ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እኛ ሁላችን እግዚኣብሔርን በድለናልና ይቅርታ ልንጠይቀው የገባል” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሚያዝያ 02/2011 ዓ.ም ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ከዚህ በፊት ጀምረውት የነበረው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል የነበረ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዚሁ በክፍል 12 የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በደላችንን ይቅር በልልን” በሚለው “አባታችን ሆይ!” በተሰኘው ጸሎት ውስጥ በሚገኘው የመማጸኛ ሐረግ ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ቅዱሳንንም ጨምሮ እኛ ሁላችን እግዚኣብሔርን በድለናልና ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራ እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 02/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

“አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ውስጥ የእለት እንጀራችንን እግዚአብሔር እንዲሰጠን ከተማጸንን በኋላ ከሌሎች ጋር ስላለን ግንኙነት እንሻገራለን። ኢየሱስ አባቱን “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን” (ማቴ 6፡12) ብለን እንድንጠይቅ ያስተምረናል። የእለት እንጀራ እንደ ሚያስፈልገን ሁሉ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ ይቅርታ ያስፈልገናል። 

አንድ የሚጸልይ ክርስቲያን ከሁሉም በላይ እግዚኣብሔርን የሚጠይቀው ነገር ቢኖር ኃጢአቱን ይቅር እንዲለው ነው። በጸሎቱ ውስጥ ይህ የመጀመሪያው እውነታ ነው፦ እኛ ፍፁም የሆንን ሰዎች ልንሆን እንችል ይሆናል፣ እኛ መልካም የሆነ ኑሮ ለመኖር የምንጥር ቅዱሳን ክርስቲያኖች ልንሆን እንችላለን፣ ነገር ግን ሁላችንም ከአባት የተወለድን ህጻናት ነን። በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በጣም አደገኛ የሚባለው ነገር ኩራት ነው። በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ቆመው ሂሳባቸውን ሊያወራርዱ የሚፈልጉ ሰዎች ዓይነት ባህሪይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌነት እንደ ቀረበው ፈሪሳዊው ሰው በቤተመቅደስ ውስጥ ሆነ ጸሎት እያደረገ እንደ ሆነ ሆኖ የሚሰማው ሰው፣ በተግባር ግን ራሱን በእግዚኣብሔር ፊት ሆኖ ያወድስ እንደ ነበረው ሰው ዓይነት ነው። በተቃራኒው ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረው ሰው፣ በሁሉም ሰዎች ዘንድ እንደ ኃጢአተኛ የተቆጠረው ሰው፣ በቤተመቅደሱ ደጃፍ ላይ ቆሞ ወደ ውስጥ ለመግባት እንኳን ብቁ አይደለሁኝም፣ የተገባው አይደለሁኝም ብሎ በማሰብ ራሱን ለእግዚኣብሔር ምሕረት በአደራ ያቀርባል። በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ በሰጠው አስተያየት “እላችኋለሁ፤ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይኸኛው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ” (ሉቃስ 18፡14) በማለት መናገሩ ይታወሳል።

በዐይን የሚታዩ እና በዐይን የማይታዩ ኃጢአቶች አሉ። ጫጫታ የሚፈጥሩ እና እንድናጉረመርም የሚያደርጉን ኃጢአቶች አሉ፣ በተጨማሪም ደግሞ በእኛ ውስጥ ሳይታወቀን በልባችን ውስጥ የሚንጸባረቁ ኃጢአቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የከፋው ኩራት ሲሆን ይህም ጠንካራ መንፈሳዊ ሕይወት ያላቸውን ሰዎች ሳይቀር ሊበክል ይችላል። በወንድማማችነት ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥር ኃጢያት ነው፣ ይህም ከሌላው ሰው እንሻላለን ብለን እንድናስብ ያደርገናል፣ ይህም እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ተመሳሳይ ነን ብለን እንድናስብ ያደርገናል።

ነገር ግን እኛ ሁላችን በእግዚኣብሔር ፊት ኃጢአተኞች ነን፣ በዚህም የተነሳ እንደ ቀረጥ ሰብሳቢው ሰው ልባችንን እየደቃን ብንጸልይ ምክንያት አለን። ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያው ምልእክቱ ውስጥ እንደ ጻፈው “ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” (1 ዮሐንስ 1፡8) ይለናል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ በዚህ በሕይወት ዘመናችን ውስጥ ብዙ ነገሮችን ስለተቀበልን ባለዕዳዎች ነን፣ ምክንያቱም በሕይወት ጉዞዋችን ውስጥ አባት እና እናት፣ እንዲሁም ጓደኛ እና ድንቅ የሆኑ የእግዚኣብሔር ስጦታዎችን . . . ወዘተ ያገኘንበት ወቅት ነው። ሁላችንም አስቸጋሪ በሚባሉ ቀናት ውስጥ ብናልፍም፣ ሕይወት ፀጋ መሆኑን ማስታወስ አለብን፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከምንም በላይ ለእኛ የሰጠን ተዓምር ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ባለዕዳ እንድንሆን የሚያደርገን ነገር ደግሞ ምንም እንኳን ማፍቀር የምንችል ብንሆንም እንኳን በእራሳችን ጥንካሬ ብቻ ማከናወን ባለመቻላችን የተነሳ ነው። ማናችንም ብንሆን በራሳችን ብርሃን ብቻ ደምቀን መታየት አንችልም። የምታፈቅር ከሆንክ ደግሞ ይህ የሆነው ከአንተ ውጭ የሆነ አንድ ሰው ልጅ እያለህ ፈገግ ብሎ ምልሽ ስለሰጠህ እና ስለፍቅር ስላስተማረህ ሊሆን ይችላል። የምታፈቅር ከሆነ ከአንተ አጠገብ የሚገኝ አንድ ሰው በአንተ ውስጥ ያለው ፍቅር እንዲነቃቃ በማደርግ የሕይወት ሕልውና የሚገኘው በፍቅር ውስጥ እንደ ሆነ እንድንገነዘብ በማድረጉ የተነሳ ሊሆን ይችላል።

በሕይወቱ ዘመን አንድ ስህተት የሰራ፣ እስረኛ የነበረ፣ አንድ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ የነበረ ሰው ታሪክ እንመልከት። ምንም እንኳን ኃላፊነቱ የግል ቢሆንም የዚህ ጥፋት ተጠያቂው ማን ነው? ብለን እንጠይቃለን፣ የራሳችንን ህሊና ብቻ ሳይሆን ከራሱ ሕይወት ጋር አብሮ የሚሄድ ከዚህ ጀርባ ያለውን የጥላቻና የብቸኝነት ሕይወት እንደነበረው ይሰማዋል።

አስቀድሞ ስለ ወደደን እኛም በተመሳሳይ መንገድ ልንወድ ይገባል፣ አስቀድሞ ይቅር ስላለን ደግሞ እኛም ይቅር ልንባባል ይገባል። እንዲሁም አንድ ሰው በፀሐይ ብርሃን ታግዞ ማብራት ካልቻለ እንደ ክረምት የመሬት አቀማመጥ ቀዝቃዛ ይሆናል። ማናችንም ብንሆን እግዚኣብሔር በሚወደን መልኩ ወደነው አናውቅም። እርሱ እንዴት እንደ ሚወደን ያለማጋነን ይህንን ሁኔታ ለመረዳት በመስቀሉ ስር ሆነን ልንመለከተው የገባል፡ እርሱ ለዘለዓለም ወደደን፣ አስቀድሞ የወደደን ደግሞ እርሱ ራሱ ነው። ስለዚህ እኛ እንጸልይ: ጌታ ሆይ: በመካከላችን የሚገኝ ቅዱስ የሚባል ሰው እንኳን በደላችንን ይቅር በልልን ብሎ መጸለዩን እንዲቀጥል አድርግልን። አባት ሆይ የሁላችንንም በደል ይቅር በልልን!

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
10 April 2019, 15:47