ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት  

ር.ሊጳ ፍራንቸስኮስ “ኃጢአት ያስረጃል፣ መንፈስ ቅዱስ ግን ወጣቶች እንድንሆን ያደርጋል”!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንታንው እለት ማለትም በግንቦት 20/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቄሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ከዮሐንስ 16፡5-11 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና “ኢየሱስ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁ፣ አጽናኙን መንፈስ ቅዱስ እልክላችኋለሁ” ብሎ ለሐዋርያቱ በተናገረው ቃል ላይ መስረቱን ባደረገው ስብከት እንደ ገለጹት “ሐዘን የክርስቲያን ባህሪ መገለጫ አይደለም” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩም “ሕይወት በደስታ ብቻ የተሞላች አይደለችም” በሕይወት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች እና ችግሮች ያጋጥማሉ፣ እነዚህን ውጣ ውረዶች እና ችግሮች ማለፍ ግን ይቻላል፣ እነዚህን ውጣ ወረዶች እና መከራዎችን ለማለፍ ግን እለታው በሆነ መልኩ ከእኛ ጋር በመሆን ከእኛ ጋር ይጓዝ ዘንድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ዋናው ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ” መሆኑን በአጽኖት በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ የነበረውን ቆይታ አጠቃሎ ወደ አባቱ ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት ለሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ እና መንፈስ ቅዱስ ማን መሆኑን የሚያመልክቱ አስተምህሮ እንደ ሰጣቸው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በቅርብ ጊዜ ከእነርሱ ተለይቶ እንደ ሚሄድ ስለነገራቸው በዚህ ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ አዝነው ስለነበረ ኢየሱስ በዚህም ምክንያት እንዳያዝኑ በመገሰጽ ይህንን አስተምህሮ ሰጥቶዋቸው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ገለጸው ምክንያቱም “ሐዘን የክርስትያን መገለጫ ባህሪ ሊሆን በፍጹም አይገባም” ብለዋል። ታዲያ ወደ ሐዘን ውስጥ ላለመግባት ምን ማድረግ ይኖርብናል? “ከሐዘን መንፈስ ለመራቅ በጸሎት አማካይነት መንፈስ ቅዱስ በድጋሚ በአዲስ መልክ እንዲያድሰን እንዲረዳን ጌታን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል” ያሉት ቅዱስነታቸው መንፈስ ቅዱስ ዘወትር አዲስ በሆነ መልኩ እንድንታደስ ይረዳናል ብለዋል።

ሐዘንተኛ የሆነ ክርስትያን  

አንድ ታልቅ የሆነች ቅድስት ‘በሐዘን መንፈስ የተሞላ አንድ ቅዱስ ሰው ሐዘንተኛ የሆነ ቅዱስ ነው’ ትል እንደ ነበረ በማስታወስ ስበከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህም መሰረት ሐዘንተኛ የሆነ አንድ ክርስትያን ሐዘንተኛ ክርስትያን ነው፣ ይህ ደግሞ ተገቢ የሆነ ነገር አይደለም” ብለዋል። በዛሬው የመጀመሪያው ምንባብ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው (የሐዋ. 16፡22-34) መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስን እና ሲላስን መከራ በሚደርስባቸው ወቅት ለእግዚኣብሔር የምስጋና መዝሙር እንዲዘምሩ እና መከራውን እንዲቋቋሙ ያደርገው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ገልጸው በተመሳሳይ መልኩም እኛ መከራዎቻችንን መሸከም እንችል ዘንድ የሚረዳን እና የሚደግፈን መንፈስ ቅዱስ ነው ብለዋል። “መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም በአዲስ መልክ ያድሳል፣ በሕይወታችን ከእኛ ጋር የሚጓዝ እና እኛን የሚደግፈን መንፈስ ቅዱስ ነው፣ እርሱም አጽናኙ ጴራቅሊጦስ ነው” ብለዋል። ይህንን ሐሳባቸውን በሚገባ ለመግለጽ በማሰብ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

ጴራቅሊጦስ፡- ጴራቅሊጦስ የሚለው ቃል ትርጉሙ እኔ እንዳልወድቅ እና ወደ ፊት ቀጥ ብዬ መጓዝ እችል ዘንድ፣ በአዲስ መልክ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንድታደስ “ከአጠገቤ ሆኖ የሚደግፈኝ” የሚለውን ትርጉም ያሰማል። ክርስትያን ሁልጊዜም ቢሆን ወጣት ነው። የአንድ ክርስትያን ልብ ማርጀት ከጀመረ ደግሞ በእዚያኑ ልክ የክርስትናው ጥሪ እየቀነሰ ይመጣል። ወጣት የሆነ ልብ እና ነፍስ የሌለህ ከሆነ፣ አንተ ሙሉ ክርስትያን አይደለህም ማለት ነው።

“እለታዊ በሆነ መልኩ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምናደርገው ውይይት ወደ ፊት እንድንሄድ ያደርገናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በሕይወት ሂደት ውስጥ መከራ ሊያገጥመን እንደ ሚችል ገልጸው ምንም እንኳን ሐዋርያው ጳውሎስ እና ሲላስ በድንጋይ ተወግረው ከፍተኛ ስቃይ ቢደርስባቸውም ቅሉ “እነርሱ ግን በደስታ ተሞልተው የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ገልጸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል . . .

ወጣት መሆን ማለት እንግዲህ ይህ ነው። የእዚህ ዓይነት ወጣትነት ደግሞ ሁሉንም ነገር በተስፋ እንድትመለከት ይረዳሃል፣ ወደ ፊት እንድትጓዝ ያደርግሃል። ነገር ግን የዚህ ዓይነቱን የወጣትነት መንፈስ ለመጎናጸፍ ደግሞ ቀጣይነት ባለው መልኩ በእየ ዕለቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መወያየት ያስፈልጋል፣ ከአጠገባችን እንዲሆን ልንጠይቀው ይገባል። ይህም ኢየሱስ ጥሎልን የሄደው ትልቁ ስጦታ ወይም ጸጋ ነው፣ ይህ ድጋፍ ወደ ፊት እንድንጓዝ ይረዳናል።

ኋጢአት ነፍሳችንን ያስረጃል፣ መንፈስ ቅዱስ ግን ወጣት ያደርገናል

“ኋጢአት ነፍሳችንን ያስረጃል፣ መንፈስ ቅዱስ ግን ነፍሳችንን ወጣት ያደርገል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን እኛ ሁላችን ኋጢአተኞች ብንሆንም ቅሉ በኋጢአታችን እንድንጸጸት እና ወደ ፊት እንድንመለከት መንፈስ ቅዱስ እንደ ሚረዳን ገልጸው በዚህም የተነሳ “ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መነጋገር ልመዱ እርሱም ድጋፉን ይሰጣችኋል፣ አዲስ እንድትሆኑም ያደርጋችኋል” ብለዋል። በአንጻሩ ደግሞ “ኋጢአት እኛን በከፍተኛ ደረጃ ያስረጃል፣ ሁሉንም ነገር አሮጌ ያደርጋል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህም የተነሳ ነፍሳችን ሐዘንተኛ እንድትሆን እንደ ሚያደርጋት ገልጸው በሐዘን ስሜት ውስጥ መግባት ደግሞ የክርስትያን ሳይሆን የአረማዊ ባሕሪይ በመሆኑ የተነሳ ምንም እንኳን በሕይወት ሂደት ውስጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን የሚችሉ ቢሆኑም ቅሉ መንፈስ ቅዱስ ግን ወደ ፊት እንጓዝ ዘንድ እና ችግሮቻችንን እንሻገራቸው ዘንድ ያግዘናል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስበከታቸውን አጠቃለዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 May 2019, 16:54