ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክፉ መንፈስ በአደገኛ አንበሳን ይመሰላል፣ ኢየሱስ ግን በኃይሉ ነፃ ያወጣናል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በግንቦት 07/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላያ በግንቦት 07/2011 ዓ.ም ያደረጉት የክፍል 15 የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው “ከክፉ ሁሉ አድነን” በሚለው የመማጸኛ የጸሎት ዓረፍተ ነገር ላይ እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል። በወቅት ቅዱስነታቸው በዚህ “ከክፉ ሁሉ አድነን” በሚለው የመማጸኛ ጸሎት ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ “ክፉ መንፈስ በአደገኛ አንበሳ ይመሰላል፣ ኢየሱስ ግን ከዚህ ከክፉ ነገሮች ውስጥ በኃይሉ ነፃ ያወጣናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 07/2011 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በመጨረሻም "አባታችን ሆይ" በሚለው ጸሎት ውስጥ ወደ ሚገኘውና “ከክፉ ሁሉ አድነን" (ማቴ 6፡13) ወደ ሚለው ሰባተኛው የመማጸኛ ጸሎት ላይ ደርሰናል።

ይህንን አገላለጽ በመጠቀም የሚጸልይ ሰው ወደ ፈተና እንዳይገባ ከመጸለዩም ባሻገር ከክፉ ነገር እንዲያድነውም ጭምር ይማጸናል። ይህ ጸሎት በመጀመሪያ ደረጃ በተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ ቃል አገላለጽ በጣም ጠንካራ የሆነ ቃል ነው ---እኛን ለማጥቃት እና እኛን ለማድከም ከሚንቀሳቀስ ክፉ ነገር እግዚአብሔር እንዲያድነን መጠየቃችንን የሚያመለክት ነው።

ከዚህ የክርስትያን ጸሎት መሰረታዊ ባህርይ ይፈልቃል፣ እነዚህም "እኛን አትተወን" እና "አድነን" የሚሉ  ሁለት መማጸኛዎች ይቀርባሉ። ኢየሱስ ሁሉንም ነገር በተለይም ክፉ እና አስፈሪ የሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደ ገባን በሚሰማን ጊዜ ጓደኞቹ ሁሉንም ነገር በአብ ፊት በማቅረብ እንዲጸልዩ አስተምሩዋቸኋል። በእርግጥ የክርስትያን ጸሎት ህይወትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዓይኖቹን አይጨፍንም። በልጅነት መንፈስ የሚደረግ ጸሎት እንጂ የሕጻናት ጸሎት አይደለም። እግዚአብሔር አባት በመሆኑ የተነሳ እኛ እንደ ሕጻናት ተቆጥረን የሰዎች መንገድ በችግር የተሞላ መሆኑን መዘንጋት ማለት አይደለም። “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ማብቂያ ላይ የተጠቀሱት የመማጸኛ ጸሎቶች ባይኖሩ ኖሮ ኃጢያተኞች፣ በስደት ላይ የሚገኙ ሰዎች፣ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች፣ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ሰዎች ይህንን ጸሎት እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባቸው ሊረዱ ይችላሉ ወይ?

በሕይወታችን ውስጥ የማይጨበጥ አንድ ክፉ ነገር አለ። እኛ ከተፈጠርንበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬው እለት ድረስ በሕይወት ሂደት ውስጥ ብዙ ውድቀቶች እንደ ነበሩብን የታሪክ መጸሐፍት ያሳያሉ። አንድ ምስጢራዊ የሆነ ክፉ ነገር አለ፣ እሱም በእርግጠኛነት የእግዚአብሄር ሥራ አይደለም፣ ነገር ግን በታሪክ ቁስሎች ውስጥ ዘልቆ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ በእርሱ የምንወሰድ ይመስለናል፡ በተወሰኑ ጊዜያት ደግሞ የዚህ ክፉ መንፈስ መገኘት ከእግዚአብሔር ምህረት የበለጠ የገዘፈ ይመስለናል።

የሚጸልይ ሰው ዓይነ ስውር አይደለም፣ በፊትለፊቱ የተደቀነውን ከእግዚኣብሔር ምስጢር ተቃራኒ የሆነውን እና እኛን ጠቅልሎ ሊይዘን የሚፈልገውን ክፉ ነገር በግልጽ ይመለከታል። በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በልቡ ውስጥ እንኳን ያ ክፉ ነገር እንዳለ ይመለከታል። ምክንያቱም ከእኛ መካከል ማንም ሰው ራሱን ከክፉ ነገር ነጻ አድርጎ የሚቆጥር ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ፈተና አልገጠመኝም ብሎ ሊናገር የሚችል ማንም ሰው የለም።

“አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘው የመጨረሻው መማጸኛ “ከመስመራችን ውስጥ ወጥተን” በእርሱ በክፉ መንፈስ የተለያየ ዓይነት ልምዶች ውስጥ እንድንገባ፣ ሰዎች በሐዘን ውስጥ እንዲገቡ፣ ንጹዕን እንዲሰቃዩ፣ በባርነት ቀንበር ውስጥ እንዲገቡ፣ ሌሎች ሰዎችን እንድንበዘብዝ ከሚያደርጉ፣ ንጹዕን ሕጻናት በእንባ እንዲታጠቡ ከሚያድርገው ክፉ ነገር ጥላ ሥር ውስጥ እንዳንወድቅ እንዲረዳን የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት ነው። እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በሰዎች ልብ ውስጥ ይንጸባረቃሉ፣ እንግዲህ በዚህ ኢየሱስ ባስተማረን ጸሎት ማብቂያ ላይ ይህ የመማጸኛ ጸሎት የቀረበው በዚሁ ምክንያት ነው።

"አባታችን ሆይ" በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ መግለጫዎች ኢየሱስ በስቃይ ውስጥ በነበረበት ወቅት “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” (ማር 14፡ 36) በማለት ኢየሱስ የተናገራቸውን ንግግሮች በሚያስገርም ሁኔታ አጠቃሎ የያዘ ጸሎት ነው። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ የክፉ ነገሮች ሰላባ ሆኖ ነበር የዚህ የክፉ ነገር ተመክሮ ወይም ልምድ ነበረው። ሞት ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም በመስቀል ላይ የመሞት ተመክሮ ነበረው። የብቸኝነት መንፈስ ውስጥ መግባቱ ብቻ ሳይሆን ተንቆ ነበር። ክፉ የሆኑ ነገሮች የተፈጸሙበት ብቻ ሳይሆ እነዚህ ክፉ የሆኑ ነገሮች በጭካኔ መንፈስ ጭምር ነበር የተፈጸሙበት። ታዲያ ሰው ምንድነው፡ ሰው ማለት ሕይወትን የሚመርጥ፣ ፍቅርን እና መልካም ነገርን ሁሉ የሚያልም፣ ነገር ግን እርሱ እራሱን እና የእርሱ ቢጤ የሆኑ ሰዎችን በየጊዜው ቀጣይነት ባለው መልኩ ለክፋት የሚያጋልጥ፣ በመጨረሻም ሰው በመሆናችን የተነሳ ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርገን ፍጡር ነው።

"አባታችን ሆይ" የሚለው ጸሎት በእያንዳንዳችን ውስጥ ይፈጸም ዘንድ ከምናቀነቅነው ሙዚቃ ጋር ይመሳሰላል። አንድ ክርስቲያን የክፋት ኃይል ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳለው እንደሚያውቅና በተመሳሳይ ሁኔታ አሰፍሪ በሚባሉ ክፉ ነገሮች ፈጽሞ ያልተሸነፈው ኢየሱስ እኛን ለመርዳት እንዴት እንደ ሚመጣ እና ከችግር እንደ ሚያወጣን ያውቃል።

ስለዚህ ይህ “አባታችን ሆይ” የሚለው ጸሎት ኢየሱስ ትቶልን የሄደው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ውርስ ነው፡ ይህም ማለት የእግዚኣብሔር ልጅ የሆነው እርሱ እኛን ከክፉ ነገር ሁሉ ነጻ ለማውጣት እና እኛን ለመለወጥ ከእኛ ጋር ይታገላል ማለት ነው። ኢየሱስ በመጨረሻው የስቃይ እና የመከራ ሰዓት ውስጥ በነበረበት ወቅት ጴጥሮስ ሰይፉን ወደ ሰገባው እንዲመልስ ነግሮታል፣ ከእርሱ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንጀለኛ ሰው ከእርሱ ጋር በገነት እንደ ሚሆን ነግሮታል፣ እርሱ በስቃይ ውስጥ በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ያንን አሳዛኝ ሁኔታ ሳያውቁ በእዚያ አከባቢ ተሰብስበው ለነበሩ ሰዎች ሁሉ "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው” (ሉቃ 23:34) በማለት የመጨረሻ የሰላምታ ቃል ተናግሮ አልፉዋል።

ኢየሱስ በመስቀሉ ላይ ሆኖ ካደረገልን ይቅርታ ውስጥ ሰላም፣ ከሁሉም ክፉ ነገሮች ሁሉ በላይ ብርቱ የሆነው የትንሣኤ ጸጋ ፈለቀ: ይህ የእኛ ተስፋ ነው!

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 May 2019, 14:57