ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የወንድማማችነትን መንፈስ አስተምረውን አልፈዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ባቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 19/2011 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዛሬው እለት ያደረጉት የክፍል አራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር » (የሐዋ 2፡42) በሚለው ጭብጥ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን « የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የወንድማማችነትን መንፈስ አስተምረውን አልፈዋል » ማለታቸው  ተገሉጽዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 19/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የበዓለ አምሳ ወይም (ጴንጤቆስጤ) ፍሬ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ላይ በወረደበት ወቅት መልካም ዜና የሆነው የቅዱስ ወንጌል ብስራት የብዙዎቹን ሰዎች ልብ ዘልቆ በመግባት - የነፃነት ስሜት እንዲሰማቸው፣ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጡ፣ ከእዚያም በኋላ በእየሱስ ስም እንዲጠመቁ እና በመጨረሻም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ እንዲቀበሉ አደረገ። ሦስት ሺህ ያህል የሚሆኑ ሰዎች የመንድሞች ኅበረትን እንዲቀላቀሉ በማደረግ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ወንጌል የማብሰር ተግባር ዋነኛው አካል የሆነውን የአማኞች ሕብረትን ተቀላቀሉ። እነዚህ በክርስቶስ አማካይነት ወንድሞች እና እህቶች የሆኑ አማኞች የነበራቸው ውስጣዊ የእምነት ግለት በሐዋርያት አማካይነት በተዓምራት እና በምልክቶች የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያሳይ ነው። ያልተለመደው ነገር ለማዳዊ የሆነ ነገር ይሆናል፣  የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ደግሞ ህያው የሆነው የክርስቶስ መገለጫ ቦታ ይሆናል።

ወንጌላዊው ሉቃስ የኢየሩሳሌምን ቤተክርስቲያን በአብነት በመውሰድ እያንዳንዱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በእዚህ መልኩ የነበረውን በደስታ እና በትህትና የተሞላውን የወንድማማችነት መንፈስ ያሳየናል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ያለው ትረካ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ወይም አማኙ ማኅበርሰብ ከሚሰበሰቡበት ቦታ ባሻገር በመመልከት በክርስቶስ አማካይነት የተሰበሰቡ ወንድሞች እና እህቶች መካከል የነበረውን የፍቅር ኅብረት እንድንመለከት ይጋብዘናል። ውስጣዊ ይዘቱን በሚገባ በምንመለከትበት ወቅት እነርሱ ግልጽ በሆነ መልኩ “እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት በመትጋት » ይኖሩ ነበር። ክርስትያኖች የሐዋርያትን አስተምህሮ በጥሞና ያዳምጡ ነበር፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ የሆኑ ሃብቶችን በማስተባበር በአንድ ላይ ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ); « እንጀራውን በጋራ በመቁረስ » ማለትም ቅዱስ ቁርባንን በመካፈል በጸሎት አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገሩ ነበር።

በተቃራኒው ሰብዓዊው ማህበረሰብ የሌሎችን ሳይሆን የግሉን ወይም የራሱን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት የማድረግ አዝማሚያ በሚታይበት ሁኔታ የዚያ አማኝ የነበረው ማኅበረሰብ ግለሰባዊነትን በመባረክ ካለው የሚያካፍል ወደ ማኅበርሰባዊነት እንዲቀየር በማደረግ በአንድነት እና በመተባበር ማህበረ-ምዕመናዊነትን ያራምዳል። ቅዱስ ሉቃስ አማኞች በጥምቀት ጸጋ አማካይነት ገለልተኛ ከሚያደርግ  ህሊና  እና ከመመጻደቅ መንፈስ ነፃ እንደ ሆኑ የሚያረጋግጥ ምልክት የሆኑትን አንድነት እና ኅበረት እንደ ነበራቸው ይነግረናል። ጥላቻ እና መከፋፈል ይወገዳሉ፣ በወጣቶች እና በአዛውንቶች፣ በወንዶች እና በሴቶች፣ በሀብታምና በድኸ መካከል ያለው ፉክክር እጅግ ይቀንሳል። የመቀራረብ መንፈስ እና አንድነት የአማኙ ማኅበርሰብ የአኑኗር ዘይቤ መገለጫዎች ናቸው።

ስለዚህ የጥምቀት ጸጋ በክርስቶስ አማካይነት ወንድማማች በሆኑ አማኞች መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በማሳየት ካላቸው እንዲያካፍሉ መጠራታቸውን በማሳየት እራሳቸውን ከሌሎች ጋር ለማስተዋወቅ እና "ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ችግሩ ካላቸው ለማከፋል” አንሳስቶዋቸዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው እና እግዚኣብሔር እጅግ የሚደሰትበት ነገር ቢኖር የድኸውን ጩኸት ማዳመጥ ነው፣ ለድሃው ጩኸት ተመጣጣኝ የሆነ ምልሽ መስጠት ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን በቃላት ብቻ ሳይሆን ያለውን እንጀራ ከሌሎች ጋር መካፈል የሚችል ማኅበርሰብ ማለት ጭምር ነው። በዚህም ምክንያት ቤተክርስቲያን ዓለምን ለመለወጥ የሚችል እና በማኅበርሰቡ ውስጥ የፍትህ፣ የአንድነት እና የርህራሄ መንፈስ የፈጠር ዘንድ የራሷ የሆነ አስተዋጾ በማደረግ ላይ የምትገኘው።

በእዚህም የተነሳ ነው እንግዲህ አንድነትን በመፍጠር እና ለችግረኛው ሰው ትኩረት በመስጠት በእዚህ ሁኔታ በእዚህ መንገድ ላይ ቤተክርስቲያን በምትጓዝበት ወቅት በእርግጠኛነት እውነተኛውን ስርዓተ አማልኮ መኖር ትጀምራላች “በእየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር” (ሐዋ. 2፡46-27) የሚለውን በተግባር ላይ ታውላለች። ሥርዓተ-አምልኮ ቤተክርስቲያኗ ካላት በርካታ ገጽታዎች መካከል አንዱ ሳይሆን ነገር ግን የእርሱን እስትንፋስ የምናገኝበት፣ ወደ መንግሥቱ የሚወስደን በር የሚከፈትበት፣ ከሙታን የተነሳውን የምንገናኝበት እና የእርሱን ፍቅር የምንለማመድበት ቦታ ነው። ቅዱስ ሉቃስ የክርስቲያን ማኅበረሰብን የሥርዓተ አምልኮ ሁኔታን አላብራራልንም ነገር ግን ተጨባጭ በሆነ መልኩ አሳየን፣ አማኙ ማኅበርሰብ የፋሲካን ምስጢር እውነትን ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚማርበት እና የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን እውነትን ለዓለም እንዴት መግለጽ እንደ ሚገባው የሚማርበት፣ ይህ የተከበረ የአምልኮ ሥነ-ስርዓት ነው። ከዚህ አንጻር እኛ የአምልኮ ሥርዓታችንን እንዴት እንደምንኖር ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ለእኛ እንዲያው እንደ አንድ በዓል ወይም ሥረዓት ናቸው፣ ወይስ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍቅር የምንቁዳስበት እና ይህ ፍቅር ወደ ዓለም እዲፈስ የሚያደረገን ምስጢር ነው?

በመጨረሻም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚያስታውሰን ነገር ቢኖር የክርስቲያን ማኅበረሰቡ በቁጥር እያደገ ይሄድ ዘንድ ጌታ ድጋፍ እንደ ሚያደርግ ያረጋግጥልናል፣ አማኞች በእምነትና በወንድሞች መካከል ባለው እውነተኛ ወዳጅነት ውስጥ የሚጸኑ አማኞች ብዙዎችን የሚስቡና ድል የማድረጊያ ኃይል ይሆናሉ፣ ይህም በእያንዳንዱ ዘመን የሚኖር የክርስቲያን ማኅበርሰብ መሰረታዊ የሆነ ጸጋ ነው።

የእኛ ማኅበረሰብ አዲስ የሆነ ሕይወት እንዲቀበል እና በተግባር እንዲኖር፣ የአንድነት እና የመግባባት ሥፍራ እንዲሆን፣ ሥረዓተ አምልኮዎቻችን እግዚኣብሔርን እንድንገናኝ የሚያደርጉን እንዲሆኑ ያስችለን ዘንድ፣ ወንድሞች እና እህቶች እግዚኣብሔርን የሚገናኙበት ቦታ ይሆን ዘንድ ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የሚወስድ በር ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይረዳን ዘንድ ወደ እርሱ እንጸልይ።

 

26 June 2019, 15:19