ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ከመጸለያችን በፊት መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳን ራሳችንን ዝቅ ማደርግ ይገባል” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በግንቦት 07/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላያ በግንቦት 14/2011 ዓ.ም ያደረጉት የክፍል 16 የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና (ሮሜ 8፡15) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን  “ባለህበት ቦታ ሁሉ የእግዚኣብሔርን ስም ጥራ” በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ላይ ባተኮረው አስተምህሮዋቸው “ለመጸለይ ራሳችንን ዝቅ ማድረግ አለብን፣ ምክንያቱም ይህ ተግባራችን መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ እንዲመጣ እና በጸሎት እንዲመራን ያስችለዋልና” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 14/2011 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከዚህ ቀደም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረነው የነበረውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬ እናጠቃልላለን። የክርስቲያን ጸሎት የተወለደው በድፍረት እግዚኣብሔርን “አባት” ብለን ከመጥራት ይመነጫል። የክርስቲያን ጸሎት ሥር መሰረት እግዚኣብሔርን “አባት” ብሎ መጥርት ነው። ይህንን ለማድረግ ግን ብርታቱ ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ እኛ በልጅነት መንፈስ ካለን ቅርበት የተነሳ እርሱን እንናመስግነው ዘንድ መሰረታዊ በሆነ መልኩ የተሰጠን ቀመር አይደለም፣ አብን የገለጸልን ኢየሱስ በመሆኑ የተነሳ እርሱ የአብን ትክክለኛ ግንዛቤ ይሰጠናል። “ነገር ግን ኢየሱስ እንደ እንደፈልግነው የምንደግመው ቀመር አልሰጠንም። በማነኛውም በቃል በሚደረግ ጸሎት ውስጥ እንደ ሚታየው መንፈስ ቅዱስ የእግዚኣብሔር ልጆች አብን እንዲለምኑ የሚያስተምረው በቃለ እግዚኣብሔፍር አማካይነት ነው። ኢየሱስ የሰጠን ጸሎት በልጅነት መንፈስ የምናደርገውን ጸሎታችንን ቃላትን ብቻ ተጠቅመን እንድንጸልይ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ታግዘን እንድንጸልይ በሚያስችለን መልኩ ጭምር ነው።” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2766)። ኢየሱስ ወደ አብ ለመጸለይ የተለያዩ አገላለጾችን ተጠቅሟል። ቅዱስ ወንጌልን በጥንቃቄ ካነበብን ኢየሱሱ ጸሎት ባደረገባቸው ወቅቶች ሁሉ ከከንፈሮቹ የወጡት ቃላት የሚያንጸባርቁት “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ውስጥ የተገለጹትን መገለጫዎች ያስታውሱናል።

ለምሳሌም ኢየሱስ በምሽት “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ (ማርቆስ 14፡36) ብሎ በጌቴሴማኒ የጸለየው ጸሎት ከዚህ ሐሳብ ጋር ይገናኛል። ይህንን በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን የኢየሱስ ጸሎት እናስታውሳለን። በዚህ ጸሎት ውስጥ አጠር ባለ መልኩ የተቀመጠውን “አባ” የሚለውን ቅኝት እኛ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው? በጨለማው ውስጥ ሆኖ ኢየሱስ እግዚአብሔርን በልጅነት የመተማመን መንፈስ "አባ" ብሎ በመጥራት፣ ፍርሃትና ጭንቀት በሚሰማው በእዚያን ወቅት የእርሱ የአባቱ ፍቃድ እንዲፈጸም ይጠይቃል። በሌላ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ ደግሞ ኢየሱስ የጸሎትን መንፈስ እንዲያዳብሩ ደቀ-መዛሙርቱን አጥብቆ ይናገራቸዋል። አንድ ጸሎት በጣም አጥብቆ መጠየቅ የሚችል ጸሎት መሆን አለበት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በተለይ ከእኛ ጋር መልካም ያልሆነ ግንኙነት ያላቸውን ወንድሞች በማስታወስ መደረግ ይኖርበታል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ይለናል “እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም” (ማር 11፡25) በማለት ይናገራል። በእነዚህ መግለጫዎች ውስጥ የሚገኙ ቃላት "አባታችን ሆይ!" ከሚለው ጸሎት ውስጥ ጋር ያለውን ተመሳሳይነት ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ዓይነት መልኩ የተጠቀሱ ብዙ ምሳሌዎች አሉ።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፈው መልእክቱ ውስጥ "አባታችን ሆይ!” የሚለውን ቃል በቀጥታ የማናገኝ ቢሆንም ነገር ግን በሚገርም ሁኔታ ተጨባጭ በሆነ መልኩ በሚታይ ውህደት የክርስትያን ጸሎት መገለጫ ጥሪ የሆነውን “አባ” የሚለው ቃል እናገኛለን (ሮሜ 8፡15, ገላ 4፡6)።

በሉቃስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ደቀ-መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ኢየሱስ በጸሎት መንፈስ ውስጥ መግባቱ ከተመለከቱ በኋላ አንድ ቀን ደቀ-መዛሙርቱ ኢየሱስን ለመጠየቅ ወስነው “ጌታ ሆይ መጥመቁ ዮሐንስ የራሱን ደቀ-መዛሙርት እንዳስተማራቸው አንተም ጸሎት መጸለይ አስተምረን” (ሉቃ 11፡1) በማለት ላቀረቡለት ጥያቄ በተሙላ መልኩ ምላሽ ተሰጥቶዋቸዋል። በዚህ መልኩ ጌታ ደቀ-መዛሙርቱ ጸሎት እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባቸው ያስተምራቸዋል።

በአጠቃላይ አዲስ ኪዳንን ስንመለከት እያንዳንዱ የክርስትያን ጸሎት ዋነኛው ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ እንመለከታለን። በእያንዳንዱ የክርስትያን ጸሎት ውስጥ ዋነኛው ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን በፍጹም መርሳት አይኖርብንም። ያለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል መጸለይ በፍጹም አንችልም። በእኛ ውስጥ የሚጸልይ እና በደንብ እንድንጸልይ የሚያነሳሳን እርሱ ነው። እኛ በሚገባ መጸለይ እንችል ዘንድ እንዲረዳን መንፈስ ቅዱስን መጠየቅ እንችላለን፣ ምክንያቱም እርሱ በእኛ ውስጥ ሆኖ ትክክለኛ ጸሎት እንድናደርግ የሚመራን እና በእኛ ውስጥ የሚሰራ ዋነኛው ተዋናይ በመሆኑ የተነሳ ነው። በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት መሆናችንን የሚገልጽ እስትንፋስ በልባችን ውስጥ ያኖራል። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን፣ በእርግጥ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት የእግዚኣብሔር ልጆች እንድንሆን ያደረገን መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ባሳየን መስመር ውስጥ ብቻ ሆነን እንድንጸልይ ያደርገናል። እንግዲህ የክርስቲያን ጸሎት ምስጢር እዚህ ጋር ነው ያለው፡ በጸጋ ተሞልተን የቅድስት ሥላሴ ፍቅር ተካፋዮች በመሆን በእዚያ ውስጥ እንገባለን።

ኢየሱስ የጸለየውም በዚሁ ሁኔታ ነበር። ኢየሱስ በሚጸልይበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ በእርግጠኛነት “አባታችን ሆይ!” ከሚለው ጸሎት ጭብጥ በጣም የራቁ ጸሎቶችን ማድረጉ እርግጥ ነው። በመዝሙረ ዳዊ በምዕራፍ 22 ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰውንና “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” (ማቴ 27፡46) በማለት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይችላል። ሰማያዊ አባቱ ልጁን ትቶ መሄድ ይችላልን? በእርግጥ እንዲህ አያደርግም። ነገር ግን ለእኛ ለኃጢአተኞች ያለው ፍቅር ኢየሱስ እዚያ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፣ አባቱ ችላ ብሎኛል ብሎ እስኪሰማው ድረስ ተሰቃይቱዋል፣ አባቱ ከእርሱ በጣም ርቆ እንዳለ ሆኖ የተሰማው ስሜት አለ፣ ምክንያቱም የእኛን ኃጢአት ሁሉ እርሱ ተሸክሙዋልና። ነገር ግን በእዚያ ከፍተኛ በሆነ ስቃይ ውስጥ ሆኖ እንኳን “አምላኬ አምላኬ” ማለቱን አላቁረጠም ነበር። “አምላኬ” በሚለው ቃል ውስጥ በጥልቀት የሚገኝ እርሱ ከአባቱ ጋር ያለው ጥልቅ የሆነ የእምነት እና የጸሎት ትስስር እንመለከታለን።

ለዚህም ነው ከዚህ ጥልቅ ከሆነ ግንኙነት ተነስቶ አንድ ክርስቲያን በሁሉም ሁኔታ ውስጥ መጸለይ ይችላል የምንለው በዚሁ ምክንያት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይም ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የተጠቀሱትን ጸሎቶች ተጠቅመን መጸለይ እንችላለን። ለአባታችን ሰለወንድሞቻችን እና በአጠቃላይ ስለሰው ልጆች በተለይም ደግሞ ስለድሆች መጸለይ የሚገባን ሲሆን ማንም ሰው ቢሆን ያለ አጽናኝ እና ያለ ፍቅር ይኖር ዘንድ ተገቢ ባለመሆኑ የተነሳ ሁሉን አቀፍ የሆነ ጸሎት ለአባታችን ማቅረብ ይገባናል። በዚህ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማብቂያ ላይ ኢየሱስ ያለውን ቃል በድጋሚ በመጠቀም “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” (ሉቃ 10፡21) በማለት እንጸልይ። ለመጸለይ ራሳችንን ዝቅ ማድረግ አለብን፣ ምክንያቱም ይህ ተግባራችን መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ እንዲመጣ እና በጸሎት እንዲመራን ያስችለዋልና።

22 May 2019, 15:45