ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወጣቶች የልባቸውን ጥርጣሬ ወደ ኢየሱስ እንዲያቀርቡ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ. ም. በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ወደሚገኘው ቅዱስ ጁሊዮ ቁምስና ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ለቁምስናው ምእመናን  ባሰሙት ንግግንር እንደገለጹት ኢየሱስ የልባችንን ንጽህናን መመልከት ይፈልጋል ብለዋል። አያይዘውም ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ከቅርብ ሆኖ በመመልከት የደከሙትን መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ በሚገኝ በቅዱስ ጁሊዮ ቁምስና ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባካሄዱበት ወቅት ከቁምስናው ምእመናን ጋር የጸሎት ሥነ ሥርዓትን ተካፍለው ከቁምስናው ልዩ ልዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አባላት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ሦስት ዓመት የፈጀውን የቁምስናውን የመዋቅር ለውጥ ማጽደቂያ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ. ም. ከቀኑ 10 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ ወደ ቁምስናው ሲደርሱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ወደ ቁምስናው ከመጡት እንግዶች መካከል የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ደ ዶናቲስ፣ የሮም ምዕራባዊ ክፍለ ከተማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፓዎሎ ሰልቫዳጂ እና የቁምስናው መሪ ቆሞስ አባ ዳሪዮ ፍራቲኒ ተገኝተዋል። የቁምሳናው ምዕመናን በደስታ እና በዝማሬ በመታጀብ ለእንግዶቹ ደማቅ አቀባበልን አድረገውላቸዋል።

ከቁምስናው መንፈሳዊ ማሕበራት ጋር የተደረገ ግንኙነት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ከመጀመሩ አስቀድመው በቁምስናው ከሚገኙ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ማሕበራት አባላት ጋር የተገናኙ ሲሆን በቁምስናው የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ማገዝ እንዲቻል ምመናኑ ያሳነጸውን የቅድስት ቤተሰብ ሐውልት በማስመልከት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስ ፍራንችስኮስም የወንጌል አገልግሎቱን ያበረክት የነበረው እና ምመናኑን ያበረታታ የነበረው የቅድስት ቤተሰብን ምስል በመያዝ እንደነበር አስታውሰው፣ በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት አዲስ የወንጌል አገልግሎት ስርጭት ጽሕፈር ቤት፣ የቅድስት ቤተሰብ ምስል የሚታወስበት ሳምንት እያስተባበረ መሆኑን ገልጸዋል። ቀጥለውም በቅርቡ የተክሊል ምስጢር ከተቀበሉት ምዕመናን ጋር ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን ዝግጅት ላይ ለሚገኙትም ከዚህ በፊትም እንደገለጹት፣ ባለትዳሮች እርስ በእርስ ፈቃድ እና ይቅርታን መጠያየቅ፣ ምስጋናንም ማቅረብ የትህትና መንገዶች መሆናቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በባለ ትዳሮች መካከል መቀያየም ወይም መኮራረፍ ቢኖር ጊዜን ሳይወስዱ በእለቱ ይቅርታን በመጠያየቅ በቀኑ መጨረሻ ሰላም ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ምክራቸውን ሰጥተዋል። በቁምስናው የሚካሄደውን የእርዳታ ማዳረስ አገልግሎትን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በበጎ ፈቃድ ሠራተኞች እና በተረጂዎች መካከል የሚታየው የርሕራሄ ምልክት የቁምሳናውን ጥንካሬን እና ሕብረት ያመለክታል ብለው ቸርነት ከፍቅር የመነጨ፣ በተግባር የሚገለጥ መሆን አለበት ብለዋል።

ኢየሱስ ፈጽሞ ተስፋን እንድንድቆርጥ አያደርግም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቁምስናው ከተገኙት አረጋዊያን እና ሕመምተኞች ጋር ሰላምታን በተለዋወጡበት ጊዜ ምዕመናኑ ባቀረቡት ስነ ጽሑፍ በኩል፣ ስመተ ርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው በታወጀበት በመጋቢት 4 ቀን 2005 ዓ. ም. ቅዱስነታቸው ያቀረቡት “የእንደምን አመሻችሁ”! ሰላምታ የሕዝቡን ጥርጣሬ በማስወገድ የወዳጅነትን ስሜት የፈጠረ መሆኑን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በበኩላቸው፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ረጅም ዕድሜን መመኘት ጥሩ እንደሆነ ተናግረው ይህን የሚያከናውን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ገልጸው ያለ እርሱ ሁሉም ከንቱ ነው ብለዋል። አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት በፍቅሩ ብዛት የሚጎበኝ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የታመኑት በሙሉ ተስፋን እንዲቆርጡ አያደርጋቸውም ብለዋል።

የተራበን መመገብ፣

የቁምስናውን ምዕመናን በመወከል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥያቄ ካቀረቡት መካከል አንዷ ወጣት፣ ቅዱስነታቸው በበኩላቸው የተራበን በማየት የሚበላ ምግብ ሰጥተው እንደሆን በማለት ጥያቄን ያቀረብችላቸው ሲሆን ቅዱስነታቸው የተራበን ሰው ብዙ ጊዜ እንደመገቡ ገልጸው፣ ይህ ተግባር የሁላችን ተግባር መሆን አለበት ካሉ በኋላ እግዚአብሔር ዘወትር እንደሚመግበን እኛም ሌሎችን መመገብ አለብን ብለዋል።

ጥርጣሬን መፍራት አያስፈልግም፣

ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ የቁምስናው አዳጊ ወጣቶች እስካሁን በተጓዙት የክርስትና ሕይወታቸው  ጥርጣሬ እንዳለ ይታይባቸዋል ያሉት የትምህርተ ክርስቶስ መምሕር “ወጣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጽኑ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?” በማለት ለቅዱስነታቸው ጥያቄን ያቀረበች ሲሆን ቅዱስነታቸውም ሲመልሱ ጥርጣሬ ከሕይወት ገጠመኞቻችን መካከል አንዱ ነው ብለው ጥርጣሬ ሲሰማን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያለንን የማይናወጥ ታማኝነት በማስታውስ እኛም ለእርሱ ያለንን ታማኝነት ማደስ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ጥርጣሬ የሚያድርብን ከሆነ ሳንፈራ በድፍረት ለሌሎች መንገር ያስፈልጋል ብለዋል።

የምንጠራጠርበትን ጉዳይ ለኢየሱስ መናገር ያስፈልጋል፣

ጥርጣሬ ሲይዘን ብቻችን ልንወጣው እንደምንችል የገልጹት ቅዱስነታቸው በጥርጣሬ መካከል ስንገኝ የሌሎችን ድጋፍ መሻት፣ ከሁሉም በላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገር ያስፈልጋል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥርጣሬ የጸዳ ልብን ማየት ይፈልጋል ብለው በጥርጣሬ ውስጥ የወደቀን ካገኘን መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስጦታ ተበረከተላቸው፣

በዕለቱ ስነ ስርዓት ማጠቃለያ ላይ፣ በቁምስናው ሕጻናት የተዘጋጁ እና የቸርነት ተግባርን የሚያስታውሱ ስጦታዎች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተበረከተላቸዋል። ቅዱስነታቸውም በቁምስናው ከተገኙት በርካታ ምዕመናን ጋር ሆነው ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቀረቡ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ከሰጡ በኋላ ምዕመናኑ በሕብረት ሆነ ባቀረቡት የምስጋና መዝሙር የስነ ስርዓቱ ፍጻሜ ሆኗል። 

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
08 April 2019, 15:06