ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ቅዱስ ቁርባን የሕይወታችን ማዕከል ሊሆን ይገባዋል” አሉ!

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሰኔ 16/2011 ዓ.ም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ የሚከበርበት አመታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው እና ካስተል ቤርቶኔ በመባል በሚታወቀው ቁምስና ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደረጉት ስብከት “ቅዱስ ቁርባን የሕይወታችን ማዕከል ሊሆን ይገባዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መበራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ዛሬ የተነበበው የእግዚኣብሔር ቃል ጥልቅ በሆኑት ሁለት ግሶች ላይ በጥልቀት በማሰብ እንድንደነቅ ይረዳናል፣ እነዚህ ግሶች ቀልል ያሉ ቢመስሉም ነገር ግን ለእለታዊ ኑሮዋችን በጣም አስፈላጊ ናቸው፣ እነዚህ ግሶች ደግሞ መናገር እና መስጠት የተሰኙት ናቸው።

መናገር። ንጉሥ መልከጼዴቅም “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) አብራምን ይባርክ […] ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ይባረክ።” (ዘጸ. 14፡19-20) በማለት ይናገራል። ለመልከጼዴቅ መናገር ማለት መባረክ ማለት ነው። በምድር ላይ የሚኖሩ ቤተሰቦች በእርሱ አማካይነት ይባረኩ ዘንድ አብራሃምን ይባርካል። ሁሉም ነገር የሚጀምረው በቡራኬ ነው፣ መልካም የሆነ ቃል መልካም የሆነ ታሪክ ይፈጥራል። ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ተነግሩዋል፣ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ከመመገቡ በፊት “አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ” (ሉቃስ 9፡16)። ቡራኬ አምስት እንጀራ በጣም ብዙ ለሆኑ ሰዎች በቂ ምግብ እንዲሆን አደረገ፣ ቡራኬ በረከትን ይወልዳል።

መባረክ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቃልን ወደ ስጦታ ስለሚቀይር ነው። ስንባርክ ለራሳችን የሆነ  ነገር እየሰራን አይደለም፣ ነገር ግን ለሌሎች ሰዎች መልካም ነገር እናደረጋለን ማለት ነው። መባረክ ማለት መልካም የሆኑ ቃላትን ወይም ዓረፍተ ነገሮችን መናገር ማለት አይደለም። በፍጹም እንዲህ ማለት አይደለም፣ መልካም የሆኑ ነገሮች በፍቅር ተሞልተን መናገር ማለት ነው። ለዚያም ነው ታዲያ ምንም ነገር ላላደረገለት ወይም ላልተናገረው አብራም በበረከት ይሞላ ዘንድ መልከጼዴቅ የባረከው። ኢየሱስ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ፈጽሙዋል፣ እናም እንጀራውን ባረከ በነፃ ለሁሉም እንዲዳረስ አደረገ፣ በእዚህ ተግባሩ ደግሞ በረከት ምን ማለት እንደሆነ አሳይቷል። ምን ያህል ጊዜ ነው በቤተክርስቲያን ወይንም በቤታችንም ውስጥ የተባረክነው? የማበረታቻ ቃል ወይም በግንባራችን ላይ በመስቀል ምልክት በማድረግ ቡራኬን የተቀበልነው ስንት ጊዜ ነው? ምስጢረ ጥምቀትን በተቀበልንበት ወቅት ተባርከናል፣ በእያንዳንዱ መስዋዕተ ቅዳሴ ማብቂያ ላይ እንባረካለን። ቅዱስ ቁርባን በራሱ ቡራከ ነው። ተወዳጅ የሆንን እኛን ልጆቹን እግዚኣብሔር ይባርካል ወደ ፊት እንድንጓዝም ያደርገናል። እኛም በፊናችን አንድ ላይ ተሰብስበን እግዚኣብሔርን እንባርካለን፣ ልባችንን ነፃ በማደረግ እና ደስታን መልሰን መጎናጸፍ እንችል ዘንድ በምናቀርበው የምስጋና ውዳሴ እንባረካለን። መስዋዕተ ቅዳሴን ለመሳተፍ የምንሄደው በጌታ እንደ ምንባረክ እርግጠኛ በመሆን ሲሆን ወደ ቤታችን ስንመለስ ደግሞ እኛም በተራችን በዓለም ውስጥ መልካም የሆኑ መሰመሮ ይዘረጉ ዘንድ ሌሎችን እንባርካለን።

ይህም ለእኛም እውነት የሆነ ነገር ነው፣ እኛ ካህናት የእግዚአብሔርን ህዝብ መባረክ ይኖርብናል። ውድ ካህናት የእግዚኣብሔርን ሕዝብ መባረክ እንዳትፈሩ።  ውድ ካህናት የእግዚሐብሔርን ሕዝብ መባረካችሁን ቀጥሉ። እግዚኣብሔር ሕዝቡን መባረክ ይፈልጋል፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር መግለጽ ይፈልጋል። የተባረኩ ሰዎች ብቻ ናቸው ሌሎችን መባረክ የሚችሉት። በዛሬው ዘመን የሚገኙ ሰዎች ከእዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ቀለል አድርገው ማሰባቸው ያሳዝነኛል፣ ይራገማሉ ሌሎችን ይሳደባሉ። በአጠቃላይ በቅዥት ውስጥ ገብተው ይኖራሉ ቁጣችን በሁሉም ሰው ላይ ነው። የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ በጣም የሚጮኹ እና በኃይለኛ ድምጽ የሚናገሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይማርካሉ እና ሌሎችን ያሳምናሉ። በእዚህ ዓይነት የእብሪት መንፈስ እንዳንጠቃ እንጥንቀቅ፣ መራራ  በሆኑ ነገሮች እንዳንወሰድ እንጠንቀቅ፣ ምክንያቱም እኛ የምንመገበው እንጀራ በውስጡ መልካም የሆነ ጣዕም አለውና። የእግዚኣብሔር ሕዝብ ማጉረመረምን ሳይሆን ማመስገንን ይወዳል፣ የተፈጠርነው ሌሎችን እንድንባርክ ነው እንጂ እንድንረግም አይደለም። በቅዱስ ቁርባን አማካይነት ኢየሱስ ለእኛ እንጀራ ሆኖ ቀርቡዋል፣ ይህ እንጀራ ደግሞ የቤተክርስቲያንን አጠቃላይ ሁኔታ ይዞ ይገኛል፣ ያሉንን ነገሮች ሁሉ እንባርካቸው፣ እግዚኣብሔርን ለማመስገን እንጠቀምበት፣ ሌሎችን የሚያበረታታ ቃላትን ለመናገር እንጠቀምበት።

ሁለተኛው ግስ ደግሞ መስጠት የሚለው ነው። “መናገር” ከእዚያን በኋላ መስጠት የሚለው ይከተላል። አብርሃም ያደርገው ይህንኑ ነው፣ በመልከጼዴቅ ከተባረከ በኋላ “ካለው ሁሉ አስራት ሰጠው”። ኢየሱስ ያደረገው ይህንኑ ነበር፣ እጀራውን አንስቶ ከባረከ በኋላ እንጀራው ለሕዝቡ እንዲከፋፈል አደረገ። ይህ አንድ ውብ የሆነ ነገር ይነግረናል። እንጀራ እንዲሁ እኛ ብቻችንን የምንመገበው ነገር ሳይሆን ከሌሎች ጋር የምናጋራው ነገር እንደ ሆነ ያሳያል። በሚደንቅ ሁኔታ ኢየሱስ አምስት እንጀራ እና ሁለት ዓሳ ባርኮ አምስት ሺህ ሰው የመገበበት ሁኔታ እጅራው ከተባረከ በኋላ በቁጥ ስንት መድረሱን አይገልጽም። በተቃራኒው በእዚህ ታሪክ ውስጥ የተገለጸው “ቆረሰ”፣ “ሰጠ” እና “አከፋፈሉ” የሚሉ ቃላት ናቸው የተጠቀሱት። በእርግጥ የእዚህ ታሪክ ዋነኛው ትኩረት ወይም ጭብጥ እጀራው እንዴት ሊበረክት እንደ ቻለ መግለጽ ሳይሆን ነገር ግን መቋደስ የሚለውን ቃል ለመግለጽ የተጠቀመበት ነው። ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው፣ ኢየሱስ አስማታዊ የሆኑ ነገሮችን አያከናውንም፣ አምስት የነበረውን እንጀራ ወደ አምስት ሺህ እንጀራ ቀይሮ “ይሄውላችሁ! ይህንን ለሕዝቡ አከፋፍሉ” አላለም። እንዲህ በፍጹም አላደረገም። ኢየሱስ በመጀመሪያ ጸለየ ከዚያም አምስቱን እንጀራ በአባቱ በመተማመን ባረከ ከእዚያም ቆረሰ። እነዚያ አምስት እንጀራዎች ለሕዝቡ አላንሱዋቸውም ነበር፣ በቂ ነበሩ። ይህ አስማታዊ የሆነ ተግባር ሳይሆን በእግዚኣብሔር እና በእርሱ መለኮታዊ ጥበቃ ስንተማመን የሚገኘውን ጸጋ ያመለክታል።

በዓለማችን ላይ እኛ ገቢያችንን እና ምርቶቻችንን ለማሳደግ ብቻ በማሰብ ሁልጊዜ እንለፋለን። ግን ለምን? መስጠት ወይስ መቀበል? ማጋራት ወይም ማጠራቀም? በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው "ሐብት" የሚገኘው በማከማቸት ሳይሆን በማካፈል፣ የምንበለጽገውም ከሌሎች ጋር ስንጋራ ብቻ እንደ ሆነ ይገልጻል። ጥቂቶችን ስግብግብ የሆኑ ሰዎችን የሚያረካ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለዓለም ህይወት ይሰጣል። ኢየሱስ የተጠቀመበት ቃል ማከማቸት የሚለውን ሳይሆን መስጠት የሚለውን ቃል ነው የተጠቀመው።

“የሚበሉትን ስጡዋቸው” (ሉቃስ 9፡13) ብሎ ነበር ለደቀ-መዛሙርቱ በቀጥታ የተናገረው። በአዕምሮአቸው ውስጥ የተከሰተውን ሐሳብ ልንገምት እንችላለን: "ለራሳችን እንኳን የሚሆን በቂ ምግብ የለንም፣ አሁን ስለ ሌሎች ማሰብ ይኖርብናል ወይ? መምህራችንን ለማዳመጥ የመጡት ራሳቸው ናቸው፣ ታዲያ ለምንድነው እርሱ እኛ የሚበላ ነገር የምንሰጣቸው? የራሳቸውን ምግብ ካላመጡ ወደ ቤታቸው ይመለሱ፣ ችግራቸው ነው፣ ወይም ደግሞ ለእነርሱ የሚሆን ምግብ መግዛት እንችል ዘንድ የሚያስችል ገንዘብ ይስጡን "። የእዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፣ ከኢየሱስ አመክንዮ ውጪ የሆነ አስተያየት ነው። እርሱ ኢየሱስ የሚለው ግን “እናንተ የሚበላ ነገር ስጡዋቸው” ነው የሚለው። ያለን ነገር ሁሉ ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው ካለን ስናካፍል ብቻ ነው፣ ኢየሱስ ሊነግረን የፈለገው ነገር ይህ ነው፣ የምንሰጠው ነገር ትልቅ ይሁን ትንሽ መስጠት ግን ይኖርብናል። ጌታ አምስት እንጀራ አምስት ሺህ ሰው እንደ መገበው በእኛ ትንሽነት እርሱ ታላቅ ነገሮችን ይፈጽማል። እርሱ አስደናቂ ተዓምራት የሆኑ ለየት ያሉ ተአምራትን አልሰራም ወይም አስማታዊ የሆኑ ነገሮችን አልፈጸመም፣ እርሱ የሚሰራቸው ተአምራት ቀልል ያሉ ነገሮችን በመጠቀም ነው።  የእግዚአብሔር ታላቅ ኃይል ትሁት እና በፍቅር የተገነባ ነው። ፍቅር ደግሞ በትናንሽ ነገሮች አማካይነት ትላልቅ ነገሮችን የማከናወን አቅም አለው። ቅዱስ ቁርባን የሚያስተምረን ይህንን ነው፣ በትንሽ ቁራሽ በሆነ እንጀራ ውስጥ ጌታን እናገኘዋለን። ቀላል፣ ወሳኝ የሆነ በተቆረሰ እንጀራ መልክ የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን እግዚአብሔር የሚያከናውናቸውን ነገሮችን ለማየት እንድንችል ይረዳናል። ራሳችንን ለሌሎች አሳልፈን እንድንሰጥ ያነሳሳናል። "ይቅርታ ያ የእኔ ጉዳይ አይደለም" ወይም "ጊዜ የለኝም፣ እኔ ልረዳህ አልችልም፣ የእኔ ችግር አይደለም" ለሚለው የአእምሮ አስተሳሰብ ማርከሻ መድኃኒት ነው።

በከተማችን ውስጥ ብቻቸውን የሚኖሩ ብዙ አረጋውያን፣ ችግር ላይ የሚገኙ ብዙ ቤተሰቦችን፣ እለታዊ እጀራ ለማግኘት እና ሕልማቸውን እውን ለማደረግ የሚኳትኑ እና የሚታገሉ ወጣቶችን፣ ፍቅር የተራቡ እና የተጠሙ እንዲሁም እንክብካቤ ያጡ ሰዎችን ጌታ ለእያንዳንዳችን “እናንተ የሚበላ ነገር ስጡዋቸው” በማለት ይናገረናል። በእዚህን ጊዜ አንተ ምን አልባት “እኔ ብዙ ነገር የለኝም፣ ይህንን የማደረግ አቅም የለኝም” ብለህ ትመልስ ይሆናል። ይህ እውነት አይደለም፣ አንተ “ትንሽ” የምትለው ነገር በኢየሱስ ፊት ትልቅ ዋጋ አለው፣ ኢየሱስ ይባርከው ዘንድ ፍቀድለት። አንተ ብቻህን አይደለህም፣ ቅዱስ ቁራባን ከአንተ ጋር አለ፣ በእየለቱ ከአንተ ጋር የሚሆን እጀራ አለ፣ ይህም የኢየሱስ እንጀራ ነው። ይህንን እንጀራ በልባችን ውስጥ የምንቀበል ከሆነ ይህ እንጀራ በውስጣችን የፍቅር ኃይል እንዲኖር ያደርጋል። እንደ ተባረክን እና እንደ ተወደድን ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል፣ በእዚህም ተነሳስተን እኛም እንድንባርክ እና እንድንወድ ያነሳሳናል፣ ያንን ቡራኬ እና ያንን ፍቅር በየከተማዎቻችን ጎዳናዎች ላይ ከሚገኙ ድሆች ጋር እንድንጋራ ይረዳናል።

 

23 June 2019, 18:05