ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ስጥተዋል፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ስጥተዋል፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በሕዝቦች መካከል ልዩነትን የሚዘራ ለራሱ ተነጥሎ ይቀራል”።

ቅዱስነታቸው በሞሮኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት እና ስለ ወንድማማችነት አንስተው መወያየታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው ከዚህ በፊትም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተማ በሆነው በአቡ ዳቢ በተደረገው የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ ወቅትም የተፈረመውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ አስታውሰው በሞሮኮ ስላለው የሐይማኖት ነፃነት እና በአገሩ ለሚገኙ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ለሚሰጠው አክብሮት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመጋቢት 21 እስከ መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሰሜን አፍሪቃ አገር በሆነችው በሞሮኮ 28ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ትናንት እሑድ ወደ ቫቲካን በሰላም መመለሳቸውን የቫቲካን የዜና አገልግሎት አስታውቋል። ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ ከቤተ ክህነት እና ከመላው ምዕመናን ጋር በመገናኘት መልዕክት ማስተላለፋቸው እና መወያየታቸው ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ወደ ሮም ለመመለስ ባደረጉት ጉዞ ወቅት እንደ ተለመደው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል። ለቅዱስነታቸው ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል ስለሚደረጉ ውይይቶች፣ የስደተኞችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር እና የሕሊና ነጻነት የሚሉ ይገኙባቸዋል።

የቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ፣ ሊንዳ ቦርዶኒ እንደገለጸችው በሞሮኮ የሁለት ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ሮም ባደረጉት የአውሮፕላን ጉዞ ላይ ከጋዜጠኞች ጋር ከግማሽ ሰዓት በላይ ቃለ ምልልስ ማድረጋቸውን ገልጻለች።

በሞሮኮ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለዓለም ሰላም እና በባሕሎች መካከል ለሚደረጉት ውይይቶች ምን አስተዋጾኦን ሊያበረክት ይችላል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲመልሱ አሁን አበባን አይተናል፣ ፍሬውን እንጠብቃለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው በሞሮኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት እና ስለ ወንድማማችነት አንስተው መወያየታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው ከዚህ በፊትም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተማ በሆነው በአቡ ዳቢ በተደረገው የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ ወቅትም የተፈረመውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ አስታውሰው በሞሮኮ ስላለው የሐይማኖት ነፃነት እና በአገሩ ለሚገኙ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ለሚሰጠው አክብሮት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ያፈካው አበባ ወደ ፊት የወንድማማችነት እና የአንድነት ፍሬ የሚታይበት በመሆኑ ስንታክት መንከባከብ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ አንዳንድ ችግሮች አልጠፉም ያሉት ቅዱስነታቸው በእያንዳንዱ የሐይማኖት ተቋማት ውስጥ የአክራሪነትን መንገድ የሚከተሉ ቡድኖች መኖራቸውን ገልጸው እነዚህ ክፍሎች ታዲያ በሕዝቦች መካከል ፍራሃትን እና የጦርነት ስጋትን በማስከተል መጥፎ ትዝታን ይተዋሉ ብለዋል። ስለዚህ በሕዝቦች መካከል እውነተኛ እና ወንድማዊ ውይይት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበው በእያንዳንዱ የሰዎች ግንኙነት መካከል ውይይት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ወደ ስምምነት ሲደረስ ሰብዓዊነት በተሞላ መልኩ በማስተዋል፣ ከልብ በመነሳሳት በተግባር እንደሚፈረም ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሞሮኮ ዋና ከተማ በራባት የኢየሩሳሌምን ከተማ በማስመልከት የተፈረመው የይገባናል ጥያቄ የሞሮኮን ወይም የቫቲካንን መንግሥት አቋም ለማንጸባረቅ ሳይሆን፣ ያች ከተማ ለሁሉም የሰው ልጆች የተስፋ ከተማ ሆና ለማየት የሚመኙ ወንድሞች እና እህቶች አቋም እንደሆነ አስረድተው ኢየሩሳሌም የአይሁድም፣ የሙስሊሙም እና የክርስቲያኑም ነው ብለው ሁላችንም የኢየሩሳሌም ዜጎች ነን ብለዋል።

የልዩነት ግድግዳን ሳይሆን የአንድነት ድልድይን መገንባት ያስፈልጋል።

በሕዝቦች መካከል የአንድነት ግድግዳን ሳይሆን የልዩነት ግድግዳን በመገንባት ላይ የሚገኙትን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በገነቡት ግድግዳ ተዘግተው እንደሚቀሩ ገልጸው እነዚያ የአንድነትን ድልድይ የሚገነቡት ረጅም መንገድን መጓዝ እንደሚችሉ አስረድተዋል። የአንድነት ድልድይን ለመገንባት ትልቅ ጥረትን እና ጉልበትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። የእውቁን ደራሲ የኢቮ አንድሪች ጽሑፍ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በመልአክት ክንፍ እግዚአብሔር የገነባው የድሪና ድልድይ ሰዎች እርስ በእርስ መገናኘት የሚችሉበት እንደሆነ አስረድተው የልዩነት ግድግዳን የሚገነቡት ራሳቸውን ከሌሎች ነጥለው ለእስር ይዳረጋሉ ብለዋል።

የአምልኮ እና የሂሊና ነጻነት፣

በብዙ አገሮች ዘንድ እምነታቸውን ከእስልምና ወደ ክርስትና የሚቀይሩት ሰዎች ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የእምነት ክህደትን በሚፈጽሙት ላይ የሚጣልባቸውን የሞት ቅጣት ፍርድ ከ300 ዓመት በፊት እንዳስወገደች ገልጸው ቤተክስቲያኒቷ እምነቶቿን ጠንቅቃ በማወቅ ለሰው ልጅ እና ለእምነት ነጻነት ከፍተኛ ክብርን ትሰጣለች ብለዋል። በአንዳንድ አገሮች እምነት መቀየር አደጋን እንደሚያስከትል የገለጹት ቅዱስነታቸው በሞሮኮ በተለየ መልኩ የሁሉም እምነት ተከታዮች መብት የተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የስደተኞችን ጉዳይ በማስመልከት ሕጎችን እና ደንቦችን ለሚያወጡ የሕግ ባለሞያዎች እና ለመንግሥታት መሪዎች አቤቱታቸውን አሰምተዋል። አንዳንድ የአውሮጳ አገሮች በሚያራምዷቸው የሕዝባዊነት ፖለቲካ ሥርዓታቸው የክርስቲያን መራጮችን ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ ባስገባታቸውን እንዴት ይመለከቱታል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፣ ከፍተኛ ፍርሃት እንደሚሰማቸው ገልጸው የአምባገነንነት ስርዓት መጀመሪያ ነው ብለዋል። በጀርመን የናዚ ሥርዓት አመሰራረትን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ታሪክ ያስተማረንን መዘንጋት የለብንም ብለው አውሮጳ የተገነባችው በስደተኞች እንደሆነ እና ስደተኞች ሃብቷ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በርካታ የየመን ሕጻናት የሚሞቱበትን ጦርነት በጦር መሣሪያ ምርት የሚደግፉ የአውሮጳ አገራት እንዳሉ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህን ከማድረግ ይልቅ ረሃብን ለማስወገድ፣ ትምህርትን ለማዳረስ እድገትን ለማምጣት የሚያስችል እገዛን ቢያደርጉ ይሻላል ብለዋል። ስደትን ማስቀረት የሚቻለው በቸርነት፣ በትምህርት እና እድገትን በሚያመጡ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 April 2019, 17:14