ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ ተቋም ማኅበር አባላት ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ ተቋም ማኅበር አባላት ጋር  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “አግላይ የሆነ ከፍተኛ የብሔራዊ ስሜት አደጋ ሊያስከትል ይችላል” አሉ።

የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት አካዳሚ የተሰኘው ጳጳሳዊ ተቋም እ.አ.አ በጥር 1/1994 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 264ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በዩሐንስ ጳውሎስ 2ኛ የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ዋና መቀመጫው ደግሞ በቫቲካን ግዛት ውስጥ ነው። ይህ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት አካዳሚ ጳጳሳዊ ተቋም የተቋቋመበት ዋናው ዓላማ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሕጋዊ፣ የማኅበራዊ እና እንዲሁም የፖለቲካዊ ሳይንስ አስተምህሮዎችን በጥልቀት በመመርመር ለቤተ ክርስቲያኗ ማኅበራዊ አስተምህሮ ተስማሚ በሆነ መልኩ የማቅረብ ተልዕኮ የተሰጠው ጳጳሳዊ ተቋም ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በየወቅቱ እንደ አስፈላጊነቱ የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብሩ እንዲጠበቅ፣ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲኖር፣ ኅብረት እና መደጋገፍ የተሰኙትን አራቱን መሰረታዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የማኅበራዊ አስተምህሮ መርሆችን ተገቢ እና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለማቅረብ ያሳችላት ዘንድ ድጋፍ የሚያደርግ ተልዕኮ የተሰጠው ጳጳሳዊ ተቋም ነው።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የዚህ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት አካዳሚ ጳጳሳዊ ተቋም አባላት እ.አ.አ ከግንቦት 1-3/2019 ዓ.ም ድረስ “አገር፣ መንግሥት፣ አገር እና መንግሥት” በተሰኙ ጭብጦች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ ጉባሄ እያደርጉ እንደ ሚገኙ ከስፍራው ለቫቲካን ዜና ከደርሰው ዘገብ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በትላንትናው እለት ማለትም በሚያዝያ 24/2011 ዓ.ም የማኅበሩ አባላት በቫቲካን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር መገናኘታቸውን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት “በብሔራዊ ስሜት የተነሳ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄዱ የሚገኙትን ግጭቶች እና የጅምላ ጨረሽ የሆኑ የኒውክለር የጦር መሳሪያዎችን ላይ ትኩረት ያደርገ ንግግር ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ እየታየ የሚገኘው የብሔራዊ ስሜት አደጋ ሊያስከትል ይችላል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐሙስ ሚያዝያ 24/2011 ዓ.ም ለዚህ ጳጳሳዊ ተቋም ያደርጉት ንግግር በውጭ አገር ዜጎች፣ በተለይም በስደተኞች እና በአሁኑ ወቅት የጋራ ተጠቃሚነትን ችላ ባለ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ እየተነጸባረቀ እና ብዙሃኑ በማራመድ እና በመገንባት ላይ በሚገኙት አግላይ የብሔራዊ ስሜት የተነሳ እየተከሰቱ የሚገኙ ግጭቶች እንደ ሚያሳዝናቸው ገልጸው እንዲህ ዓይነቶቹ አዝማሚያዎች ዓለም አቀፋዊ ትብብርን፣ እርስ በእርስ የመከባበርን እና በአጠቃላይ የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት የልማት ግቦችን የሚቃወሙ ተግባራት መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በቫቲካን ለተገኙት ከ 50 በላይ የተቋሙ አባላት ቅዱስነታቸው ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት ከዚህ ቀደም የጅምላ ጨራሽ የሆነው የኒውክለር የጦር መሳሪያ ይወገድ ዘንድ የተደረጉ ስምምነቶች በሁኑ ወቅት በአዲስ መልክ ስምምነቱ አደጋ ላይ መውደቁ እንደ አሳሰባቸው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ስደት እና አግላይ በሆኑ ብሔራዊ ስሜት የተነሳ የሚከሰቱ ግጭቶች

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ጨምረው እንደ ገለጹት እያንዳንዱ ሰው ሕዝቡን እና የገዛ አገሩን ጭምር፣ የሌላ አገር ሰዎችን ባሕል፣ ወግ እና ልምድ ከግምት ባስገባ መልኩ መውደድ እንደ ሚገባቸው ቤተ ተክርስቲያን አጥብቃ እንደ ምታስተምር የገለጹ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ከፍተኛ በሆነ ብሔራዊ ስሜት ተነሳስቶ እና ይህ ስሜት መልኩን ቀይሮ "ከዚህ ከፍተኛ ከሆነ ብሔራዊ ስሜት በመነሳት በጥላቻ መንፈስ ተነሳስቶ ግንብ መገንባት፣ ዘረኝነትን ማካሄድ እና  ፀረ-ሴማዊነትን የሆኑ” ተግባራትን መፈጸም ግን ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በአብዛኛው በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የበላይ የሆነ ቡድኖች ኢኮኖሚያዊ ትርፎችን ለማጋበስ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የሌሎቹን አናሳ ቁጥር ያላቸውን በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የጎሳ፣ የቋንቋ ወይም የሃይማኖት ቡድኖች ላይ ጭቆና እንደ ሚፈጽሙባቸው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸው በተቃራኒው ደግሞ አንድ አገር ስደተኞችን የሚቀበልበት መንገድ ያ አገር ለሰብአዊ ክብር እና ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ራዕይን ያሳያል ብለዋል።

የገዛ አገራቸውን አስገዳጅ በሆነ መልኩ ጥሎው የሚሰደዱትን ሰዎች ወይም ቤተሰቦች መቀበል ሰብዓዊ የሆነ ተግባር ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህ ረገድ እርሳቸው ብዙን ጊዜ ይህንን የስደተኞች ጉዳይ በተመለከተ በሚያደርጉዋቸው ንግግሮች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀሙባቸውን እና አንድ ስደተኛን መቀበል፣ መንከባከብ፣ ማስተዋወቅ እና ማዋሃድ የሚሉት አራት ቃላት በድጋሚ መጠቀማቸው ተገልጹዋል።

አንድ ስደተኛ ለተቀበለው ሀገር ባህልን፣ ወግን እና እሴቶችን ስጋት ላይ የሚጥል አለመሆኑን አጽኖት ሰጥተው የገለጹት ቅዱስነታቸው በተቃራኒው ደግሞ ስደተኛው ከተቀበለው ሀገር ማኅበረሰብ ጋር ራሱን ማዋሃድ እና ጥምረት የመፍጠር ኅላፊነት እንዳለበት ጨምረው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጨምረው እንደ ገለጹት ስደት የሰው ልጅ ታሪክ ቋሚ ገፅታ ነው፣ እናም ሁሉም ሀገራት የተለያየ ተከታታይነት ያለው የሰዎች ዝውውር ውጤት ናቸው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን የተለያየ የሰዎች ስብዕና የጋራ በሆኑ እሴቶች አማካይነት መዋሃዳቸውን ገልጸው ይህም ባሕልን የሚያዳብር እና በተለይም ጠቃሚ የሆኑ ልምዶች እንዲበለጽጉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

“ሌሎችን አጋልይ የሆነ ብሔራዊ ስሜት በሕዝቡ መካከል እንዲጎለብት የሚያደርጉ መንግሥታ እና ይህንን አግላይ የሆነ ብሔራዊ ስሜት በመከተል የሚያንጸባርቁ ሰዎች ወይም ቡድኖች” እንዲህ ዓይነቱ ልዩነት እና አካሄድ ወደ የት እንደሚያመራ እና ምን ዓይነት ውጤት እንደ ሚያስከትል ከታሪክ መማር የገባል በማለት አሳስበዋል።

አገርን እና መንግሥትን በተመለከተ የተናገሩት ቅዱስነታቸው አንድ አገር እና መንግሥት ራሱን ፍጹም አድርጎ እና ራሱን እንደ አንድ ደሴት አድርጎ በመቁጠር ራሱን በራሱ ሙሉ እንደ ሆነ አድርጎ በመውሰድ ከሌሎች የከባቢ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያቋርጥ ከሆነ፣ የገዛ አገሩን ሰዎች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አይችልም፣ በተጨማሪም አሁን በከፍተኛ ሁኔታ በመታየት ላይ የሚገኘውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮት ማስወገድ፣ ዘመናዊ ባርነትን መዋጋት  እና እንዲሁም ሰላምን ማረጋገጥ አይችልም ብለዋል።

በአገሮች መካከል ያለው የጋራ ትብብር ብሔራዊ የሆነ ስሜትን ብቻ ከመቀስቀስ እና በሌሎች ላይ የበላይ ለመሆን በማሰብ ከሚረቀቁት ፖሊሲዎች በተቅራኒው ጎራ በመሰለፍ በአዲስ መልክ ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ ዓለማቀፋዊ ትብብርን በሚያጠንካር መልኩ ትብብር ማካሄድ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በአጽኖት ገልጸዋል።

ሰብአዊነት በሀገሮች መካከል ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ በጦር መሣሪያ የተደገፈ ግጭቶችን መጠቀምን በማስወገድ ይከላከላል፣ እንዲሁም ኃያላን የተባሉት አገራት አደገኛ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦችን በሌሎች ላይ እንዳይጭኑ እና እጅግ በጣም ብርቱ የሆኑት ደግሞ በደካሞች ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ፣ የብሔራዊ እና ክልላዊ ገጽታዎችን በማይቀንስ መልኩ ጉዳዮችን ዓለማቀፍ በሆነ መልኩ መመልከት እንዲችሉ እንደ ሚረዳ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ልዩነቶችን አንድ ለማድረግ በሚጥረው እና የአገር በቀል ስሜትን አፍኖ የሚየዘውን ዓለማቀፋዊነትን (ግሎባላይዜሽን) በመቃወማቸው የተነሳ የብሔራዊ ስሜት መንፈስን በሰፊው በማራመድ እና አንድ አገር ሌላውን ለመቆጣጠር በማሰብ የሚያወጧዋቸውን ፖሊሲዎችን የሚቃወሙ አገራት ቁጥር እየበዛ መምጣቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው ዓለማቀፋዊ “ብዝሃነትን” በሚገልጽ መልኩ እና በእያንዳንዱ ህዝብ እና የጋራ ማንነት መካከል የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተና "ሁሉን አቀፍ" የሆነ ዓለም አቀፋዊ ስርዓት መዘርጋት ተገቢ እንደ ሆነ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ይህም ዓለማችን አጠቃላይ ወደ ሆነ ሰላምና ኅብረት ውስጥ ለመግባት ያስችላታል ብለዋል።

ዓለማቀፋዊ “ብዝሃነትን” የሚያራምዱ አካላት የበቀልን፣ የበላይነትን፣ የጭቆናን እና የግጭትን መንፈስ በውይይት ፣ በመግባባት፣ በስምምነት፣ በኅብረት በመተካት አንድ የጋራ መኖሪያ ያለን አንድ ዓይነት ሰብአዊ ፍጡር መሆናችንን እንድንገነዘብ በማድረግ ተስፋን በመፈንጠቅ ላይ እንደ ሚገኙ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን ራዕይ እና ሐሳቦች በሌሎች ላይ ለመጫን እና በራሳቸው የርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛት ሥር ለማስገባት ጠንክረው በመሥራት ላይ የሚገኙ እና ይህንን ሐሳባቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን ደፋ ቀና በማለት ላይ የሚገኙ ተጽኖ ፈጣሪ ኃይሎች እና ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ቡድኖች ብዙውን ጊዜ እነርሱን የሚመለከቱ ሕዝቦችን ማንነት፣ ባሕል እና ወግ እንዲሁም ክብር እና ስሜት ሲጠብቁ አይታዩም ብለዋል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ዝንባሌዎች ብቅ ማለት የብዝሃነትን ሥርዓት በማዳከም ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ስርዓት ታማኝነት የጎደለው እንዲሆን በማድረግ እና የዓለም አቀፉ ቤተሰብ አካል የሆኑትን በጣም ተጋላጭ የሆኑትን የማኅበርሰብ ክፍሎች የማግለል ደረጃ ላይ የሚደርስ ውጤት ያስከትላል ብለዋል።

“ቀደም ሲል ብዙዎቹን ባሳተፈ መልኩ የተደርጉት የኒውክለር የጦር መሥራያዎችን ማስወገድ የሚያስችሉ ስምምነቶች ዛሬ ጊዜ እያለፈባቸው እና ከእንግዲህ ወዲህ የአቶሚክ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቁ ኃይሎች ፖለቲካዊ ሐስተሳሰባቸውን እየቀየሩ በስምምነቱ ተገዢ ላለመሆን እያቅማሙ መሆናቸውን” በስጋት የገለጹት ቅዱስነታቸው በተቃራኒው የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን ለመታጠቅ ሩጫው በአዲስ መልክ ተጧጡፎ በቀጠለበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለው ይህም ተግባር ባለፉት እና አሁን ባለው ጊዜ ሳይቀር የተደረጉትን ስምምነቶች በማፍረስ ከፍተኛ የሆነ የጦርነት ሥጋት ፈጥሩዋል ብለዋል። የኒውክለር የጦር መሣርያ እና መከላከያው በምድራችን ገጽ ላይ እና እንዲሁም በሕዋ ላይ መተከል ከጀመረ በዚህ ረገድ አዳዲስ የዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ ቡድኖች ብቅ ማለት በመጀመር የኑክሌር የጦር መሣሪያ እልቂት አደጋን ከፍ እንደ ሚያደርገው ቅዱስነታቸው ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለዚሁ የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ ተቋም ማኅበር አባላት ባደረጉት ንግግር ማብቂያ ላይ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ሰብአዊ ክብርን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ለምድራችን ክብር እንዲሰጣት እና የላቀ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ አዲስ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ለመፍጠር የሚደረገውን የግንዛቤ አሰጣጥ ሂደት ለማሰራጨት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

03 May 2019, 16:59