ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊጳ ፍራንቸስኮስ ለቡልጋሪያ እና ለሰሜን መቀዶኒያ ምስጋና አቀረቡ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቡልጋሪያ እና በሰሜን መቀዶኒያ ከሚያዝያ 27-29/2011 ዓ.ም ድረስ በቅደም ተከተል ያደርጉትን 29ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው በሚያዝያ 29/2011 ዓ.ም አመሻሹ ላይ ወደ ቫቲካን መመለሳቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በትላንትናው እለት ማለትም በሚያዝያ 30/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በወቅቱ ዘወትር ረቡዕ እለት በሚያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ፈንታ በቅርቡ በቡልጋሪያ እና በሰሜን መቀዶኒያ አድርገው ስለነበረው 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገራቱ ባለስልጣናት እና ሕዝቦች ጭምር ስለተደረገላቸው መስተንግዶ ምስጋና አቅርበው እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቡልጋሪያ እና ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ እንደ ገለጹት በቡልጋሪያ ያደርጉት 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት የቅድስት መንበርን በመወከል በቡልጋሪያ ለዐስር አመታት ያህል የቅድስት መንበር ልዑክ በመሆን ባገለገሉት  “በቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ዘላለማዊ ማህደረ ትውስታ" ተሞልተው እንደ ነበረ ገልጸዋል። በቡልጋሪይ ላደርጉት 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት የተመረጠው መሪ ቃል በላቲን ቋንቋ “Pacem in Terris” በአማርኛ “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” የሚለው እንደ ነበረ ያስተወሱት ቅዱስነታቸው ይህም የሆነበት ምክንያት ሁሉም የሰው ልጆች በወንድማማችነት መንፈስ ሆነው በጋራ ይራመዱ ዘንድ ለመጋበዝ እንደ ሆነ ገልጸው በቡልጋሪያ በነበራቸው ቆይታ ከቡልጋሪያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ከሆኑት ብጽዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ኔዎፊት እና ከሲኖዶሱ ጋር ተገናኝተው እንደ ነበረ አስታውሰው “እንደ ክርስቲያኖች የእኛ ጥሪ እና ተልዕኮ የአንድነት ምልክትና መሣሪያ መሆን እንዳለበት ተነጋግረናል" ብለዋል።

ቡልጋሪያ፣ ቅዱሳን ቀሬሊዮስ እና መቶድየስ

ቅዱስነታቸው በቅርቡ በቡልጋሪያ አድርገውት ስለነበረው 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት በተናገሩበት ወቅት እንደ ገለጹት ቅዱሳን ቀሬሊዮስ እና መቶድየስ በቡልጋሪያ የክርስትናን እምነት ያስተዋወቁ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጸው ምንም እንኳን እነዚህ ሁለቱ ቅዱሳን በትውልድ ግሪካዊያን የነበሩ ቢሆንም “ነገር ግን የአገሪቱን ባሕል ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ ለእስላቪ ሕዝቦች የክርስትና እምነትን በተሳካ መልኩ” አስተላልፈው እና መስክረው ማለፋቸውን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “ዛሬም ቢሆን ቅዱስ ወንጌል በርኅራኄ እና በዘዴ” መሰበክ እንደ ሚገባው የተናገሩት ቅዱስነታቸው በዚህ መልኩ ቅዱስ ወንጌልን ለማያውቁ ሕዝቦች ማዳረስ እና እንዲሁም ከዚህ ቀደም የክርስትና እምነት ሥር መሰረት የነበራቸው፣ ነገር ግን አሁን ያ ሥር የደረቀባቸው አገራት ሥራቸው መልሶ ይለመልም ዘንድ ቅዱስ ወንጌልን በርኅራኄ እና በዘዴ መስበክ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሰሜን መቀዶኒያ እና ቅድስት እማሆይ ትሬዛ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቡልጋሪያ የነበራቸውን የሁለት ቀን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛ መዳረሻ የሆነችውን ሰሜን መቀዶኒያ በሚያዝያ 29/2011 ዓ.ም መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን በሰሜን መቀዶኒያ ለአንድ ቀን ያህል አድርገውት የነበረውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ እንደ ተናገሩት በመቀዶኒያ በነበራቸው ቆይታ “ጠንካራ የሆነው የቅድስት እማሆይ ትሬዛ መንፈሳዊ ጥበቃ ከእርሳቸው ጋር እንደ ነበረ” ገልዋል። የሰሜን መቀዶኒያ ዋና ከተማ የሆነችው እስኮፒዬ እማሆት ትሬዛ ተወልደው ያደጉበት ሥፍራ እንደ ሆነ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህቺ ከተማ እ.አ.አ ከ1910 ዓ.ም ጀመሮ የሰሜን መቀዶኒያ ዋና ከተማ እንደ ሆነችም የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው በሰሜን መቀዶኒያ በሚገኘው የእማሆት ትሬዛ የትውልድ ሥፍራ ተገኝተው እንደ ነበረ ገልጸው እርሳቸው ትንሽ የሆኑ ነገር ግን ጠንካራ የሆኑ ሴት እንደ ነበሩ ገልጸው የእርሳቸው ሰብዓዊ ገጽታ “በእዚያች አገር ውስጥ ያለውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ብለው ለእማሆይ ትሬዛ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ለመገንባት በእቅድ ላይ ላለው ቤተ መቅደስ የግንባታ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን እና በእዚያም የመታሰቢያ ጸሎት ማድረጋቸውንም ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ሰሜን መቀዶኒያ እና ወጣቶች

በሰሜን መቀዶኒያ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተ የተናገሩት ቅዱስነታቸው በሰሜን መቀዶኒያ ያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቀ የሚገኘውን “የተለያየ የዘርና የሃይማኖት ግንኙነቶችን ለማስተናገድ አገሪቷ ያላት ባሕላዊ የሆነ አቅም” ለማበረታታት አስበው እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ሰሜን መቀዶኒያ በጣም ብዙ የሆኑ ስደተኞችን እና የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማስተናገድ እና ለመርዳት ያላትን ቁርጠኛነት እንደ ሚያደንቁም ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ሰሜን መቀዶኒያ "ተቋማዊ በሆነ አግባብ ስንመለከታት ገና በጣም ወጣት የሆነች አገር ናት” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህም የተነሳ ከወጣቶች ጋር በእዚያ የነበራቸው ቆይታ እጅግ የሚያስደምም እና በጣም አስፈላጊ የሆነ ጉብኝት እንደ ነበረ ጨምረው ገልጸዋል። ከወጣቶች ጋር በነበራቸው ቆይታ ልክ እንደ እማሆይ ትሬዛ “ትልቅ የሆነ ሕልም እንዲያልሙ እና ያንን ሕልም እውን ለማድረግ እንዲሰሩ” ወጣቶቹን መምከራቸውን የገለጸት ቅዱስነታቸው “ወጣቶች በጸሎት አማካይነት የሚናገራቸውን የእግዚኣብሔርን ድምጽ ማዳመጥ የገባቸዋል፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለሚያቀርቡልን የእርዳታ ጥሪ መልስ መስጠት ይኖርባችኋል” ብለው መናገራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

08 May 2019, 10:50