ፈልግ

በሊቢያ ከሚገኙ ስደተኞች በከፊል፣ በሊቢያ ከሚገኙ ስደተኞች በከፊል፣ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በሊቢያ የሚገኙት ስደተኞች ሁኔታ አሳስቦአቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚያዝያ 20/2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት በርካታ ምዕመናን እና አገር ጎብኝዎች ጋር ሆነው ካሳረጉት የሰማይ ንግሥት ሆይ ጸሎት በመቀጥል ባቀረቡት ንግግር በሊቢያ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሊቢያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት እየተፋፋመ መምጣቱ የበርካታ ዜጎችን እና የስደተኞችንም ሕይወት አደጋ ላይ መጣሉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሚያዝያ 20/2011 ዓ. ም. ለምዕመናን ባሰሙት ንግግር በሊቢያ ውስጥ የስደተኞች ሁኔታ አስቀድሞም ቢሆን እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ተናግረው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እየተፋፋመ በመጣው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሕይወት ለአደጋ መጋለጡን አስታውሰው ምዕመናኑም በጸሎታቸው ከጎናቸው እንዲሆኑ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በሊቢያ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በርካታ ሕጻናት፣ እናቶች እና ሕሙማን እንደሚገኙ ገልጸው እነዚህ ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል የማይችሉትን ስደተኞች ከሞት አደጋ ለማትረፍ ጦርነቱ የሚካሄድበትን አካባቢ ለቀው ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወሩ ጠይቀዋል።  

በሊቢያ በመካሄድ ላይ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት የዓለም አቀፍ እውቅና ከተቸረለት ከሊቢያ መንግሥት ታማኝ ሠራዊት እና በጦር አዛዥ ካሊፋ ሐፍታር የሚመራ የመንግሥት ተቃዋሚ ሠራዊት መካከል መሆኑ ታውቋል። ስደተኞችም ከመጠለያ ጣቢያቸው ወጥተው የመንግሥት ሠራዊትን በመቀላቀል የጦርነቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በመገደድ ላይ ናቸው ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በርካታ ነዋሪዎች በሚገኙበት በምዕራብ ሊቢያ ክፍለ ሃገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት 220 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ሲያስታውቅ፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅትም በበኩሉ በዋና ከተማ ትሪፖሊ ደቡባዊ አካባቢ የተጠለሉ 39,000 ስደተኞች የሚገኙበትን መጠለያ ጣቢያ ለመልቀቅ መገደዳቸውን አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦርነቱ ሰለባ ቁጥር እንዳስታወቀ ባለፈው ቅዳሜ የሊቢያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ እንዳታወቀው በአማጺያኑ ሠራዊት ቁጥጥር ስር የሚገኝ ምዕራባዊው ክፍለ በሦስት ቀናት ውስጥ ከአማጽያኑ እጅ ነጻ እንደሚወጣ ማስታወቁ ታውቋል።

በኢጣሊያ ውስጥ “አጀንሲያ አበሻ” የተሰኘ ድርጅት መሥራች የሆኑት ክቡር አባ ሙሴ ዘርዓይ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት በሊቢያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው ስደተኞች ከተደቀነባቸው የሞት አደጋ ለማዳን ጦርነቱ ከሚካሄድበት አደገኛ አካባቢዎች ስደተኞቹን ወደ ሌላ አካባቢ ለማዛወር እንዲቻል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እገዛ እና ትብብር የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።   

በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች የስቃይ ሕይወት እና አሁን የተጋረጠባቸው የጦርነት አደጋም ቢሆን ከማንም የተሰወረ አይደለም ያሉት ክቡር አባ ሙሴ ዘርዓይ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚያዝያ 20/2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ምዕመናን እና አገር ጎብኝዎች ባሰሙት ንግግር በሊቢያ ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ማስታወሳቸውን ተናግረው በሊቢያ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች ሁኔታ አስቀድሞም ቢሆን እጅግ አስቸጋሪ ነበር ማለታቸውን አስታውሰዋል።

በትሪፖሊ ደቡባዊ ምስራቅ ክፍለ ከተማ በጦር አዛዥ ካሊፋ ሐፍታር የሚመራ የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ሃይል ወታደሮች በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በከፈቱት ጥቃት ሃያ ስደተኞችን ማቁሰላቸው እና ስድስቱን መግደላቸውን አባ ሙሴ ገልጸው ለአደጋው የተጋለጡት ስደተኞች የነፍስ አድን እርዳታን በመወትወት ላይ እንዳሉና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ወደ ሌላ ሦስተኛ አገር እንዲዛወሩ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን አባ ሙሴ ተናግረዋል።

በሞት አደጋ ላይ ለሚገኙት ለእነዚህ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በተለይም ሕጻናትን፣ እናቶችን እና በሕመም ላይ የሚገኙትን በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን የነፍስ አድን የእርዳታ ጥሪን ያስታወሱት በኢጣሊያ ውስጥ የሚገኝ አጀንሲያ አበሻ የተባለ ድርጅት መስራች የሆኑት ክቡር አባ ሙሴ ዘርዓይ እንደኣተናገሩት ለሞት አደጋ የተጋለጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሕይወት ማዳን የሚቻለው ጦርነት ከሚካሄድበት ከሊቢያ ወጥተው ወደ ሦስተኛ አጎራባች አገር የሚዛወሩ ከሆነ ነው ብለው ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት የበኩሉን ድጋፍ ሲያደርግ ነው ብለዋል።              

አሁን በሊቢያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት በጦር አዛዥ ካሊፋ ሐፍታር የሚመራ የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ሃይል ወታደሮች ዋና ከተማ ትሪፖሊን የዓለም አቀፍ ዕውቅና ካለው ከሊቢያ መንግሥት ሠራዊት እጅ ነጻ ለማድረግ በሚያደርገው ፊልሚያ እንደሆነ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 April 2019, 16:32