ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ስፖርት ያቀራርባል፣ በሕዝቦች መካከል በጎነትን ይጨምራል”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ስፖርት ለሰላም እና ለእድገት” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ስፖርት ያቀራርባል፣ በሕዝቦች መካከል በጎነትን ይጨምራል ማለታቸው ተገለጸ። ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ. ም. ባስተላለፉት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ማጥቃለያ ላይ እንዳስገነዘቡት በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች በማሳተፍ ሕይወትን ማጣጣም እንደሚቻል ገልጸው በዘርፉ ለተሰማሩት በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።    

የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊው 1896 ዓ. ም. ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን እንዲከበር በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መወሰኑ የሚታወስ ነው። ስፖርት በሕዝቦች መካከል እንዲዘወተር የተፈለገበት ታሪካዊ ዓላማው በእያንዳንዱ ማሕበረሰብ ውስጥ አዎንታዊ ለውጦችን ለማምጣት የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ለማስገንዘብ፣ ስፖርትን በማዘውተር ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለእድገት፣ በሕዝቦች መካከል ሰላምን እና የእርስ በእርስ ትውውቅን ለማሳደግ ታስቦ የተጀመረ መሆኑ ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ “ስፖርት ሕዝቦችን ለማገናኘት እና ግጭቶችን ለማርገብ የሚያግዝ  ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው” ብለዋል። በማከልም ስፖርት ለአንድ ማሕበረሰብ እድገት መሠረት፣ በጎነት የሚቀሰምበት ትምህርት ቤት እንደሆነ ተናግረው ስፖርት የደስታ እና የመልካም ስሜት ምንጭ መሆኑን  አስረድተዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ለተሠማሩት ሰዎች ባስተላለፉት መልዕክት  በተሰማሩበት የስፖርት ዓይነት ለአዲሱ ትውልድ መልካም ምሳሌ በመሆን ጠቃሚ መልዕክቶችን ማዳረስ፣ ደስታን የተሞላ የወንድማማችነት መንፈስን እንዲያሳድጉ አደራ ብለዋል። ከስፖርተኞቹ መካከል አንዱ የሆነው እና የውሃ ዋና ስፖርት ተወዳዳሪው ወጣት አማኑአል ቦርቱዞ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት ከራሱ የሕይወት ልምድ ጋር በማገናዘብ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ባቀረበው ምስክርነት እንደገለጸው፣ ከጥቂት ወራት በፊት የአካል ጉዳት አደጋ ቢያጋጥመውም ተስፋን ባለመቁረጥ ለስፖርቱ ባደረበት ፍቅር፣ የተሰማራበት የውሃ ዋና ስፖርት ለግል ሕይወቱ የሚሰጠውን ደስታን እና ብርታትን በመገንዘብ፣ አክብሮትንም በመስጠት ወደ ስፖርቱ መመለሱን ገልጾ ከደረሰበት አደጋ ለማገገም ብሎ በሕክምና ላይ በቆየባቸው ሁለት ወራት ውስጥ በርካታ አድናቂዎቹ በማሕበራዊ መገናኛዎች በኩል በመተባበር ማጽናናታቸውን ተናግሯል።

የእኔ የስፖርት ልምድ የኢጣሊያን ሕዝብ አንድ አድርጓል፣

“እርካታን ለማግኘት ከቻልኩበት መንገድ አንዱ ስፖርት የለገሰልኝ ሕይወት ነው” ያለው አማኑኤል፣ ስፖርት በሕዝቦች መካከል አንድነትን ለማምጣት  የሚያስችል ታላቅ ሃይል እንደሆነ አስረድቶ ማንኛውም የስፖርት ዓይነት ቢሆን ትክክለኛ እና ቀዳሚ ዓላማው ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ሳይሆን ለሁሉም በሚገባ ቋንቋ፣ በሕዝቦች መካከል ደስታን በመጨመር አንድነትን እና ሕብረትን መፍጠር ነው ብሏል።

ለወጣቱ ትውልድ መልካም ምሳሌ ሆኖ መገኘት፣

ከበርካት የስፖርት አፍቃሪዎች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠው አማኑኤል እንደገለጸው ምኞቱ በሚወዳድርበት የስፖርት ዓይነት ዝናን ማትረፍ እንዳልሆነ ገልጾ ዝናን ማትረፍ ከሆነ በማንኛውም ዓይነት የሥራ ተሰማርቶ በሚያገኘው ወርሃዊ ገቢ ራሱን ወይም ቤተሰቡን ማስተዳደር የቻለ ሁሉ ዝናን ማትረፍ እንደሚችል ገልጾ፣ ለእርሱ ዝነኛ መሆን ማለት ሊያጋጥሙ የሚችሉትን እንቅፋቶች ተቋቁሞ፣ ለተሠማራበት የሥራ ዓይነት አክብሮትን፣ ታማኝነትን፣ ጽናትን እና መልካም ስነ ምግባርን ያሳየ ሁሉ መልካም ስምን ሊያተርፍ ይችላል ብሏል።        

ወጣት አማኑኤል ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ሲደመድም እንደተናገረው ዋና ዓላማው ከደረሰበት የአካል ጉዳት በማገገም ወደ ቀድሞ የሰውነት አቋሙ በመመለስ፣ ከሕጻንነቱ ጀምሮ የተመኘውን የኦሊምፒክ ውድድር ለመካፈል የሚፈልግ መሆኑን ገልጿል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

04 April 2019, 16:59