ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ኅብረት ሕጋዊ መሰረት ያለውን ብዝሃነትን አያጠፋም” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 28/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዘወትር ረቡዕ እለት በሚያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ፈንታ በቅርቡ ከግንቦት 23-25/2011 ዓ.ም ድረስ በሮማኒያ ያደርገትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ ንግግር ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት ይህ እርሳቸው በሮማኒያ አድርገውት የነበረው ሐዋርያዊ ጉብኝት ከእዚህ ቀደም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ከ20 ዓመታት በፊት በሮማኒያ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በመቀጠል የተደረገ ጉብኝት እንደ ሆነ ያስታወሱ ሲሆን ይህ እርሳቸው “በኅበረት ወደ ፊት እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል ያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሳካ ይሆን ዘንድ የሰሩትን ባለድርሻ አካላት በሙሉ አመስግነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

"በሁሉም ክርስቲያኖች መካከል ያለው ኅበረት ሙሉ የሚባል ኅበረት ነው የሚያስብል ባይሆንም በአንድ ጥምቀት ላይ የተመሰረተ በመቀጠልም በሰማዕታት ደም ማኅተም ያረፈበት፣ ጨለማ በሚባሉ ጊዜያት በሁላችን ላይ በተቃጣው ስደት፣ በተለይም ባለፈው ክፍለ ዘመን ውስጥ እግዚኣብሔር መኖሩን በማያምን ሥርዓት ውስጥ የደረሰው ከፍተኛ ስቃይ ኅብረታችንን የሚያጠናክር” ሥር መሰረት እንዳለን ያሳያል ያሉት ቅዱስነታቸው በሮማኒያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በውስጣቸው ደስታን የፈጠረ፣ በሮማኒያ ሕዝቦች መካከል እንደ ነጋዲ ሆነው መገኘታቸው በራሱ እንዳስደሰታቸው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ከሮማኒያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተገናኘተን በመግባባት መንፈስ ውይይት ማደረጋቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው በወቅቱ በነበረኝ ቆይታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቀድሞ ጊዜ የነበረንን ማዕደረ ትውስታ በማሰብ በእርቅ እና በአንድነት መንፈስ በኅብረት ወደ ፊት መጓዝ እንደ ምትፈልግ መግለጻቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በእዚህ ረገድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጋራ ወደ ፊት ለመጓዝ ያላትን መሻት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከግንቦት 23-25/2011 ዓ.ም ድረስ 30ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በሮማኒያ ማደረጋቸውን ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን  በወቅቱ ቅዱስነታቸው በቡካሬስት ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደ ደረሱ የአገሪቷ ርዕሰ ብሔር አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ባሕላዊ ልብስ የለበሱ ሕጻናት ለቅዱስነታቸው የአበባ ጉንጉን በስጦታ ለቅዱስነታቸው ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የሮማኒያ የክቡር ዘበኛ የባንድ አባላት ለቅዱስነታቸው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ከእዚያም ባሻገር በሮማኒያ የሚኖሩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ለቅዱስነታቸው አቀባበል ለማድረግ በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ መገኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ከእዚያም በመቀጠል ቅዱስነታቸው ወደ ሮማኒያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት የተወሰዱ ሲሆን በእዚያው ለተገኙ የአገሪቷ ባለስልጣናት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት እና የተለያዩ አገራትን ልዑካን በተገኙበት የአገሪቷ ርዕሰ ብሔር ካደረጉት የእንኳን መጣችሁ መልእክት በመቀጠል ቅዱስነታቸው ንግግር ማድረጋቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “አንድ ማኅበረሰብ አቀመ ደካማ የሆኑ ግለሰቦችን አቅፎ መያዝ ይገባዋል” ማለታቸውን ይታወሳል።

ከእዚያም በመቀጠል ቅዱስነታቸው በግንቦት 23/2011 ዓ.ም በሮማኒያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ መኖሪያ ሕንጻ በማቅናት በሮማኒያ  የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ በሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ዳኒኤል ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው ለተገኙ በሮማኒያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ዳኒኤል እና በአገሪቷ የምትገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ቋሚ አባላት ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፣ በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “እኛን የሚያገናኝ  የእምነት ትስስር ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው” ማለታቸው መግለጻችን ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ከእዚያን በመቀጠል አዲስ በተገነባው በሮማኒያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ማቅናታቸው መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በእዚያው በሮማኒያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ዳኒኤል እና በአገሪቷ የምትገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ቋሚ አባላት ጋር “አባታችን ሆይ!” የሚለውን ጸሎት መድገማቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ቅዱሰንታቸው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኙትን የመማጸኛ ቃላትን አንድ በአንድ በአጭሩ ማብራራታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “አባታችን” የሚለው ቃል የሁላችን የሆነ አንድ የጋራ አባት እንዳለን ያሳያል፣ የእኔ አባት እና የእንተም አባት የሚለውን ትርጉም እንደ ሚያሰማ ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

“በሰማይ የምትኖር” የሚለው ቃል ደግሞ ሰማያት በሁሉም ማለትም በክፉዎች እና በደጎች፣ በፍትሃዊ እና ኢፍታዊ በሆኑ ሰዎች ላይ የምትወጣው ጸሐይ መገኛ” እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው እኛ በምድር ላይ ልናመጣው ያልቻልነውን ሰላምና ኅበረት ማስፈን እንችል ዘንድ የሚያሳስበን ነው፣ ይህንንም ለማድረግ እንችል ዘንድ በሰማይ ቤት የሚገኙትን በእምነት አባት እና እንት የሆኑትን የቅዱሳንን አማላጅነት መማጸን ይገባል ብለዋል።

“ስምህ ይቀደስ” የሚለው መማጸኛ ደግሞ በሰማይ ቤተ ከሚገኙ ከቅዱሳን ጋር በጋራ በመሆን የእኛ ስም ሳይሆን የእርሱ፣ በጎ ሥራዎችን እንድናከናውን የሚረዳን እና የምያንቀሳቅሰን የእግዚኣብሔር ስም የተቀደሰ ይሁን የሚለውን ትርጉም እንደ ሚያሰማ ገልጸዋል።

“መንግሥትህ ትምጣ” የሚለው መማጸኛ ደግሞ የአንተ መንግሥት ትመጣ ዘንድ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፣ የእግዚኣብሔር መንግሥት ይመጣ ዘንድ በናፍቆት እንጠባበቃለን፣ ምክንያቱ አሁን በዓለም ውስጥ የሚታዩ ሁኔታዎች የእግዚኣብሔር መንግሥት መምጣትን የማይደግፉ በመሆናቸው የተነሳ የሰማያዊ አባታችን መንግሥት ይመጣ ዘንድ በመማጸን በዓለም ውስጥ የሚታዩ” ያልተገቡ ድርጊቶችን በመላካም ይቀይርልን ዘንድ የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል ነው ብለዋል።

“ፍቃድህ ይሁን” የሚለው መማጸኛ ደግሞ “የእግዚኣብሔር ፈቃድ ሁሉም ይድኑ ዘንድ ነው” የሚለውን ትርጉም የሚያሰማ እንደ ሆነ ገልጸው አድማሳችንን በማስፋት ውስንነታችንን በእርሱ በአባታችን ምሕረት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የሰው ልጆች ይድኑ ዘንድ በመመኘት የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት መሆኑን ያስረዳል ብለዋል።

“የእለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው የመማጸኛ ጸሎት ደግሞ እግዚኣብሔር የሕይወት እንጀራ መሆኑን እና ይህም የተወደድን የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን እንድናስተውል ያደርገናል፣ ወላጅ አልባ ሕጻናት እንዳልሆንም እንድንረዳ ያደረገናል” የሚለውን ትርጉም እንደ ሚያሰም ገልጸው እርሱ ለሁላችን የሚያገለግል የሕይወት እንጄራ በመሆኑ የተነሳ እኛም እርስ በእርሳችን አንዱ አንዱን እንድያገልግል ይረዳን ዘንድ የምንጸልየው መማጸኛ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩም ዛሬ በዚህ አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ “የእለት እንጀራችንን ስጠን” ብለን የምንማጸነው ጸሎት በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ውስጥ በቂ የሆነ የምግብ ክምች ቢኖርም ቅሉ የሚቀመስ ምግብ አጥተው የሚሰቃዩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እግዚኣብሔር ያስባቸው ዘንድ የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል እንደ ሆነ ገልጸው በተለይም ደግሞ ከምግብ ባሻገር ፍቅር የተራቡ ብዙ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ስለሚገኙ እግዚኣብሔር በበረኩት ያጠግባቸው ዘንድ በማሰብ የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት ነው ብለዋል።

“በደላችንን ይቅር በልልን” የሚለው የመማጸኛ ጸሎት ደግሞ እግዚኣብሔር ኋጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ በማሰብ የምንጸልየው ጸሎት እንደ ሆነ ገልጸው እኛም በበኩላችን የበደሉንን ሰዎች በደል ይቅር ማለት እንደ ሚጠበቅብን የሚያሳስብ የጸሎት ክፍል እንደ ሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ይህ የጸሎት ክፍል ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ማለት እንችል ዘንድ ብርታቱን እግዚኣብሔር ይሰጠን ዘንድ የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል እንደ ሆነ ገልጸው እግዚኣብሔር ይቅር እንደ ሚለን እኛም እርስ በእርሳችን ይቅር መባባል እንችል ዘንድ እንዲረዳን፣ እንዲያነሳስን የምንጸልየው ጸሎት ነው ብለዋል።

“ወደ ፈተና አታግባን” የሚለው የመማጸኛ ጸሎት ደግሞ እግዚኣብሔር ከፈተና ውስጥ ያወጣን ዘንድ በተለይም ክፉ የሆነ መንፈስ ከልባችን ውስጥ ያስወግድልን ዘንድ በማሰብ የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በተለይም ደግሞ ወደ ፈተና ውስጥ ለመግባት በከፍተኛ ሁኔታ በምንፈተንበት ወቅት እግዚኣብሔር ከእዚህ ፈተና ያወጣን ዘንድ፣ ከኋጢአት ቀንበር ሥር ያላቅቀን ዘንድ እና ሁሉም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መሆናቸውን በመገንዘብ በጋራ እና በመተጋገዝ ወደ እርሱ ወደ እግዚአብሔር መጓዝ እንችል ዘንድ እንዲረዳን የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት መሆኑን ገልጸው እግዝአብሔርን ሁል ጊዜ አባት ብለን መጥራት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እንማጸነው ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው አስተንትኖዋቸውን ማጠናቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

06 June 2019, 15:35