 3/2016 ዓ.ም የካህናት አመት በመባል ተሰይሞ የነበረው አመት በተጠናቀቀበት ወቅት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የካህን ልብ በክርስቶስ ፍቅር የተወጋ ልብ በመሆኑ የተነሳ ካህን ራሱን ብቻ መመልከት አይኖርበትም፣ ነገር ግን እግዚኣብሔርን እና ወንድም እህቶቹን መመልከት ይኖርበታል” ማለታቸው ይታወሳል።

እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመጋቢት 29/2018 ዓ.ም ላይ የጸሎተ ሐሙስ በዓል በተከበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት የእግዚኣብሔር ሕዝብ አንድ ካህንን የሚመለከተው “በሕዝቡ መካከል እየተንቀሳቀሰ፣ ለሕዝቡ ያለውን ቀረቤታ የሚገልጽ፣ መልካም እረኛ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያሳይ፣ ሁል ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ በእዚያ ስፍራ እንደ ሚገኝ የሚመሰክር” ካህን እንደ ሆነ አድርገው መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

06 June 2019, 14:29