ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ኢየሱስ ያሳየንን የትህትና፣ የጸሎት እና የዝምታ መንገድ መከተል ይገባል” አሉ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሚያዝያ 6/2011 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት፣ ሕዝቡም በታላቅ ደስታ “በጌታ ስም ሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው፣ በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በማለት የተቀበሉበት እለት የሚዘከርበት የሆሣዕና በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሮ አልፏል። ይህን በዓል ምክንያት በማድረግ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ስብከት እንደገለጹት ዲያቢሎስ የሚያቀርብልንን "ክብር" ለማሸነፍ እና የእግዚአብሔር መንግሥት ተካፋይ ለመሆን እንችል ዘንድ ኢየሱስ ያስተማረንን ሦስት አብነቶች “ትህትና፣ ዝምታ እና ጸሎት” የተሰኙትን መከተል ይኖርብናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው እለት የሆሳዕና በዓል በተከበረበት ወቅት በቫቲካን በሚገኘው በቅድሱ ጴጥሮስ አደባባይ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፦

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ወቅት ከተደረገለት አስደሳች አቀባበል በመቀጠል ውርደት ይገጥመዋል። የደስታ ጩኸት ወደ አስቃቂ ስቃይ ይቀየራል። ዛሬ በተከበረው በዓል ውስጥ መሠረታዊ በሆነ መልኩ በተንጸባረቀው የውይራ ዝንጣፊ ተይዞ በተደርገው ዑደት እና ኢየሱስ የሚቀበላቸውን መከራዎች በሚተርኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አማካይነት በእነዚህ ሁለት ዓይነት ገጽታ ባላቸው ምስጢራት ታጅበን በየዓመቱ ወደ ሕማማት ሳምንት ውስጥ እንገባለን።

በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ወደዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እንግባ እናም በመግቢያ ጸሎት ላይ እንደ ተጠቀሰው በዚህ የጸሎት መነፈስ በሚገኘው ጸጋ ውስጥ ገብተን ለመኖር እንሞክር፣

በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ወደዚህ እንቅሳቃሴ ውስጥ እንግባ፣ እናም በጸሎታችን አማካይነት የምንፈልገውን ፀጋ ለማግኘት እንሞክር: የአዳኛችንን ትህትና አብነት በመከተል፣ በመከራ ውስጥ ብንገኝም እናኳን ይህንን መከራ በታላቅ ትዕግስት ማለፍ እንደሚገባን የሚያስተምረውን ትምህርት እና በመጨረሻም በክፉ መንፈስ ላይ ድልን በመጎናጸፍ የሚገኘውን ደስታ ተካፋይ እንድንሆን እንዲያደርገን መጸለይ ይገባናል።

ኢየሱስ የመከራ ጊዜን እንዴት መጋፈጥ እንደ ሚገባን በማሳየት እና ታላቅ የሆነ ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት በልባችን ውስጥ ከእርሱ እንዳንለይ የሚያደርገንን ወይም ደግሞ ከልክ በላይ በሆነው ሰብዓዊ የሆነ ኃይል በሚያደርስብን ጫና እንዳንሸነፍ፣ ሰላሙን በቀጣይነት በልባችን ውስጥ በማኖር ሕይወትን እና ምህረትን በሚሰጠው በአብ እና በእርሱ የማዳን ፍላጎት ተማምነን እንድንኖር ያስተምረናል። በአገልግሎቱ ውስጥ በሁሉም ቦታ ላይ የእዚህ ዓይነቱ ለአብ ያለው ታዛዥነት በሁሉም እርሱ በምድር ላይ በነበረው አገልግሎት ውስጥ የደርሰበትን ፈተና ለመጋፈጥ እንዳስቻለው እና አብን ሙሉ በሙሉ መተማመን ደግሞ ፈተናዎችን በሙሉ ለማሸንፍ እንደ ሚያስችለን አሳይቶናል። በበረሃ ውስጥ በነበረው የአርባ ቀን ቆይታ ተሞክሮ አንስቶ መከራውን እስከ ተጋፈጠበት እለት ደረስ በነበረው ሂደት ውስጥ ኢየሱስ የደረሰበትን ፈተና በአሸናፊነት ሊወጣው የቻለው ለአባቱ ትዕዛዝ ታማኝ ሆኖ እስከ መጨረሻው ድረስ በመዝለቁ ነው።

ዛሬም ቢሆን ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ወቅት ይህንን መንገድ ያሳየናል። በዚያን ወቅት የዚህ ዓለም ልዑል የሆነው ክፉ መንፈስ የጥፋት ክንዱን ለማሳየት ሞክሯል፤ ይህም የድል አድራጊነት ስሜት ነው። ነገር ግን ጌታ በራሱ መንገድ በመሄድ በትሕትና መንፈስ ምላሽ ሰጠ።

ድል አድራጊነት ግቡን የሚመታው በአቋራጭ መንገድ በመሄድ እና በሐሰት በሚሰነዘሩ አስተያየቶች አማካይነት ነው። የአሸናፊነትን መገለጫ በሆነ ሰረገላ ላይ በፍጥነት ዘሎ መቀመጥ ይፈልጋል። እርሱ በመስቀል መጋረጃ ውስጥ ያልተካተቱትን ምልክቶች እና ቃላት በመጠቀም በሌሎች ላይ በመፍረድ፣ ሌሎችን ዝቅተኛ አድርጎ በመቁጠር የእነርሱን ውድቀት በመመኘት ራሱን እንደ ድል አድራጊ አድርጎ በመቁጠር ለመኖር ይፈልጋል። የዚህ ዓይነቱ የድል አድራጊነት መንፈስ ደግሞ ዓለማዊነት ነው፣ አደገኛነትን ይወክላል፣ በጣም እጅግ የከሸፈ እና ቤተ ክርስቲያንን እያጋጣማት የሚገኝ ፈተና ነው። የዚህን ዓይነት የድል አድራጊነት መንፈስ ኢየሱስ በተቀበለው መከራ ድል አድርጎታል።

ጌታ የእርሱን ስም እየጠሩ፣ እርሱ ንጉሥ እና መሲህ እንደ ሆነ አድርገው በታላቅ ድምጽ ይጮኹ ከነበሩ ወጣቶች ጋር አብሮ ተደስቶ ነበር። በእስራኤል የነበሩ ድኾች ለእርሱ የነበራቸውን ቀና አስተሳሰብ እና ያሳዩት ደስታ እርሱን አስገርሞት ነበር። በተመሳሳይ መልኩ እነዚህ በደስታ እየጮኹ የሚገኙት የእስራኤል ልጆችን ዝም እንዲያሰኛቸው ለጠየቁት ፈሪሳዊያን “እነርሱ እንኳን ዝም ቢሉ ድንጋዮች መጮኽ ይጀምራሉ” (ሉቃስ 19፡40)በማለት መለሰ። ትሕትና እውነታን መካድ ማለት አይደለም፣ ኢየሱስ በእርግጥ መሲህ እና ንጉሥ ነው።

ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ የኢየሱስ ልብ በእርሱ እና በአባቱ ብቻ በሚታወቀው ቅዱስ ጎዳና ላይ እየሄደ ነበር፣ ይህ መንገድ ደግሞ “እግዚአብሔር ከመሆን” ወደ “አገልጋይ ወደ መሆን”፣ ራስን ከማስገዛት መንፈስ የተወለደ የታዛዥነት መንገድ፣ "እስከሞት ድረስ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ” (ፊል 2፡6-8) ታዛዥ ሆነ። እውነተኛ ድል የሚገኘው ለእግዚአብሔር ቦታ በመስጠት እና ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ራስን አሳልፎ መስጠት እና ራስን ባዶ አድርጎ ማቅረብ እንደ ሚያስፈልግ እርሱ አሳይቶናል። በዝምታ መቆየት፣ መጸለይ እና ውርደትን መቀበል። በመስቀል ላይ ምንም ድርድር የለም፣ አንድ ሰው መቀበል ወይም አለመቀበል ብቻ ነው ምርጫው። ኢየሱስ ራሱን ዝቅ በማድረግ እርሱ የእምነትን መንገድ በመክፈት እናም በእዚያ የእምነት መንገድ ላይ እንድንጓዝ ፈለገ።

በዚህ የእምነት መንገድ ላይ በቅድሚያ የተጓዘችው ሐዋርያ የእርሱ እናት ማርያም ናት። በንጽህት ድንግል ማርያም እና ቅዱሳን ጭምር የእግዚአብሔርን ፍቃድ ለመፈጸም እና በእምነት ሕይወት መንገድ ላይ በመጓዛቸው የተነሳ ተሰቃይተዋል። አስጨናቂ እና አሰቃቂ በሆኑ የሕይወት ጉዞ ውስጥ በእምነት የምንሰጠው ምላሽ “የልባችንን ክብደት” ያሳያል። በጨለማ ውስጥ የሚገኝ እምነት። በእርግጥ በጨለማ ውስጥ ሆነን ነው የትንሳኤውን ብርሃን የምንመለከተው። በመስቀል ሥር የነበረችው ማርያም መልአኩ “እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” (ሉቃስ 1፡32-33) ብሎ የተናገራትን ቃል አስታወሰች። በጎልጎታ ላይ ማርያም ይህን የተስፋ ቃል ሙሉ በሙሉ መቃወም ነበረባት። ምክንያቱም ልጇ እንደ ወንጀለኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እየሞተ ስለነበር። በዚህ ሁኔታ የድል አድራጊነት መንፈስ ኢየሱስ ራሱን ዝቅ በማድርጉ የተነሳ ተሸነፈ፣ በተመሳሳይ መልኩም በማርያም ልብ ውስጥ የነበረው የድል አድራጊነት መንፈስ ተሸነፈ። ሁለቱም ዝም ጸጥ አሉ።

የማርያምን ዳራ በመከተል ቁጥር ስፍር የሌላቸው ቅዱስ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች በትህትና እና በመታዘዝ መንገድ ኢየሱስን ተከትለዋል። ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወጣት የሆኑ እግዚኣብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ቅዱሳን አሉ። ወጣቶች ለኢየሱስ ያላችሁን ፍላጎት ለመግለጽ አትፈሩ፣ እርሱ ሕያው እንደ ሆነ እና በተጨማሪም እርሱ ሕይወታችሁ እንደ ሆነ ጮክ ብላችሁ መመስከር አትታክቱ። በተመሳሳይ መልኩም በእርሱ የመስቀል መንገድ ላይ መጓዝ አትፍሩ። እርሱ ራሳችሁን በመካድ ወደ እርሱ እንድትቀርቡ በሚነግራችሁ ወቅት፣ እርሱ ለእራሳችሁ ደህንነት በማሰብ መንገዳችሁን እንድትቀይሩ በሚመክራችሁ ወቅት፣  እርሱ ራሳችሁን ሙሉ በሙል ለእግዚኣብሔር በአደራ እንድትሰጡ በሚጠያቃችሁ ወቅት ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ! ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በሚወስደው ጎዳና ላይ ናችሁና!

የደስታ ጩኸት እና አሰቃቂ መከራ፡ በመከራው ወቅት የነበረው የኢየሱስ ዝምታ በጣም አስገራሚ ነበር። እንደ አንድ ኮከብ እንደ ሆነ ሰው ሆኖ እንዲሰማው ሊያደርገው ይችል የነበረውን ምላሽ የመሰጠት ፈተና አሸንፏል። በጨለማ እና በታላቅ መከራ ውስጥ በምንገባበት ወቅት ዝም ማለት ይጠበቅብናል፣ ምላሽ ስጥ ብሎ የሚወተውተንን ፈተና በብርታት ማለፍ ይገባል፣ ዝምታችንም በየዋህነት መንፈስ ሊሆን ይገባል እንጂ በንዴት በተሞላው መንፈስ ግን በፍጹም ሊሆን አይገባውም። በየዋህነት መንፈስ ተሞልተን ዝም የምንል ከሆነ የባሰውኑ ደካሞች እና ትሁቶች እንሆናለን። ከእዚያም በኋላ ክፉ የሆነ መንፈስ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ብቅ ማለት ይጀምራል፤ ግልጽ በሆነ ሁኔታ መታየት ይጀምራል። እርሱን ደግሞ "ያለበትን አቋም ይዘን" በዝምታ መቃወም ያስፈልገናል፣ ኢየሱስም ያደረገው በዚሁ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው። እርሱ ይህ ጦርነት በእግዚአብሔር እና በዚህ ዓለም አለቃ መካከል እየተካሄደ በመሆኑ የተነሳ፣ አስፈላጊው ነገር እጃችንን ሰይፋችንን ለማውጣት መስደድ ሳይሆን ነገር ግን በእምነት ጸንተን መቆየት እንዳለብን። የእግዚአብሔር ሰዓት ነው። እግዚአብሔር ለመዋጋት በሚወጣበት ሰዓት ሁሉንም ነገር እርሱ እንዲቆጣጠረው ልንፈቅድለት የገባል። ደህንነት የምናገኝበት ቦታ ደግሞ የእርሱ እናት በሆነቸው በማርያም ጥበቃ ሥር ነው። በውስጣችን የተቀሰቀሰውን ማዕበል ጌታ መጥቶ ጸጥ ያደርገው ዘንድ በዝምታ ውስጥ ሆነን በምንጸልይበት ወቅት በውስጣችን ላለው የእግዚአብሔር ተስፋ ክብር እንሰጣለን ማለት ነው። ይህም በተስፋ ቃሎች ትውስታ፣ በመስቀል ላይ ባለው ሥቃይ፣ እና በትንሣኤ ተስፋ መካከል በሚኖረው ሂደት ውስጥ በመጓዝ በቅድስናና እና በተስፋ ትንሳኤውን እንድንጠባበቅ ያደርገናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 April 2019, 13:31