ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በፈተና ወቅቶች ሁሉ በእግዚኣብሔር መተማመናችንን መቀጠል እንችል ዘንድ ኢየሱስ ያስተምረናል”

በፈተና ወቅቶች ሁሉ በእግዚኣብሔር መተማመናችንን መቀጠል እንችል ዘንድ፣ “አባት” ብለን በመጥራት ከአባታችን ጋር በመገናኘት እርሱም ይቅር ማለት የምንችልበትን ብርታት ይሰጠን ዘንድ ልንጠይቀው የገባል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በሚያዝያ 09/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ላይ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላያ በሚያዝያ 09/2011 ዓ.ም ባደርጉት የክፍል 13 የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ገለጹት “ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት በአብ መተማመናችንን እንድንቀጥል ኢየሱስ ያስተምረናል” ማለታቸው ተገሉጽዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸኮስ በሚያዝያ 09/2011 ዓ.ም ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

በእነዚህ ሳምንታት ውስጥ "አባታችን ሆይ" በሚለው ጸሎት ላይ እያሰላሰልን እንገኛለን። አሁን ለፋሲካ በዓል ዝግጅት በምናደርግበት በዚህ የሕማማት ሣምንት ውስጥ ኢየሱስ በዚህ በስቃዮ ወቅት ወደ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ቃላት እንመለከታለን።

የመጀመሪያው ተማጽኖ የሚጀምረው ከመጨረሻው እራት በኋላ ጌታ "ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ” “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው-ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ- እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐንስ 17፡1.5) በማለት ጸለየ። የእርሱ መከራ በተቃረበበት ወቅት ተጻራሪ በሚመስል መልኩ ኢየሱስ ክብር እንዲሰጠው ይጠይቃል። ይህ ምን ዓይነት ክብርን ያመለክታል? ክብር በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚኣብሔር መገለጥ ያመለክታል፣ የእርሱ በሰዎች መካከል ተገኝቶ የማዳን ሁኔታውን የሚገልጽ ልዩ ምልክት ነው። አሁን ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መገኘት እና የእግዚኣብሔርን የማዳን ኃይል የሚገልጽ ልዩ ምልክት ነው። ይህንንም ያደረገው በፋሲካ ነው፣ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ በዚህም የተነሳ ክብርን አገኘ። እግዚአብሄር በመጨረሻም የእርሱን ክብር ያሳየናል፣ የመጨረሻውን መሸፈኛ በማስወገድ ከዚህ በፊት ተሰምቶን በማያውቅ ሁኔታ ያስደንቀናል። በእርግጥ የእግዚኣብሔር ክብር መገለጫው ፍቅር ነው፣ ንጹሕ የሆነ ፍቅር፣ ከመጠን በላይ እና ሊደረስበት የማይችል ፍቅር፣ ገደብ የሌለው እና የማይለካ ፍቅር።

ወንድሞችና እህቶች እኛ የኢየሱስን ጸሎት ጸሎታችን እናድርግ፣ ዓይኖቻችንን የጋረዱንን መጋረጃዎች እግዚኣብሔር ከዓይናችን ላይ እንዲያስወግድ እንጠይቀው፣ ምክንያቱም በዚህ ባለንበት የሕማማት ሳምንት ውስጥ የእርሱን መስቀል በመመልከት እግዚአብሔር ፍቅር ነው ብለን መቀበል እንችላለን። እንደ አባታችን አድርገነው ሳይሆን ነገር ግን እንደ አንድ ጌታ አንድርገን የቆጠርነው ለምን ያህል ጊዜ ይሆን! ምን ያህል ጊዜ ይሆን እርሱን በምሕረት የተሞላ አባት አድርገን ሳይሆን እንደ አንድ ፈራጅ ዳኛ የቆጠርነው! ነገር ግን እግዚኣብሔር በእዚህ የፋሲካ በዓል እኛ እና እርሱ የነበረንን ርቅት ያጠባል፣ በትህትና እና በፍቅር በተሞላ መንፈስ የእኛን ፍቅር ይጠይቃል። እርሱ ለእኛ እንዳደረገው እኛም ሁሉንም ነገር ከልባችን በፍቅር በምናከናውንበት ጊዜ ሁሉ ለእርሱ ክብር እንሰጣለን ማለት ነው። እውነተኛ ክብር የፍቅር ክብር ነው፣ ምክንያቱም ለዓለም ህይወት የሚሰጥ ብቸኛው ይህ ነውና። እርግጥ ነው ይህ ክብር በአድናቆት፣ በሙገሳ፣ በውደሳ፣ እኔ እኔ የሚል እና እኔን ማዕከል ባደርገ መልኩ በዚህ ሁኔታ በተሞላ ቃላት ዓለም ከሚሰጠው ክብር በጣም የተለየ እና በተቃራኒው የሚገኝ ክብር ነው። የእግዚኣብሔር ክብር ግን ከዚህ በተለየ መልኩ የሚገኝ ክብር ነው፡ ምንም ዓይነት ጭብጨባ እና ምንም ዓይነት ተመልካች የማይፈልግ ክብር ነው። በእግዚኣብሔር ክብር ውስጥ “እኛ” የሚለው ቃል እንጂ “እኔ” የሚለው ቃል ቦታ የለውም፣ በእርግጥ በፋሲካ በዓል የምንመለከተው ይህንን ሀቅ ነው፣ አብ ለልጁ ክብር የሰጣል፣ በተመሳሳይ መልኩም ወልድ ለአባቱ ክቡር ሲሰጥ እንመለከታለን። ማነኛቸውም ቢሆኑ ለራሳቸው ክብር አልሰጡም። እኛ ዛሬ ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባ ጥያቄ “እኔ በሕይወቴ የምኖርለት ክብር ምንድነው? ለእኔ ክብር ነው ወይስ ለእግዚኣብሔር ክብር? ከሌሎች ክብር ለመቀበል ብቻ ነው የምሻው ወይስ እኔ ለሌሎች መስጠት እፈልጋለሁ?”

ከመጨረሻው ራት በኋላ ኢየሱስ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ገባ፣ በዚያ ስፍራ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል። ደቀ-መዛሙርቱ ነቅተው ለመቆየት ባልቻሉበት ወቅት እና ይሁዳ ከወታደሮቹ ጋር እየመጣ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ "ፍርሃትና ጭንቀት" ይሰማዋል። ለተፈጸመበት ክህደት፣ ውርደት እና ውድቀት ባስከተለው ጭንቀት ውስጥ ገባ። በዚያ ስፍራ በጥልቅ ሐዘን እና ብቸኝነት ውስጥ ገብቶ ነበር፣ በዚህም የተነሳ ገር እና ጣፋጭ በሆነ ቃል አባቱን “አባ” በማለት ይጠራል። ጥልቅ በሆነ መከራ ውስጥ በምንገባበት ወቅት ይህንን መከራ መጋፈጥ የሚያስችለን ኃይል እንዲሰጠን አብን አጥብቀን መያዝ እንደ ሚገባን ኢየሱስ ያስተምረናል። በችግር ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ጸሎት እፎይታን እና እምነትን ይሰጣል። በሁሉም በመካዱ የተነሳ ኢየሱስ የብቸኝነት መንፈስ ተሰምቶት የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በውስጡ ብቻውን አለነበረም አባቱ ከእርሱ ጋር ነበረ። እኛ የጌተሴማኒ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በምንገባበት ወቅት “አባት ሆይ” ብለን በመጣራት ኢየሱስ እንዳደረገው ራሳችንን ለእግዚኣብሔር በአደራ ከመስጠት ይልቅ ራሳችንን በብቸኝነት መንፈስ ውስጥ ማስገባት እንወዳለን። ነገር ግን ፈተና በሚከሰትበት ጊዜ ራሳችንን በራሳችን ዝግ በማድረግ በውስጣችን ዋሻ እንቆፍራለን፣  ውስጣዊ የሆነ በሐዘን የተሞላ ጉዞ አንድ አቅጣጫ ብቻ ይከተላል፣ ይህም አቅጣጫ ይበልጡኑ ሐዘን ውስጥ ይከተናል። ዋናው እና ትልቁ ችግር ሐዘን ውስጥ መግባቱ ሳይሆን ነገር ግን እንዴት ይህንን ሐዘን መጋፈጥ እንደ ሚኖርብን ማውቁ ነው። ብቸኝነት ከሐዘን የመውጫ አቅጣጫ አያመላክተንም፣ የሚያዋጣው መንገድ ጸሎት ነው ምክንያቱም ጸሎት ግንኙነትን እና መተማመንን ሰለሚፈጥር። ኢየሱስ ሁሉንም ነገር በአደራ ሰጠ፣ ራሱን ለአባቱ በአደራ ሰጠ፣ የሚሰማውን ስሜት እና በትግሉ ውስጥ የሚገጥመውን ነገር ሁሉ አባቱ ይደግፈው ዘንድ በአደራ ሰጠው። ወደ ጌቴሴማኒ ስንገባ (እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ ጌቴሴማኒ ውስጥ እንገኛለን፣ ወይም በጌቴሴማኒ ውስጥ ገብተን አልፈናል፣ ወይም ደግሞ ለወደፊቱ ጌቴሴማኒ ሊገጥመን ይችል ይሆናል) በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በምንገባበት ወቅት ሁሌም ይህንን እናስታውስ “አባት ሆይ!” የሚለውን እናስታውስ።

በመጨረሻም ኢየሱስ ለአባቱ "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" (ሉቃ. 23፡34) በማለት በርኅራኄ በተሞላ መንፈስ ለእኛ ጸለየ። ኢየሱስ በእርሱ ላይ ክፉ ነገር ለፈጸሙ ለገዳዮቹ ጸለየ። ይህ ቃል የተገለጸው በመስቀል ላይ እንደ ነበረ ቅዱስ ወንጌል ግልጽ በሆነ መልኩ ያቀርብልናል። ምን አልባትም ኢየሱስን በመስቀል ላይ ሊሰቅሉት በተዘጋጁበት ወቅት እጆቹን እና እግሮቹን በሚስማር በሚቸነክሩበት በእዚያ አሳዛኝ ወቅት የተነገረ ቃል ሊሆን ይችላል። በእዚህ ስቃይ ጫፍ ላይ በደረሰበት ወቅት የፍቅሩ መግለጫ መደምደሚያው ላይ ደረሰ፣ ይቅርታ የማድረጊያው ጊዜ ደረሰ፣ ገደብ የሌለውን ስጦታውን ሰጠ፣ የክፋትን ተግባራታ በጣጠሰ።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ "አባታችን ሆይ" ብለን በመጸለይ ከእነዚህ ጸጋዎች ውስጥ አንዱን መጠየቅ እንችላለን: በሕይወት ዘመናችን ለእግዚኣብሔር ክብር ብለን ለመኖር ማለትም በፍቅር ለመኖር ያስቸልን ዘንድ፣ በፈተና ወቅቶች ሁሉ በእግዚኣብሔር መተማመናችንን መቀጠል እንችል ዘንድ፣ “አባት” ብለን በመጥራት ከአባታችን ጋር በመገናኘት እርሱም ይቅር ማለት የምንችልበትን ብርታት ይሰጠን ዘንድ ልንጠይቀው የገባል። እዚህ ሁለት ነገሮች አብረው የሚጓዙ ነገሮች ናቸው፦ አብ ይቅር ይለናል እኛም ይቅርታ ማደርግ እንችል ዘንድ ብርታቱን ይሰጠናል።

 

17 April 2019, 15:28