ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚኣብሔር ለሚያቀርብልን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት አይገባም” አሉ።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ከትንሣኤ በዓል በኋላ የሚገኘው አራተኛው እለተ ሰንበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎት የሚደረግበት እለተ ሰንበት እንደ ሆነ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ይህ 56ኛው ዓለማቀፍ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎት የሚደረግበት ቀን በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 04/2011 ዓ.ም በጸሎት ታስቦ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን ይህንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎት የሚደረግበትን እለት በማስመልከት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት “እግዚኣብሔር ለሚያቀርብልን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ” ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎትየሚደረግበት እለት ኢየሱስ “ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው። ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት” (ማቴ 9፡37-38) በማለት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሮ እንደ ነበረ በማስታወስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ራሳቸውን ዝግጁ ያደርጉ ቄሳውስት እና ደናግላን በቁጥር እና በጥራት እየበዙ በእዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ጥቂቶች ግን ተጠራጠሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28፡ 16-20) በማለት ኢየሱስ የሰጣቸውን ታላቅ ተልዕኮ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ በማሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የሚውል የጸሎት ቀን ነው።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንፍሳዊ ጥሪ የሚደረግ የጸሎት ቀን እ.አ.አ በ1964 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ጌታ የሰጠን ታላቁ ተልዕኮ ቀጣይነት ባለው መልኩ ግቡን ይመታ ዘንድ መንፈሳዊ የሆነ አግልግሎት የሚሰጡ ቄሳውስት እና ደናግላን በቁጥር እና በጥራት ይበዙ ዘንድ ወደ ጌታ ጸሎት የደረግ ዘንድ ባወጁት መሰረት የሚደረግ የጸሎት ቀን እንደ ሆነ የሚታወስ ነው።

እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተከበረው ለመንፈሳዊ ጥሪ የሚደረግ ጸሎት ቀን መሪ ቃል ሆኖ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የተመረጠው “ለአምላክ የገባነውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችል ብርታት ይኑረን” የሚለው መሪ ቃል እንደ ነበረ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻል ሲሆን ይህንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎት የሚደረግበትን ቀን አስመልክተው ቅዱስነታቸው አስተላልፈውት በነበረው መልእክት እንደ ገለጹት “ ለምስጢር ጥምቀት ምስጋና ይግባውና ሁላችንም ክርስቲያኖች የየራሳችን የሆነ ጥሪዎች አሉን” በዚህም የተነሳ እያንዳንዱ ክርስትያን በተጠራበት የኑሮ መስክ ውስጥ ጥሪውን ማስተላለፍ ይችላል ማለታቸውም ተገልጹዋል። “የእያንዳንዳችን ሕይወት ምልአት ያለው ሕይወት እንዲሆን ነው እንጂ ሕይወታችን እንደ እስር ቤት እንዲሆን እግዚኣብሔር አይመኝልንም” በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው “እግዚኣብሔር ለሚያቀርብልን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ላለማለት ታላቅ ብርታት ያስፈልጋል፣ ይህ ጥሪ ደግሞ ከሁሉም በላይ እግዚኣብሔር ላቀረበልን የደህንነት እቅድ በነጻ የሚሰጥ ሕይወት መሆኑን እና እኛ መልካም እንድንሆን እና ደስተኞች እንሆን ዘንድ” የተሰጠን ጥሪ መሆኑንም መዘንጋት አይኖርብንም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማብቂያ ላይ እንደ ገለጹት ከጌታ ጋር በምንፈጥረው የጠበቀ ግንኙነት አማካይነት ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለጌታ አገልግሎት እንድንሰጥ የሚያነሳሳንን ጥሪ፣ ወይም ደግሞ ካህናት እና ገድማዊያን ገዳማዊያት በመሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጀመረውን ተልዕኮ ለማስቀጠል እንችላለን ብለዋል።

12 May 2019, 18:50