ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ተንከባካቢ የሌላቸውን ሰዎች ተቀብሎ ማስተማር ተገቢ ነው አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 08/2011 ዓ.ም የክርስትያን ወንድሞች በመባል ከሚታወቀው መንፈሳዊ ማኅበር አባላት ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት እንደ ገለጹት በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የክርስትያን ወንድሞች ትምህርት ቤቶች ማኅበረሰቡ ችላ ያላቸውን ወገኖች በርኅራኄ ተቀብለው በትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ ትምህርት እንዲያገኙ እና “የትንሣኤ ባሕል” በማስተዋወቅ አዲስ የሕይወት ተስፋ ይፈነጥቁ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በክርስቲያን ወንድሞች ማኅበር የሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች የላሳል ትምህርት ቤቶች በመባል የሚታወቁ ሲሆን ይህ መጠሪያ ስም የተሰጣቸው የዛሬ 300 አመት ገደማ ይህንን የክርስቲያን ወንድሞች ማኅበር በመባል የሚታወቀውን ማኅበር በመሰረተው በቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል በመባል በሚታወቀው ፈረንሳዊ የማኅበሩ መስራች ስም እንደ ሆነም ተገልጹዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል እ.አ.አ በ1680 ዓ.ም የክርስትያን ወንድሞች መንፈሳዊ ማኅበር በመመስረት ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት መስጫ ተቋም በመገንባት ጥራት ያለው ትምህርት በተለይም ለድሃው ማህበረሰብ ክፍል ልጆች ይሰጡ ዘንድ ይህንን መንፈሳዊ ማኅበር ማቋቋማቸው ይታወሳል።

የዚህ የክርስትያን ወንድምቾ መንፈስዊ ማኅበር አባላት የመስራቻቸውን 300ኛ የሙት አመት በዘከሩበት ወቅት በማግስቱ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል ያደነቁ ሲሆን “በወቅቱ በትምህርት ዘርፍ አዲስ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት የፈጠረ ቅዱስ በመሆኑ” ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ጨምረው እንደ ገለጹት ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል በወቅቱ የፈጠረው አዲስ የመማር የማስተማር ስረዓት የመምሕር ፅንሰ-ሀሳብን ጨምሮ አሁንም ድረስ ይህ ቅዱስ የሚወደስበት አዳዲስ የማስተማር ዘዴዎችን ጥሎ ማለፉን ጨምረው ገልጸዋል።

ትምህርት የማግኘት መብት

“ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል የፈጠረው የትምህርት ቤት ጽንሰ-ሐሳብ ድሆችን ጨምሮ ትምህርት ለሁሉም ማኅበርሰብ ተደራሽ መሆን አለበት፣ እያንዳንዱ ማኅበርሰብ ትምህርት የማግኘት መብት አለው” የሚል አመለካከት እንደ ነበረው በንግግራቸው ወቅት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ይህንን አመለካከቱን ከግብ ለማድረስ ይቻለው ዘንድ “ይህንን ተግባር ቤተክርስትያን ብቻዋን መወጣት እንደ ማትችል በመገንዘቡ የተነሳ ምዕመናኑን በዚህ የመማር የማስተማር ተግባር ውስጥ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ በጊዜው የነበረውን ማኅበራዊ የሐሳብ ግጭት ለመፍታት ችሉዋል” ብለዋል።

እ.አ.አ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ አገር ትምህርት ይሰጥ የነበረው በካህናት አማካይነት እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ምዕመናን በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ማካተት በወቅቱ እንደ አዲስ አብዮት ተደርጎ ይቆጠር የነበረ ሲሆን በወቅቱ የክርስትያን ወንድሞች ማኅበርን በማቋቋም በተለይም የድሃ ልጆችን ትምህርት ማስተማር ይችሉ ዘንድ መንገድ መክፈቱን ገልጸዋል።

የማስተማር ተልዕኮ

ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል መምህራንን በተመለከተ የነበረውን አመለካከት በተመለከተ የገለጹት ቅዱስነታቸው “ትምህርት በጣም ወሳኝ የሆነ እውነታ በመሆኑ የተነሳ የማስተማር አገልግሎት የሚሰጡ መምሕራን በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል” የሚል ከፍተኛ እምነት እንደ ነበረው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

በጊዜው በቂ እና ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል መዋቅር እና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ባለመኖራቸው የተነሳ ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል የማስተማር አገልግሎት እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ ሳይሆን እንደ አንድ ተልዕኮ እንዲቆጠር የራሱን ከፍተኛ የሆነ አስተዋጾ አድርጎ ማለፉን የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህም የተነሳ ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል በተፈጥሮ የማስተማር ክህሎት ያላቸውን ሰዎች በመሰብሰብ የመምሕር ሙያ የተከበረ ሙያ እንደ ሆነ አሳይቶ ያለፈ ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል “የተራቀቀ እውነታ ላይ የተመሰረት የመማር/ማስተማር ዘዴ” የቀየሰ ቅዱስ እንደ ነበረ በንግግራቸው ወቅት የጠቀሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን አዲስ የመማር/የማስተማር ዘዴ ገቢራዊ በማድረግ በዘመኑ ፈር ቀዳጅ የነበረ ቅዱስ እንደ ነበር ጨምረው ገልጸዋል። በጊዜው በፈረንሳይ በስፋት ይነገር የነበረው ቋንቋ የላቲን ቋንቋ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል ግን ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በፈረንሳይኛ እንድማሩ በማድረግ ተማሪዎችን እንደ የትምህርት አቀባበል ችሎታቸው በቡድን በቡድን በመከፋፈል እንደ የደረጃቸው አስፈላጊውን እውቀት እንዲቀስሙ የራሱን ጥረት አድርጎ ማለፉን ቅዱስነታቸው ጨምረው የገለጹ ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል በቂ የሆኑ መምሕራንን ለማፍራት በማሰብ ሴሚናሮችን በመስጠት መምህራንን ያሰለጥን እንደ ነበረ፣ በተጨማሪም ጎልማሶች እሁድ እሁድ የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቶ የነበረ ቅዱስ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ ባቲስታ ዲ ላ ሳል “ለሁሉም የሰው ልጆች ክፍት የሆነ ትምህርት ቤት ይመኝ እና ያልም እንደ ነበረም” ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

18 May 2019, 09:59