ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባር ሰዎችን ወደ ሸቀጥ የሚለውጥ ወንጀል ነው”።

ሐሙስ ሚያዝያ 3 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚወያይ ጉባኤ መካሄዱ ታውቋል። የጉባኤው ዋና ዓላማ ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀልን ለመከላከል የሚያግዝ ሐዋርያዊ መመሪያን በጋራ ለመመልከት እንደሆነ ታውቋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ጉባኤን ከተለያዩ አገሮች የመጡ እንግዶች መካፈላቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን ከዚህ በታች የሠፈረው ጽሑፍም የቅዱስነታቸው ንግግር ሙሉ ትርጉም ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን ዋላችሁ!

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ የሚከታተል ክፍል፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባርን ለመከላከል የሚያግዝ ሐዋርያዊ መመሪያን ማዘጋጀቱ የሚታወቅ ሲሆን ይህን መመሪያ እኔም ተመልክቼው አጽድቄዋለሁ። በቅድስት መንበር የሰዎች ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ክቡር አባ ሚካኤል ዠርኒ በጉባኤው አባላት ስም ላደረጉት ንግግር ማስጋናዬን አቀርባለሁ።

“እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ”(ዮሐ. 10.10)። በዚህ የወንጌል ጥቅስ በኩል የኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ መከናወኑን እንገነዘባለን። የጊዜ ገደብ ሳይደረግበት እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሙሉ ሕይወትን እንዲያገኝ የእግዚአብሔር እቅድ ተከናውኗል። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ ሰው ሆኖ የተገለጠው ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ ሰብዓዊ ማንነታቸውን በትክክል እንዲገነዘቡ እና የማይለዋወጥ ሰብዓዊ ማንነት እንዳላቸው ለማስገንዘብ ነው።

የዛሬው ዓለም ይህ የእግዚአሔር ዕቅድ ተግባራዊ እንዳይሆን በሚያደርጉት እንቅፋቶች ውስጥ ይገኛል። ተዘጋጅተው የወጡት ሐዋርያዊ መመሪያዎች ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባርን አስ፣አልክቶ በዝርዝር እንደሚያብራራው በሰዎች ማሕበራዊ ኑሮ ውስጥ የግለኝነት ስሜት እያደገ መምጣቱን፣ የስግብግብነት ባሕርይ ማደጉን እና የግል ጥቅምን ብቻ ማሰብ ሌሎች ሰዎችን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ መገልገያ መሣሪያ አድርገው እንዲቆጥሩት የሚያደረግ አስተሳሰብ እያደገ መምጣቱን ይገልጻል።  

ከዚህ በፊትም ብዙ ጊዜ እንደተናገርኩት የሰው ልጅ እንደ ሰው ሳይሆን ለንግድ እንደተዘጋጀ የሸቀጥ ዕቃ የሚታይበትን አዝማሚዎች እናያለን። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባር ነው። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በበርካታ ገጽታው በማሕበረሰባችን መካከል ከባድ አደጋን በተለይም ወንጀሉ በሚፈጸምባቸው ሰዎች ላይ ጥልቅ ቁስልን ይፈጥራል። ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባር የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ እና ነጻነቱንም የሚያሳጣ ተግባር ነው። ይህ ተግባር የወንጀሉ ተጠቂን ብቻ ሳይሆን የወንጀሉ ፈጻሚን ስብዕና የሚያሳጣ እና የተሟላ ሕይወትን እንዳያገኝ የሚያደርግ ተግባር ነው።  ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባር በአጠቃላይ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነውን ቤተሰብ የሚጎዳ እና የሚያፈርስ ተግባር ነው።

ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባር በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት የሌለው፣ የወንጀሉ ተጠቂ የሆኑ ሰዎችን ነጻነት የሚጻረር፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያዘጋቸላቸውን እቅድ የሚቃረን በመሆኑ የወንጀል ተግባር ነው። ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ተግባር አስከፊነት የስደተኛውን ሆነ ስደተኞች የሚገኙባቸው አገሮች ዜጎች ነፃነትን እና ክብርን የሚቀንስ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል።

በዚህ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፍ ሁሉ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በራሱም ሕይወት ላይ ከባድ ጥፋትን ይፈጽማል። እያንዳንዳችን የተፈጠርነው ሌሎችን ለማፍቀር እና አስፈላጊ እንክብካቤ እንድናደርግላችው ነው።  “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም” (ዮሐ. ወንጌል ምዕ. 15፤13) ወደሚለው መደምደሚያው ላይ እንድንደርስ ይጋብዘናል። ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በምናደርጋቸው የተለያዩ ግንኙነቶች በኩል እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገለጠልንን ግንኙነት እናጠናክረዋለን አለበለዚያም እናበላሸዋለን። የእግዚአብሔርን እቅድ የሚጻረር ምርጫ በሙሉ ስብዕናችንን በመካድ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰጠንን የተሟላ ሕይወት እንድናጣ ያደርጋል።

የእኛን እና የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ እንዲሁም ለመንከባከብ የምናደርገው ጥረት እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የጀመረው የማዳን ተልዕኮ ቀጣይነት እንዲኖረው የምናደርግበት የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ነው። ይህ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ማንኛውንም በሰዎች ላይ የሚፈጸም ሕገ ወጥ ዝውውርን የሚቃወም፣ ከወንጀሉ ያመለጡትን ወደ ቤታችን ተቀብለን ራሳቸውን እንዲችሉ የምናደርግበት እና የተሟላ ሕይወትን ለመጀመር የሚያስችል መንገድ መሆን አለበት።

ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! በዛሬው ዕለት በቁጥር በርከት ብላችሁ እዚህ መገኘታችሁ ቤተክርስቲያን ቸርነቷን በተግባር በመግለጽ ማሕበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ምን ያህል ሐዋርያዊ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰች መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው። ይህን አስከፊ ችግር ለመከላከል መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ብዙ ቢሆኑም ከእነዚህም መካከል ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲገታ ማድረግ፣ የወንጀሉ ሰለባ ለሆኑት እና ከወንጀሉ ሊያመልጡ የቻሉትን ተቀብሎ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ እና በወንጀሉ ላይ ተሰማርተው በሚገኙት ላይ ሕጋዊ እርምጃን መውሰድ የሚሉ ይገኙባቸዋል። በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተጠቁትን እና ከወንጀሉ ጥቃት ማምለጥ የቻሉትን ወደ ቤታቸው ተቀብለው አስፈላጊውን እርዳታ ያበረከቱትን እና በማበርከት ላይ የሚገኙትን በርካታ ገዳማዊያትን እና ገዳማዊያንን፣ ወንጀሉን ለመከላከል ቤተክርስቲያን ለምታደርገው ሐዋርያዊ ተልዕኮ መሳካት የበኩላቸውን እገዛ ላደረጉት እና በማድረግ ላይ ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከዚህ በፊት ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል ወደ ፊትም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመሰለ የተወሳሰበ ማሕበራዊ ክስተት ሲያጋጥም ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች በብሔራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀናጅተው በሕብረት መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው። የቁምስና ጽሕፈት ቤቶች፣ የገዳማዊያት እና ገዳማዊያን ማሕበራት፣ ሌሎች በርካታ ካቶሊካዊ ተቋማት እና ድርጅቶች አቅማቸው በማስተባበር ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ፣ ሰዎች ለስደት የሚዳረጉባቸው አገሮች፣ ስደተኞች የሚሻገሩባቸው አገሮች እና የስደተኞች መድረሻ አገር የሆኑት በጋራ ሆነው የችግሩን መነሻ እና መወሰድ ስላለበት እርምጃ መወያየት ያስፈልግል።

ቤተክርስቲያንም ተልዕኮዋን በበቂ መጠን እንድታከናውን ከመንግሥታት እና ሕዝባዊ ማሕበራት በኩል ድጋፍ ሊኖራት ይገባል። በርካታ ተቋማት እና ድርጅቶች ተስማምተው የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ዘላቂ እና አስተማማኝ የሆኑ መልካም ውጤቶችን ለማምጣት ያግዛል።

በችግር ላይ የሚገኙትን በርካታ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከችግራቸው ለማላቀቅ ብላችሁ ላደረጋችሁት ጥረት እና በማድረግ ላይ ለምትገኙት ጥረቶች በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከማሕበረሰቡ ዘንድ ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ ያላችሁት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር አደገኛ እና የተሠወረ ወንጀል በመሆኑ ለዚህ ከባድ ተልዕኮአችሁ ብራታትን እመኝላችኋለሁ።

ከሕጻንነቷ ጀምሮ በባርነት ሕይወት የተሰቃየች፣ በኋላም ለነጻነት የበቃች የእግዚአብሔር ልጅ የቅድስት ጁሴፒና ባኪታን አማላጅነት በመለመን ተልዕኮአችሁ ፍሬያማ እንዲሆን በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬዬ ለእያንዳንዳችሁ እንዲደርሳችሁ እያልኩ በጸሎቴ እንደማስታውሳችሁ አረጋግጥላችኋለሁ፣ እናንተም በጸሎታችሁ እንድታስታውሱኝ አደራ እላለሁ።                   

11 April 2019, 17:47