ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የኢየሱስ ፍቅር የተስፋ አድማስ ከፍቶልናል” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 11/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ከዮሐንስ 13፡31-35 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ባደረገ አስተንትኖ እንደ ገለጹት “የኢየሱስ ፍቅር የተስፋ አድማስ ይከፍትልናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 11/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን ።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ መካራ ከመቀበሉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ባደረገው “የስንብት ንግግር” ውስጥ የተጠቀሱትን አንዳንድ ቃላት እንድንሰማ ያደርገናል። የደቀ-መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ዩሐንስ 13፡31-34) በማለት ይነግራቸዋል። ታዲያ ኢየሱስ ይህንን ትዕዛዝ “አዲስ” ያለበት ምክንያት ምንድነው? አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ባልንጀራዎቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው እንዲወዱ ትዕዛዝ ሰጥቶዋቸው (ዘለዋዊያን 19፡18) እንደ ነበር ስለምናውቅ የእዚህ ትዕዛዝ አዲስነት ምኑ ላይ ነው? ኢየሱስ ራሱ “ከሕጎች ሁሉ የሚበልጠው ትዕዛዝ የቱ ነው?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ ከሁሉም የሚበልጠው የመጀመሪያው ትዕዛዝ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ መውደድ እና ሁለተኛው ደግሞ “ባልንጀራዎቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን መውደድ” ነው በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር (ማቴ 22፡38-39)።

ስለዚህ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በአደራ የሰጠው ይህ “አዲስ” የተባለው ትዕዛዝ አዲስነቱ ምኑ ላይ ነው? ልምንድነው እሱ “አዲስ ትዕዛዝ” በማለት የሰየመው? አዲስነቱስ ምኑ ላይ ነው? ከጥንት ጊዜ ጀመሮ የነበረው የፍቅር ትዕዛዝ አዲስ ሆኖ ምልአትን ያገኘበት ምክንያት "እኔ እንደ ወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ቃላት ስለተጨመረበት ነው። ይህ ትዕዛዝ አዲስ የሆነበት ምክንያት ለእኛ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስለተጨመረበት ነው። ይህ አዲስ ትዕዛዝ ሁለንተናዊ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ያለምንም ገደብ የተሰጠ እና ይህም በመስቀል ላይ የተረጋገጠውን የእግዚአብሔር ፍቅር የሚያመልክት ነው። በዚያን ጊዜ እጅግ በጣም ትሁት በሆነበት ወቅት፣ ራሱን ለአባቱ በአደራ በሰጠበት ወቅት የእግዚአብሔር ልጅ ሙላት ያለው ፍቅር ለዓለም ሰጥቷል። ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ህማማት እና ስቃይ መለስ ብለው ሲያስቡ "እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” የሚለውን የእርሱን ቃላት ትርጉም ተረድተዋል።

አስቀድሞ የወደደን ኢየሱስ ራሱ ነበር፣ ከእነድክመቶቻችን፣ ከሰብዓዊ ውድቀቶቻችን እና ውስንነታችን ጭምር ይወደናል። እሱ ምንም ገደብ የሌለውን እና ፈጽሞ የማያልቀውን ፍቅሩን እንድናውቅ ያደርገን እርሱ ነበር። አዲስ ትዕዛዝ በመስጠት እኛ እርስ በርሳችን በራሳችን ፍቅር ሳይሆን እርሱ በመንፈስ ቅዱስ እና በእምነት አማካይነት በልባችን ውስጥ ባሰረጸው ፍቅር አማካይነት እንድንዋደድ ይፈልጋል። በዚህ መንገድ እና በዚህ ሁኔታ ብቻ: እኛ ራሳችንን በምንወድበት መንገድ ሳይሆን ነገር ግን እርሱ በወደደን ዓይነት ፍቅር እጅግ አድርገን እንድንዋደድ ይጋብዘናል። በእርግጥ እኛ ለራሳችን ካለን ፍቅር እጅግ በጣም በላቀ መልኩ እግዚኣብሔር እኛን ይወደናል። እናም በሰዎች መካከል ግንኙነቶችን የሚያድስ እና የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ የፍቅር ዘርን በየቦታው መዝራት እና ማሰራጨት እንችላለን። ኢየሱስ የተስፋ አድማሶችን ሁሉ ይከፍታል፣ የእርሱ ፍቅር የተስፋ አድማስ ይከፍታል። ይህ ፍቅር በጌታ አዲስ ሰዎች እንድንሆን ያደርጋል፣ በጌታ ስም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች እንድንሆን በማድረግ እኛ ሁላችን ክርስቶስን እንድንወድ እና ብሎም እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ያደርገናል፣ የቤተክርስቲያን አባላት እንድንሆን በማድረግ  አዲስ የእግዚኣብሔር ሕዝብ እንድንሆን ያደርገናል።

ይህ ፍቅር በጌታ አዲስ ሰዎች እንድንሆን ያደርገናል፣ በጌታ ወንድማማቾች እና እህታማማቾች እንድንሆን በማድረግ እኛ ሁላችን ክርስቶስን እንድንወደው እና እርስ በራስ እንድንዋደድ በመጥራት የእግዚአብሄር አዲሱ ሕዝብ ማለትም የቤተክርስቲያን አባል እንድንሆን ያደርገናል።

በክርስቶስ መስቀል ላይ የተገለጠው ፍቅር እና አዲስ ህይወት እንድንኖር የሚፈልገው ፍቅር በውስጣችን የሚገኘውን የድንጋዩን ልብ ወደ ሥጋ ልብ መቀየር የሚችል ብቸኛው ኃይል ነው፣ ልባችንን ለመለወጥ የሚችለው ብቸኛው ኃይል ያለው የክርስቶስ ፍቅር ነው፣ እኛም እርስ በእርሳችን መዋደድ የምንችለው በዚሁ ፍቅር አማካይነት ብቻ ነው። ጠላቶቻችንን እንድንወድ እና ለበደሉን ሰዎች ደግሞ ይቅርታ ማደርግ የሚያስችለንን ኃይል የሚሰጠን ይህ የክርስቶስ ፍቅር ብቻ ነው። አንድ ጥያቄ ለሁላችሁም ላቅርብላችሁ፣ መልሱን ግን ሁላችም በልባችሁ ውስጥ ብቻ መልሱት። ጠላቶቼን የመውደድ አቅም አለኝ ወይ? እያንዳንዳችን የማንወዳቸው ወይም ደግሞ የማንግባባቸው ሰዎች ሊኖሩን ይችላሉ፣ ወይም ደግሞ በእኛ ላይ መጥፎ የሆነ ነገር የፈጸሙብን ሰዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎችን የመውደድ ችሎታው አለን ወይ? በእኛ ላይ ክፉ ነገር የፈጸሙብን ወይም በደል ያደረሱብንን ሰዎች የመውደድ ችሎታ አለን ወይ? እደነዚህ ዓይነቱን ሰዎች ይቅር የማለት ችሎታ አለን ወይ? መልሱን እያንዳንዳችሁ በልባችሁ ውስጥ መልሱ። የኢየሱስ ፍቅር ሌላውም ሰው የኢየሱስ ማኅበርሰብ አባል እንደ ሆነ አድርገን እንድንመለከት ያደርገናል፣ እርስ በእርሳችን እንድንነጋገር ያደርገናል፣ እንድንደማመጥ ያደርገናል፣ እርስ በእርሳችን በሚገባ እንድንተዋወቅ ያደርገናል። ፍቅር ለሌላኛው ወገን ክፍት እንድንሆን በማድረግ የሰዎች ግንኙነት መሰረት ነው። ድክመቶቻችንንና ጭፍን ጥላቻዎቻችንን መሰናክሎችን ማሸነፍ እንድንችል ያደርገናል። በእኛ ውስጥ ያለው የኢየሱስ ፍቅር ድልድዮችን ይፈጥራል፣ አዳዲስ መንገዶችን ያስተምረናል፣ የወንድማማችነትን መንፈስ ያጠናክራል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነት አማላጅነቷ ልጁ ኢየሱስ የሰጠንን አዲሱን ትዕዛዝ መቀበል እንችል ዘንድ እና በየቀኑ በህይወታችን በመለማመድ ጥንካሬን ከመንፈስ ቅዱስ ማግኘት እንችል ዘንድ በአማላጅነቷ እርሷ ትርዳን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 May 2019, 18:10