ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የእውነትን እና የፍቅርን ቋንቋ የሚትናገር ከሆነ ሁሉም ሰው ይረዳሃል” አሉ።

ክፍል ሦስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ

በእለቱ የተነበበው ምንባብ

በበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወረደ

የበዓለ ኀምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር፤ ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር (ሐዋ 2፡1-4)።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በሰኔ 12/2011 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዙሪያ ላይ ጀምረው የነበረው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ “የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ  (የሐዋ 2፡3) በሚለው ጥቅስ ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ከደረሰን መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የእውነትን እና የፍቅርን ቋንቋ የሚትናገር ከሆነ ሁሉም ሰው ይረዳሃል”! ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ኩቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 12/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የፋሲካ በዓል ከተከበረ ከአምሳ ቀናት በኋላ ሐዋርያቱ እና የጌታ እናት የሆነችው ማርያም እንደ ቤታቸው አድረገው ይጠቀሙበት በነበረው በላይኛው ክፍል በሕብረት ተቀምጠው በነበረበት ወቅት ሐዋርያቱ እነርሱ ከገመቱት በላይ የሆነ ድንቅ ነገር ሲከሰት ያያሉ። በጸሎት መንፈስ ተሰብስበው ነበር--ጸሎት  ለደቀ-መዛሙርቱ ሁል ጊዜም እስትንፋስ የሚሰጣቸው "ሳንባ" ነበር። ያለ ጸሎት አንድ ሰው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም፣ ያለጸሎት እኛ ክርስቲያኖች መሆን አንችልም! ከጸሎት መንፈስ የሚወጣው አየር የክርስቲያን ሕይወት ሳምባ ይሞላል- በእግዚአብሔር መንፈስ የተቀባ ይሆናል። ይህ ቅባት በሮቹ ዝግ ሆነው  እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ቅባት ሳይሆን ነገር ግን በሮቹን በርግዶ በመክፈት አስቀድሞ የሚወጣው ትንፋሽ እርሱ አሁን ሕያው የሆነው እርሱ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት ቃል የገባላቸው ኃይል ሆኖ ይቀርባል። “ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው » (ሐዋ 2፡2)።

ከእዚህ ዐውሎ ንፋስ ጋር በተያያዘ መልኩ የእሳት አምሳል የታየ ሲሆን እነዚህም የእሳት አምሳሎች ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ዐስርቱን ትዕዛዛት በተቀበለበት ወቅት የሚቃጠል የሚመስለው ቁጥቋጦ ጋር ይመሳሰላል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አገላለጽ እሳት ከእግዚአብሔር መገለጥ ጋር ይዛመዳል። በእሳት ውስጥ እግዚአብሔር የወደፊቱን ሁኔታ በግልጽ የሚያመለክት  ሕያው የሆኑ ቃላቱን እና ብርታቱን ያድላል። እሳት ምሳሌያዊ በአሆነ አገላለጽ የሰውን ልብስ የማሞቅ፣ የማብራት፣ ልብ ጥበበኛ እንዲሆን የማድረግ፣ ልብን ከአቧራ የማጽዳት እና ሰዎች ሰብዓዊ በሆነ መልኩ ይተጋገዙ ዘንድ የማደረግ እና ልብን የማጽዳት እና የማደስ አቅም እንዳለው ሆኖ ይገለጻል። በሲና ተራራ የእግዚአብሔር ድምፅ ሲሰማ፣ በኢየሩሳሌም በጰንጤቆስጤ በዓል ላይ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን ሊመሰርት የመረጠው ዓለት ለሆነ ለጴጥሮስ ይናገራል። የእሱ ቃል ደካማ እና ጌታን እስከ መካድ የደረሰ እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እሳት ከወረደበት በኋላ ደግሞ ብርታትን ያገኛል፣ ልቡ ይለወጣል መንፈሳዊ ለውጥ ያመጣል። በእውነትም እግዚአብሔር ደካማ የሆነውን ሰው ይመርጣል ከእዚያም ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል።

በዚህም ምክንያት ቤተክርስቲያን የፍቅር እሳት፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ብርቱ ቃላት የሚንጸባርቅባት "እሳት" ናት። አዲሱ እና የመጨረሻው ቃል ኪዳን በድንጋይ ጽላት ላይ የተፃፈው ህግ አይደለም፣ ነገር ግን ሁሉንም ነገር አዲስ አድርጎ በሚፈጥረው እና በሁሉም የሰው ልብ ውስጥ በተቀረፀው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ላይ ነው።

የሐዋርያቱ ቃል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ አዲስና የተለያዩ ቃላት ሆኗል፣ ይሁን እንጂ ሁሉም በተመሳሳይ ወቅት በሁሉም ቋንቋዎች በአንድ ጊዜ ይተረጎም እና ሁሉም ይረዱት ነበር “ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ » (2፡6) ። የእውነት እና የፍቅር ቋንቋ ነው፣ ያም ሁለንተናዊ ቋንቋ ነው፣ ያልተማሩ ሰዎች እንኳ ሊረዱት ይችላሉ። ሁሉም የእውነት እና የፍቅር ቋንቋን ይረዳሉ። ከልብህ እውነት ጋር በቅንነት የምትራመድ ከሆነ እና በሀቀኝነት መንፈስ የምትጓዝ ከሆነ፣ በፍቅር መንገድ ላይ የምትጓዝ ከሆነ ሁሉም ሰው ይረዳሃል። ምንም እንኳን በቃል ባትናገር እንኳን፣ በምታሳየው መልካምነት፣ እውነት እና ፍቅር ሰዎች ሊረዱ ይችላሉ።

መንፈስ ቅዱስ በዐውሎ ንፋስ መልክ የሚገለጽ እና ብዝሃነትን ወደ ሕብረት፣ ልዩነቶችን ወደ አንድነት በተቀናጀ መልኩ የሚመልስ ድምጽ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለእግዚአብሄር "ታላላቅ ስራዎች" የምስጋና ደረጃዎችን የሚያቀርብ መሪ ነው። መንፈስ ቅዱስ የኅብረት ፈጣሪ ነው፣ እሱ መጽናናትን የሚያመጣ ተዋናይ ነው፣ በአይሁዶችና በግሪኮች መካከል፣ በባሮችና በነፃ ሰዎች መካከል ያለውን መሰናክል እና ልዩነት እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ያውቃል፣ አንድ አካል ለመመስረት ይተጋል። እሱ የክርስቲያን ማሕበረሰቡ አንድ አካል እንዲሆን በማደረግ እና በአንድ አካል ላይ የተመሰረተ ብዝሃነት እንዲፈጠር ይደርጋል። ቤተክርስቲያን ከሰብዓዊ ገደቦች፣ ከኃጥያት እና ከማንኛውም ዓይነት ያለተጉ ተግባራት በሻገር እንዲትሄድ በማደርግ ቤተክርስቲያን እንድታድግ ያደርጋል።

በወቅቱ የተከሰተው ነገር በጣም አስደናቂ ነገር በመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ሐዋርያቱ ሰክረው ነበር በማለት ይናገሩ ነበር። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ሁሉንም ሐዋርያት በመወከል ጣልቃ ገብቶ ይህን ክስተት በዮኤል 3 ላይ እንደ ተጠቀሰው “ይህም አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ውጤት መሆኑን ይገልጻል። የኢየሱስ ተከታዮች አልሰከሩም ነገር ግን ቅዱስ አምብሮዚዮስ እንደ ሚለው በእነርሱ በሐዋርያት እና በእግዚኣብሔር ህዝብ ውስጥ እግዚአብሄርን በሕልም እና በራዕይ ውስጥ በማየት ወደ "መንፈስ ቅዱስ ስርዬት" በመግባታቸው የተነሳ የተፈጠረ ክስተት ነው። ይህ የትንቢት ጸጋ ለአንዳንዶች ብቻ የተሰጠ ስጦታ ሳይሆን የጌታን ስም ለሚጠሩ ሁሉ የተሰጠ ጸጋ ነው።

ከአሁን ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በአንድ ሰው አማካይነት በመስቀል ላይ በተሰቀለው እና እግዚኣብሔር ከሙታን ባስነሣው "በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚያልፍ ድህንነትን እንዲቀበሉ ያነሳሳቸዋል”።

ጌታ አዲስ የጴንጤ ቆስጤን ልምምድ እንዲያሳየን እንጠይቀው፣ ልባችንን ለማስፋት እና ስሜቶቻችንን ለክርስቶስ ለመስጠት፣ ያለምንም እፍረት የእርሱን ቃል በድፍረት መመስከር እንችል ዘንድ ኃይሉን እንዲሰጠን፣ የእርሱን የፍቅር ኃይል ለሁሉም መመስከር እንችል ዘንድ ኃይሉን እንዲሰጠን መንፈስ ቅዱስን እንማጸነው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 June 2019, 14:58