ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ስለራሳችን ሳይሆን ስለክርስቶስ መመስከር ይኖርብናል” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በሰኔ 05/2011 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰትምህሮ ከእዚህ በፊ ባለፈው ሳምንት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በሐዋርያት ሥራ ላይ ትኩረቱን ያደርገ የመጀመሪያ ክፍል የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማደረጋቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም በሰኔ 5/2011 ዓ.ም ደግሞ በዩሁዳ ቦታ የተመረጠው እና ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ በድፍረት በመሰከረው በሐዋርያው ማቲያስ ላይ ትኩረቱን ያደረገ አስተምህሮ እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ስለራሳችን ሳይሆን ስለክርስቶስ መመስከር ይኖርብናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ኩቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 05/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው የቅዱስ ወንጌል ቀጣይ ክፍል ላይ ያለውን "ጉዞ" የሚያመልክት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረጋችንን ዛሬ እንቀጥላለን። ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው። ይህ በእርግጥ በሌሎች ክስተቶች መካከል የተከሰተ አንድ ክስተት ሳይሆን ነገር ግን የአዲስ ህይወት ምንጭ ነው። ደቀ-መዛሙርቱ ይህን አውቀው -ለኢየሱስ ትእዛዝ ታዛዦች ሆነው - ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው በመግባባት መንፈስ በአንድነት እና በጽናት ይጸልዩ ነበር። እናት የሆነችውን ማርያምን አጥብቀው ይዘዋል፣ የእግዚአብሔርን ኃይል አጋጣሚ በሆነ መንገድ ሳይሆን ነገር ግን በመካከላቸው ያለውን ኅብረት በማጠናከር በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።

ይህ የመጀመሪያ ማኅበረሰብ በ 120 ወንድሞች እና እህቶች የተገነባ ሲሆን በውስጡ 12 የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ምልክቶች የሚታዩበት እና የቤተክርስቲያን አርማ የሆኑ ኢየሱስ የመረጣቸው አስራ ሁለት ሐዋርያቶች በውስጥ አቅፎ የያዘ ነው። ነገር ግን አሁን አስከፊ ከሆነው መከራ እና ሞት በኋላ የጌታ ሐዋርያት ቁጥራቸው አስራሁለት ሳይሆን 11 ሁኑዋል። ከእነርሱ መካከል አንዱ የነበረው ይሁዳ በፈጸመው ተግባር ተጸጽቶ ራሱን በማጥፋቱ የተነሳ ከእነርሱ ጋር የለም።

እርሱ ከጌታ እና ከሌሎቹ ጋር ከነበረውን ኅብረት በመተው ራሱን ማግልገል የጀመረ ሲሆን ብቸኛ በመሆን ብቻውን ለመሥራት ይፈልግ ነበር፣ ራሱን ከሌሎች ገለልተኛ በማድረግ፣ ራሱን በነጻ የመስጠት ጸጋ ችላ በማለት፣ የትዕቢት ቫይረስ በጭንቅላቱ እና በልቡ ውስጥ እንዲገባ በመፍቀድ ድሆችን በመጠቀም ድሆችን ለመበዝበዝ በመፈለግ፣ ከ“ጓደኛነት” ወደ ጠላትነት በመቀየር እና “ኢየሱስን ለመያዝ የሚሄዱትን ሰዎች በመምራት” ሥራ ላይ ተጠምዶ ነበር። ይሁዳ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ቡድን አባል በመሆን እና በአገልግሎቱ ውስጥ በመሳተፍ ታላቅ ጸጋን ተቀብሏል፣ ነገር ግን በአንድ ወቅት የራሱን ሕይወት በራሱ ኃይል ያዳነ መስሎት ሕይወቱን ያጣል። እርሱ ልቡን ከኢየሱስ ጋር ማደረጉን አቁሟል፣ ከኢየሱስ እና ከሌሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት አቁሙዋል። ደቀ መዝሙር መሆኑን አቁሞ እርሱ ራሱን ከጌታው በላይ አደረገ። ኢየሱስን በመሸጥ ባገኘው ገንዘብ አንድ መሬት ተገዛበት፣ ይህ መሬት ምንም ዓይነት ፍሬ አላፈራም፣ ነገር ግን የገዛ የራሱ ደም ፈሰሰበት።

ይሁዳ ከሕይወት ይልቅ ሞትን መርጦ (ዘዳ 30:19፣ ሲራቅ 15.17 ተመልከቱ) ክፉዎች የሚጓዙበትን የጨለማ ምንገድ ተከትሉዋል (ምሳሌ 4.19; መዝ 1, 6)፣ በተቃራኒው ደግሞ ዐስራ አንዱ ሕይወትን እና በረከትን መረጡ፣ ይህ በረከት በታሪክ ውስጥ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ፣ ከእስራኤል ሕዝብ ወደ ቤተክርስትያን እንዲፈስ አላፊነቱን ተቀበሉ።

ወንጌላዊው ሉቃስ እንዳስቀመጠው ከአስራሁለቱ መሃል የአንዱ ሰው ክህደት ለተቀረው የማሕበሩ አባላት እመም የሆነባቸው በመሆኑ የተነሳ ይህ እርሱ የነበረው የሥራ ድርሻ ወደ ሌላ ሰው እንዲሻገር አድረጉ። ደግሞስ ማን ሊተካው ይችላል? ጴጥሮስ ይህንን ጥያቄ አመልክቷል- አዲስ የሚመረጠው ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ፣ ከመጀመሪያው ማለትም በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀበት እስከ መጨረሻው ማለትም ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ ከኢየሱስ ጋር የነበረ መሆን እንዳለበት አመላክቱዋል (የሐዋ. 1፡21-22)። አስራሁለቱን በድጋሚ ሙሉ አድርጎ መገንባት አስፈላጊ ነበር። በዚህ ነጥብ ላይ የማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ላይ የተመሰረት በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ውሳኔ ማደረግ አስፈልጎ ነበር፣ ይህም እውነታውን በእግዚአብሔር ዓይን፣ በማኅበር እና በአንድነት ዓይን ጭምር ማየትን ያካትት ነበር።

ለእዚህ ተግባር የሚውሉ ሁለት ሰዎችን ማለትም ኢዮስጦስ የሚሉትን፣ በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማቲያስን በእጩነት አቀረቡ። ከእዚያም በኋላ ሁሉም በአንድነት እንዲህም ብለው ጸለዩ፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ታውቃለህ፤ ከእነዚህ ከሁለቱ መካከል የመረጥኸውን ሰው አመልክተንና ። ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ትቶት በሄደው በዚህ አገልግሎትና በሐዋርያዊነት ቦታ ላይ ሹመው።” (የሐዋ. 1፡24-25)። እናም ከአስራ አንዱ ጋር ይቀላቀል ዘንድ በወቅቱ በተጣለው እጣ አማካይነት ጌታ ማቲያስን መረጠ። በእዚህም ሁኔታ ነበር አስራ ሁለቱ እንደ ገና አዲስ አካል በመሆን አዲስ ኅበረት የፈጠሩት፣ ይህም ኅብረት የመከፋፈልን፣ ገለልተኛ የመሆንን፣ የግል አስተሳሰባችንን ለማርካት ብቻ በማሰብ የግል ቦታ መፈለግን፣ በማስወገድ ሐዋርያት በመጀመርያ ደረጃ ሊሰጡት የሚገባው ምስክርነት ኅብረት መፍጠር መሆኑን አሳይተዋል። "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ" (ዮሐ. 13 35) በማለት ኢየሱስ ተናግሮ ነበር።

አስራ ሁለት ሐዋርያት በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ጌታ ያሳያቸውን አብነት ሲከተሉ እናያለን። እነርሱም የክርስቶስ የማዳን ሥራ እውቅና ያላቸው ምስክሮች እና የእነርሱ ራሳቸው ፍጹም መሆናቸውን ለዓለም ማሳየት ሳይሆን ነገር ግን በአንድነት መንፈስ ባገኙት ጸጋ በሕዝቦቹ መካከል በሚኖረውን አዲስ መንገድ የሚያሳየውን ጌታ ኢየሱስን ለሕዝቦች ሁሉ መሰከሩ። ሐዋርያት በወንድማማችነት መንፈስ ውስጥ በሚገኘው ከሙታን በተነሳው ጌታ ሥር ሆነው ለመኖር መርጠው ራሳቸውን ለመስጠት ያስቻላቸው ዘንድ ብቸኛው የጸጋ ስጦታ የሚገኘው ከእዚያ መሆኑን ተረድተው በእዚህ መንፈስ ይኖሩ ነበር።

እኛም የእግዚአብሄርን የጸጋ ስጦታ ችላ ሳንል እና አድሎአዊ ለሆነ ሥራ ያለንን እምቢተኝነት በመግለጽ ራሳችንን በራሳችን የማሞገስ ባህሪይ በማስወገድ ከሙታን የተነሳውን ጌታ መመስከር የሚያስገኘውን ውበት መልሰን መጎናጸፍ ያስፈልገናል። የክርስቲያን ማኅበረሰቡ ውስጥ በሚገኘው በሐዋርያትን መድበለ ዘር (DNA) ውስጥ በመግባት አንድነታችንና ነጻነታችንን እንዴት መጠበቅ እንደ ሚገባን በመረዳት፣ ብዝሃነትን ሳንፈራ አንድነትን እንድንፈጥር፣ ከቁሳቁሶች ጋር የተቆራኜ ሕይወት እንዳይኖረን በማድረግ እና  ሰማዕታት ለመሆን የሚረዳንን ጸጋ በመጠየቅ በታሪክ ውስጥ የምንሰራ ህያው እግዚአብሔር ምስክሮች መሆን ይጠበቅብናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
12 June 2019, 16:04