ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለቡልጋሪያ ያስተላለፉት መልእክት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከሚያዝያ 27-29/2011 ዓ.ም ድረስ 29ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቡልጋሪያ እና ሰሜን መቀዶኒያ በቅደም ተከተል እንደ ሚያመሩ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ቀደም እንደ ተለመደው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማደርግ ወደ ሚሄዱባቸው አገራት አስቀድመው በቪዲዮ መልእክት እንደ ሚልኩ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት በሚያዝያ 26/2011 ዓ.ም የ29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመርያ መዳረሻ ወደ ሆነችው ቡልጋሪያ መልእክት ማስተላለፋቸው የታወቀ ሲሆን ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ቅዱስነታቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በባልካን አገራት  ያደርጉት የመጀመርያው ጉብኝት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በስድስት ዓመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስናቸው ዘመን በጣሊያን ውስጥ እና ከጣሊያን ውጪ 29 ሐዋርያዊ ጉብኝት ማደርጋቸውን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በሚያዝያ 27/2011 ዓ.ም የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ መዳረሻ ለሆነችው ለቡልጋሪያ ሕዝቦች ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት ወደ እዚያው ማለትም ወደ ቡልጋሪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በመንፈሳዊ ንግደት ስሜት የሚደረግ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ ሆነ ገልጸው ይህ ሐዋርያዊ ጉኝታቸው “የእምነት፣ የኅበረት እና የሰላም ምልክት መገለጫ” እንደ ሚሆን ያላቸውን ተስፋ ቅዱሰነታቸው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው መልእክታቸው በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “የእናንተ ምድር ወንድማማቾቹ ቅዱሳን ቄሬሊዮስ እና ሜቶዲዮስ የዘሩት የቅዱስ ወንጌል ዘር ፍሬ ውጤት የሆነው የእምነት አገር ነው” ያሉት ቅዱሰንታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ በቡልጋሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደርጉበት ወቅት "በአስቸጋሪ ጊዜያት እንኳን የወንጌል ስብከት ሥራዎቻቸው ብዙ ፍሬዎችን እንዳመጡ” ተናግረው እንደ ነበረ አስታውሰው በሚያዝያ 27/2011 ዓ.ም በቡልጋሪያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ከሆኑት ብጽዕ ፓትሪያርክ ቴዮፋይት እና ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር እንደ ሚገናኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው “በጋራ እና በአንድነት ጌታ ክርስቶስን ለመከተል ያለንን ፍላጎት በሁሉም ክርስቲያኖች መካከል ያለውን የወንድማማች ኅብረት መንገድ እናሳያለን "ብለዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ በሕይወት ዘመናቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የቅድስት መንበርን በመወከል የቅድስት መንበር ልዑክ ሁነው ለዐስር ዓመታት ያህል በቡልጋሪያ ተልዕኮዋቸውን ተወተው እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው “እርሳቸው በወቅቱ የጀመሩት ግንኙነት እስከ ዛሬው ቀን ድረስ ዘልቆ በሁለቱም ማለትም በኦርቶዶክስ እና በካቶሊክ አብያተ ክርስትያናት መካከል መልካም የሚባል ግንኙነት እንዲፈጠር መንገድ መከፈታቸውን” ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በዚህም ምክንያት የተነሳ እና እርሳቸው ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ አከናውነው ያለፉትን መልካም ተግባር በድጋሚ ለማስታወስ ይህ 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት በላቲን ቋንቋ “Pacem in terries” በአማርኛው ሲተረጎም “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” በሚል መሪ ቃል እንደ ሚደረግ ገልጸዋል።   ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የተሳክ ይሆን ዘንድ ሁሉም ክርስትያኖች ጸሎት እንዲያደርጉላቸው የተማጸኑ ሲሆን “እግዚአብሔር ለቡልጋሪያ ሰላምና ብልጽግናን እንዲሰጥ”  ከተማጸኑ በኋላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለዚህ በቡልጋሪያ ለሚያደርጉት 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ይሆን ዘንድ የመረጡት መሪ ቃል በላቲን ቋንቋ “Pacem in terries” በአማርኛው “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” የሚለው መሪ ቃል ሲሆን ይህ “Pacem in terries” በሚል አርእስት ለንባብ የበቃወ ሐዋርያዊ መልእክት ከዚህ ቀደም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1960ዎቹ በተከሰተው የቀዝቃዛው ጦርነት ሳቢያ ሁለቱም (አሜርካ እና ራሻ) የዓለማችን ኃያላን የሚባሉ ሀገራት የኒውክለር የጦር መሳሪያን በከፍተኛ ሁኔታ መታጠቅ መጀመራቸው የሚታወቅ ሲሆን በወቅቱ ይህንን ጅምላ ጨራሽ የሆነ መሳሪያ ለመታጠቅ የሚደርገው እሽቅድድም ለዓለማችን ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ የተነሳ መወገድ የሚገባው ፍጥጫ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አቋሟን መገልጿ ይታወሳል።

04 May 2019, 17:04