ፈልግ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመቁጠሪያ ስጦታ፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመቁጠሪያ ስጦታ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለወጣቶች የመቁጠሪያ ስጦታን አበረከቱ።

የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያስን ዘንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል ዛሬ ሚያዝያ 15/2011 ዓ. ም. ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጳጳሳዊ የእርዳታ ተግባር አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በኩል ስድስት ሺህ ለጸሎት የሚያገለግሉ መቁጠሪያዎችን በስጦታ መልክ ለወጣቶች ማቅረባቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ አሜሪካ አገር በሆነችው በፓናማ ዘንድሮ በተከበረው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ የታደለው መቁጠሪያ ዓይነት፣ ዛሬ ጠዋት ሚያዝያ 15/2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ በተደረገው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ለወጣቶች መታደሉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስጦታቸውን በጳጳሳዊ የእርዳታ ተግባር ሥራ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በኩል ለወጣቶች የላኩ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ስጦታቸውን ያበረከቱ ዛሬ ተከብሮ በዋለው እና በስማቸው የሚጠራውን የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ምክንያት በማድረግ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገልጸዋል።

ዛሬ ጠዋት በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት በኢጣሊያ የሚላኖ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማርዮ ዴልፒኒ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመቁጠሪያ ስጦታቸውን ለወጣቶቹ ያቀረቡበትን አጋጣሚ ተጠቅመው ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶቹ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሚያደርሱት ጸሎት በኩል እርሳቸውን እንዲያስታውሷቸው መጠየቃቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ ክፍል ዳይሬክተር ገልጸዋል።

እነዚህ መቁጠሪያዎች በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ከበቀሉ የወይራ ዛፍ እንጨት የተሠሩ መሆናቸው ሲነገር በዝግጅቱ የተሳተፉትም በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ በሚገኙ እስር ቤቶች፣ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና በከተማው ውስጥ በሚሰጥ የእርዳታ አገልግሎት የሚተዳደሩ ደሆች መሆናቸው ታውቋል። ዛሬ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት የተካፈሉት በርካታ የሚላኖ ሀገረ ስብከት ወጣቶች ነገ ረቡዕ ሚያዚያ 16/2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች በሚያቀርቡት ሳምንታውዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውም የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።

ድራጎኑን የገደለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፣

የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያስን ዘንድ ዛሬ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በመስዋዕተ ቅዳሴ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ታስቦ የዋለ መሆኑ ሲታወቅ በስማቸው በርጎሊዮ ጊዮርጊስ የሚባሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የደስታ መግለጫ መልክቶች እየደረሱ መሆናቸው ታውቋል። የዲዮቅላጽያዊያን ጦር ሠራዊት አዛች የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ እምነቱን ላለመካድ ባሳየው ቆራጥነት ምክንያት የሮማዊ ንጉሠ ነገሥት ባስተላለፈው ትዕዛዝ በኩል በክርስቲያኖች ላይ በተፈጸመው ግድያ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊው 303 ዓ. ም. የተገደለ ሰማዕት መሆኑ ይታወቃል። ሰማዕቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ባገኘው ሃይልን በማግኘት ሕዝቡን ያስጨንቅ የነበረን ዴራጎን በጦር ወግቶ እንደገደለ የቤተክርስቲያን አፈ ታሪክ ያስረዳል። ይህም የክርስትና እምነት በክፋት ላይ ድልን የተጎናጸፈበት ምልክት ሆኖ በክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ሲታወስ መቆየቱ ይታወቃል።

ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. 5,000 አይስ ክሬም ለድሆች ታድሏል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. በተከበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል በጳጳሳዊ የእርዳታ ተግባር አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በኩል በሮም ከተማ ለሚገኙት ወደ 5,000 ለሚጠጉ ደሆች የ “አይስ ክሬም” ስጦታን ማበርከታቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ የ “አይስ ክሬም” ስጦታዎች በሮም ከተማ በ “ካሪታስ ሮማ” እና በቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር በኩል የእርዳታ አገልግሎት ወደ ሚቀርብባቸው የስደተኛ ጣቢያዎች እና 900 የፖለቲካ ጥገኞች በእንግድነት ወዳረፉበት ማዕከል መዳረሱ ታውቋል።               

23 April 2019, 17:22