ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ደህንነት የምንገዛው ወይም የምንሸምተው ነገር ሳይሆን በነጻ የሚሰን ስጦታ ነው

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ቀደም ባሉት ጊዜያት  “አባታችን ሆይ !” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አገባደው በዛሬው እለት ማለትም በግንቦት 21/2011 ዓ.ም ላይ በአዲስ መልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የሐዋርያት ሥራ ላይ መሰረቱን ያደረገ የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማደርግ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን “ደህንነት የምንገዛው ወይም የምንሸምተው ነገር ሳይሆን በነጻ የሚሰጠን ስጦታ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 21/2011 ዓ.ም በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ በሚገኘው የሐዋርያት ሥራ ላይ ያደረጉትን የክፍል አንድ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የምናደርገውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንጀምራለን። በወንጌላዊው በቅዱስ ሉቃስ የተጻፈው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ አካል የሆነ መጽሐፍ ስለ ጉዞው ይናገራል፣ ነገር ግን ስለየተኛው ጉዞ ነው የሚናገረው? በአለም ውስጥ ቅዱስ ወንጌል ስለሚያደርገው ጉዞ እና በእግዚአብሔር ቃል እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን አስደናቂ ግንኙነት በመግለጽ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚጀመርበትን ጊዜ በይፋ ያበስራል። በሐዋርያት ሥራው ውስጥ ዋነኛው ተዋናዮች ሕያውና ውጤታማ የሆኑ "የማይነጣጠሉት" የእግዚኣብሔር ቃል እና መንፈስ ቅዱስ ናቸው።

እግዚአብሔር ወደ "ምድር ቃሉን ይልካል” "ቃሉም በፍጥነት ይሰራጫል" ይለናል ዳዊት በመዝሙሩ። የእግዚኣብሔር ቃል ፈጣን፣ ተራማጅ እና የወደቀበትን መሬት ሁሉ የሚያረሰርስ ነው። ታዲያ ይህንን ጥንካሬ ያገኘው ከየት ነው? ቅዱስ ሉቃስ እንደሚነግረን የሰዎች ቃል ውጤታም ሊሆን የሚችለው ባላቸው የመናገር ብቃት ሳይሆን የእግዚኣብሔር ተራማጅነት፣ የእግዚአብሔር ኃይል፣ ቃሉን ሰምተው በደስታ እንዲቀበሉ በሚያደርገው በእግዚኣብሔር ኃይል እርዳታ እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እና ጸጋ መሆኑን ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪኮች እና የሰው ቃላቶች ይገኛሉ፣ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ እና በታሪክ መጽሐፍ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ቃላት በጣም ታላቅ የሆነ ኃይል እንዲኖራቸው፣ የተለያየ ዓይነት ኃይል እንዲጎናጸፉ ያደረጋቸው፣ ያ ቃል የቅድስና ምንጭ፣ የሕይወት መፍለቂያ እና ፍሬያማ እንዲሆን የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ የሰውን ቃል ሲጎበኝ ያ ቃል ኃይለኛ የሆነ ጥንካሬን በማግኘት “እንደ ድማሚት” ይሆናል፣ ይህም በሰዎች ልብ ውስጥ እሳት ለማቀጣጠል እና ከፋፋይ ስርዓቶችን፣ ተቃውሞዎችን እና የሚለያዩንን ግድግዳዎችን ዘለን እንድናልፍ በማድረግ አዲስ መንገዶች ለመክፈት እና የእግዚአብሔር ህዝብ ድንበሮችን ለማስፋፋት እንድንነሳሳ ያደርገናል። ይህንን ሂደት በተመለከተ አሁን በዚህ በሐዋርያት ሥራ ላይ የጀመርነውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በጥልቀት በምንመለከትበት ጊዜ የምንመለስበት ጉዳይ ይሆናል።

ለእኛ ብርቅዬ የሆነ ቃል የሚሰጠን እና ደካማ ለሆነ ሰብዓዊ ቃላችን ጥንካሬ እንዲኖረው የሚያደርገው ከተሰጠን ኃላፊነት እንድንሸሽ ሳይሆን የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ እንድንወጣ የሚያስችል ብቃት የሚሰጠን፣ የእግዚኣብሔር ልጅ በእርሱ አማካይነት ከሰው እንዲወለድ ያደርገው መንፈስ ቅዱስ፣ የቀባው እና ተልዕኮውን በሚገባ እንዲወጣ የረዳው መንፈስ ቅዱስ፣ ሐዋርያቱን እንዲመርጥ እና ተልዕኮዋቸው በብርታት እንዲወጡ እና ፍሬያማ እንዲሆኑ ያደርገው፣ አሁንም ቢሆን በእኛ ተልዕኮ ውስጥ አለኝታነቱን በማረጋገጥ ላይ ያለው መንፈስ ቅዱስ ነው።

የቅዱስ ወንጌል ታሪክ የሚደመደመው በኢየሱስ ትንሣኤና ዕርገት ላይ ሲሆን የሐዋሪያት ሥራ ደግሞ መልእክቱን የሚጀምረው በሐዋርያት አገልግሎት ላይ መሰረቱን በማድረግ ነው፣ በዚህም ተግባራቸው በቤተክርስትያን ውስጥ የሚገኘውን እና ከሙታን የተነሳው የሕይወት ጌታ ለየት ባለ መልኩ መመስከር መጀመራቸውን በመግለጽ ነው። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደ ገለጸው “ከሕማማቱም በኋላ ራሱ ቀርቦ ሕያው መሆኑን፣ ለእነዚሁ በብዙ ማስረጃ እያረጋገጠላቸው አርባ ቀንም ዐልፎ ዐልፎ እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው » (የሐዋ 1፡3) በማለት ይናገራል። ከሞት የተነሳው ክርስቶስ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፣ ምግብ ከሐዋርያቶቹ ጋር በመጋራት፣ ሰብዓዊ አካላዊ መገለጫዎችን በመጠቀም እና የአብ የተስፋ ቃል ፍፃሜዎች እንደ ሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ እምነት እንዲኖራቸው በመጋበዝ "በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ" (ሐዋ 1 5) በማለት ተናግሮዋቸው ነበር።

በእውነቱ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት ውስጥ እንድንገባ እና በእርሱ ዓለምን የማዳን የደህንነት እቅድ ውስጥ እንድንሳተፍ በማድረግ፣ የእርሱን ጸጋ በመስጠት ቃሉን “በልጅነት መንፈስ” በብርታት ለማወጅ እንችል ዘንድ ኃይሉን በማጎናጸፍ፣ የሰው ልጆች ብቻ ሳንሆን የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን ጭምር እንድንረዳ በማደረግ፣ ግልጽ የሆነ፣ ነጻ፣ ውጤታማ፣ ለክርስቶስና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር በምልአት የምንገልጸበት ቃል ማወጅ እንችል ዘንድ ይረዳናል።

ስለዚህም የእግዚአብሔርን ስጦታ ለማግኘት ወይም ለመቀበል ትግል ማድረግ አያስፈልግም። ሁሉም ነገር በጊዜው እና በነፃ ይሰጠናል። ጌታ ሁሉንም ነገር በነጻ ነው የሚሰጠን። ደህንነት አይገዛም፣ አይሸጥምም፣ በነጻ የሚሰጠን ጸጋ ነው። እርሱ አስቀድሞ የተናገራቸው ክስተቶች እንደሚፈጸሙ ለማወቅ በማሰብ አስቀድሞ ከመጠን በላይ ለነበራቸው ጭንቀት ኢየሱስ ራሱ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜ ወይም ወቅት ማወቁ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ » (የሐዋ 1፡7-8) በማለት ራሱ መልስ ይሰጣል።

ከሞት የተነሳው ጌታ የራሱ የሆኑትን ደቀመዛሙርቱ በጭንቀት ውስጥ ሆነው እንዲኖሩ ሳይሆን ነገር ግን በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚጣጣም ነገሮችን በመፈጸም አዲስ ቅዱስ የሆነ ታሪክ እንደ ሚፈጸም በማመን እንዲጠባበቁ እና ሁልጊዜም ወደ ፊት እንዲጓዙ፣ በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚገለጹትን የእግዚኣብሔር እርማጃዎች እንዴት ማወቅ እና መጠበቅ እንደ ሚገባቸው እንዲያውቁ ይጋብዛቸዋል። ከሙታን የተነሳው ጌታ የእርሱ የሆኑ ደቀመዛሙርቱ የራሳቸው የግላቸው የሆነ ተልዕኮ እንዳይፈጥሩ ጥሪ በማድረግ ነገር ግን አብ በሚሰጣቸው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት ልባቸው እንዲመራ በመፍቀድ በኢየሩሳሌም እና በሰማርያ በመዘዋወር እርሱ የሰጣቸውን ተልዕኮ ከእስራኤል ጀምሮ እስከ ዓለም ዳርቻዎች ድረስ የእርሱን ቃል እንዲያዳርሱ ጥሪ ያደርግላቸዋል።

ሐዋርያቱ ይህንን ተስፋ በመጠባበቅ በጋር እና በኅበረት ሆነው እንደ አንድ የጌታ ቤተሰብ በመሆን በላይኛው ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ኢየሱስ በቅዱስ ቁርባን አማካይነት የሰጣቸውን ጸጋ ለመመስከር ኃይል የሚሰጣቸውን ጸጋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ይህንንም ጸጋ እየተጠባበቁ የነበሩት በጽናት በመጸለይ ሲሆን እንደ ብዙ ሰው ሳይሆን እንደ አንድ ሰው በመሆን በጋራ ይጸልዩ ነበር። በኅበረት እና በጽናት ይጸልዩ ነበር። በጸሎት አማካይነት የብቸኝነት መንፈስን ማሸነፍ ይቻላል። በጸሎት አማካይነት የብቸኝነት መንፈስ፣ ፈተና፣ የጥርጣሬ መንፈስ ይሸነፋል የልብ አንድነት የፈጠራል። በእነርሱ መካከል የሴቶች እና እንዲሁም የኢየሱስ እናት የሆነችው የማርያም መገኘት ደግሞ ይህ ተስፋቸው በተገቢው ሁኔታ እንዲለመልም ያግዛቸዋል፣ እነርሱ በቅድሚያ የፍቅር መግለጫ እና የፍቅር ጥንካሬን እንዲሁም ፍርሃቶችን በሙሉ ማሸነፍ የሚችል የኅበረት ኃይል አስፈላጊ መሆኑን በቅድሚያ ከጌታ ተምረዋልና።

ጌታ የእርሱን ሂደት በትዕግስት መጠባበቅ እንችል ዘንድ እንዲረዳን፣ የእርሱ ሥራዎች ፈጣሪ እንዳንሆን እንዲረዳ፣ ለጸሎት ታማኝ ሆነን እንኖር ዘንድ እንዲረዳን፣ በወስጣችን ያለውን መንፈስ ቅዱስ መኮትኮት ወይም መንከባከብ እንችል ዘንድ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ኅበረት አምጭዎች እንሆን ዘንድ እንዲረዳን ልንጠይቀው ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 May 2019, 16:43