ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የኢየሱስ ክርስቶስ የስቃይ መስቀል የዓለም ስቃይ የሚገኝበት ነው”።

ዓርብ ሚያዚያ 11/2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ ኮሎሴውም በተባለ ሥፍራ በተከናወነው የፍኖተ መስቀል የጸሎት ስነ ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሰሙት ንግግር በሞት ላይ የተቀዳጀውን ድል እና የብርሃነ ትንሳኤውን ተስፋ በልባችን ውስጥ በድጋሚ እንድናስታውስ ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን ማለታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከተማ በሚገኝ በኮሎሴዉም፣ በጎርጎሮርሳዊው የቀን አቆጣጠር መሠረት የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉት ምእመናን ዘንድ፣ ትናንት ዓርብ ሚያዝያ 11/2011 ዓ. ም. በተከናወነው የስቅለተ ዓርብ ዕለት የፍኖተ መስቀል የጸሎት ስነ ስርዓት ለተገኙት በርካታ ምዕመናን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  ባሰሙት ንግግር ኢየሱስ ክርስቶስ የተጓዘበት የመስቀል መንገድ በሰብዓዊ ፍጥረት እና በቤተክርስቲያን ላይ የተፈጠረውን ቁስል ያጠቃልላል ማለታቸው ታውቋል። ይህን ካሉ በኋላ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የመላው ዓለም መከራ እና ስቃይ የሚገኝበት መሆኑ እንድንገነዘብ እግዚአብሔር ይርዳን ብለዋል። በሮም ከተማ የተከናወነው የዘንድሮ ፍኖተ መስቀል የጸሎት ሥነ ሥርዓት የኮንሶላታ ማርያም ገዳማዊያት አባል የሆኑት እህት ኤውጄኒያ ቦነቲ ባቀረቡት አስተንትኖ የታገዘ መሆኑ ታውቋል። እህት ኤውጄኒያ ያቀረቡት አስተንትኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው የስመቀል መንገድ፣ እርሱን ይከተሉ የነበሩ የኢየሩሳሌም ሴቶች በማስታወስ ዛሬ በዘመናችን ሴቶች ላይ የሚደርስ መከራ እና ስቃይ ብዙ መሆኑን የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል።                 

ፍትህ እና ሰላም የጠማቸው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለማችን የዕለት እንጀራን እና ፍቅርን የተራቡ፣ በስቃይ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው ከእነዚህም መካከል ከልጆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው፣ ደጋፊን አጥተው የስቃይ ሕይወት የሚኖሩ እንዳሉ ተናግረዋል። የሚመግባቸው፣ የሚያለብሳቸው እና የሚያጽናናቸው የሌላቸው፣ ለብዙ ዓመታት ብቻቸውን ሆነው የሚሰቃዩ አረጋዊያን በቁጥር በርካታ  እንደሆኑ ገልጸዋል።

ስደተኞችን እና ሕጻናትን የሚያጋጥም የመስቀል ሕይወት፣

ሰዎችን የሚያጋጥም የመስቀል ሕይወት በማሕበረሰቡ መካከል የሚታይ የማግለል ባህል ውጤት እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ይህ ባሕልም ራሳቸውን ለመከላከል አቅም የሌላቸውን የማሕበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ መሆኑን አስታውቀዋል። ስደተኞችን የሚያጋጥም የመስቀል ሕይወት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ድንበሮች የተዘጋባቸው፣ በደረሱበት አገር ተፈርተው አስፈላጊውን መስተንግዶ እና ፍቅርን የተነፈጉ፣ የመንግሥታት መሪዎችም ሕጎቻቸውን በማጥበቃቸው ምክንያት ለጥገኝነት ጥያቄያቸው መልስ ያልተሰጣቸው ብዙ ስደተኞች መኖራቸውን አስታውሰው በተጨማሪም በሚፈጸምባቸው በደል እና የጉልበት ብዝበዛ የስቃይ እና የመከራ ሕይወት እየኖሩ ብዙ ሕጻናት መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ቤተሰብን እና የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን የሚደርስ የመስቀል ሕይወት፣

በዓለማችን ውስጥ የስቃይ ሕይወትን ከሚኖሩት መካከል ቤተሰብን እና የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ዓለማችን ከደረሰበት የጨለማ እና የጥርጣሬ ባሕል የተነሳ በርካታ ቤተሰብ በክህደት፣ በመታለል እና በራስ ወዳድነት፣ የመስቀል ሕይወት እየኖሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። የወንጌልን ብርሃን ሳያቋርጡ ወደ ዓለም ዙሪያ ለማድረስ ጥረት ላይ የሚገኙትን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአገልግሎታቸው ወቅት ተቃወሞ፣ ስድብ እና ውርደት እንደሚያጋጥማቸው አስታውሰዋል።

ከድካማችን ምክንያት የሚያጋጥመን የመስቀል ሕይወት፣

እንደ እግዚአብሔር ቃል ለመኖር ጥረት ላይ የሚገኙትን የቤተክርስቲያን ልጆች የሚደርስ የስቃይ ሕይወት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእነዚህም መካከል ስደተኞች፣ ከማሕበረሰቡ መካከል የተገለሉ እና ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው ተለይተው የሚገኙ በርካታ ሰዎች እንዳሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው ከእነዚህም ጋር በስንፍና፣ በግብዝነት፣ በክህደት እና በሐጢአት ምክንያት የሚያጋጥም የመስቀል ሕይወት እንዳለ አስታውሰዋል።

ቤተክርስቲያንን የሚያጋጥም መስቀል፣

የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ የሆነች ቤተክርስቲያንም የራሷ መስቀል አለባት ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለችውን የወንጌል ቃል በታማኝነት ወደ ዓለም ለማዳረስ በምታደርገው ጥረት መካከል መስቀል እንደሚያጋጥማት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በገዛ ልጆቿ በኩል ከውስጥም ሆነ ከውጭ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚሰነዘርባትን እና ጉዳት የደረሰባትን ቤተክርስቲያን        ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውሳት በማለት በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣

የምንኖርባትን የጋራ ምድር በመጉዳት ላይ የሚገኝ መስቀል አለ ያሉት ቅዱስነታቸው በስግብግብነት እና በስልጣን በመመካት የሚመጣ መስቀል እንዳለ ገልጸው ዓለማችን የሚያጋጥማትን መስቀል ወይም ስቃይ የምናስወግድበት ብቸኛው ተስፋችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ባቀረቡት ጸሎት “ኢየሱስ ሆይ! በሞት ላይ የተቀዳጀሄውን ድል እና የብርሃነ ትንሳኤህን ተስፋ በልባችን እንድናስታውስ እርዳን በማለት ልመናቸውን አቅርበዋል።  

20 April 2019, 16:31