ፈልግ

በፓናማ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን፣ በፓናማ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር ወጣቶችን ይወዳል፣ ቤተክርስቲያንም ትፈልጋቸዋለች”።

ወጣቶች የነገ ብቻ ሳይሆኑ የዛሬም ተስፋ ናቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ዛሬ በማበርከት ላይ የሚገኙት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ብለው ወጣቶች የነገ ተስፋ ናቸው እየተባለ መጠቀሱ ወጣቶችን እንደማያስደስታቸው ገልጸዋል። ወጣቶችን የሚያጋጥሟቸው በርካታ ማሕበራዊ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው ከእነዚህም መካከል ስደት፣ ጭቆና፣ የጾታ ጥቃት እና የዲጂታል ዓለም አወንታዊ እና አሉታዊ ገጽታዎች እንደሆኑ ተናገረው የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ጥረታቸው ቢታከልበት የጨለማ ጊዜ ተወግዶ ብርሃን ሊመጣ እንደሚችል አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በዓለም ወጣቶች ዘንድ በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው አዲሱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. ታትሞ ይፋ መደረጉን ከቫቲካን የወጣ መግለጫ አስታወቀ።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከዓለም ዙሪያ ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ሆነው ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ከተማ ባደረገው የብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ወጣቶች፣ እምነት እና ጥሪያቸውን በጥበብ እና በማስተዋል ተገንዝበው ትክክለኛ እና ቆራጥ ውሳኔን እንዲያደርጉ በሚል ርዕሥ ሰፊ ውይይትን ካደረጉ በኋላ የጉባኤያቸውን ጠቅላላ ሃሳብ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማቅረባቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የጉባኤውን ጠቅላላ ሃሳብ ተቀብለው ከተመለከቱት በኋላ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል። ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱ ቃለ ምዕዳን “ሕያው ክርስቶስ” የሚል መጠሪያን ይዞ በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. ለንባብ መብቃቱን የቫቲካን መግለጫ ክፍል አስታውቋል።    

“ክርስቶስ ሕያው ነው፣ እናንተንም ሕያው እንድትሆኑ ይፈልጋል” በማለት የሚጀምረው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ ምዕዳን በርካታ መልዕክቶችን የያዘ መሆኑ ታውቋል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለው የቫቲካን ሬዲዮ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክፍል የሥራ ባልደረባ፣ አቶ ፓትሪክ ሎቨት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያ ላይ የተናገሩትን መልዕክት ሲገልጽ፣ ቤተክርስቲያንም የወጣቶችን ጥንካሬ፣ አቅም እና እምነትን እንደምትፈልግ መናገራችውን ጠቅሶ ወጣቶች የደረሱበትን ቦታ ደርሰው ወደ ኋላ የቀሩት ካሉ በትዕግስት እንዲጠብቋቸው ማሳሰባቸውን ገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሕያው ክርስቶስ” በሚለው ቃለ ምዕዳናቸው በኩል ያስተላለፉት መልእክት ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆነ ታውቋል።

በቫቲካን ከተማ ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ፣ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፣ ወጣቶች፣ እምነታቸው እና ጥሪያቸውን እንዲያስተውሉ በሚሉት ርዕሶች ዙሪያ ባደረጉት ሰፊ ውይይት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅግ መርካታቸውን ገልጾ እነዚህን ሦስቱን መሠረታዊ ርዕሠ ጉዳዮችን ቅዱስነታቸው በዘጠኝ ምዕራፎች ከፍለው መመልከታቸውን አቶ ሎቨት አስታውቀዋል።

ምዕራፍ አንድ፦ የእግዚአብሔር ቃል እና ወጣቶች፣

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉት መጽሕፍት በዕድሜ ማነስ ምክንያት ለወጣቶች ይህ ነው የሚባል ሥፍራ አለመስጠታቸውን እንደምሳሌ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ ግን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስለሚመለከተው በዕድሜ ማነስ ወይም መጨመር ላይ ትኩረትን እንዳልተሰ፣ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ መገኘት ሊሰጥ ከሚገባው ትኩረት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስታውሰዋል።

ምዕራፍ ሁለት፦ ኢየሱስ ሁል ጊዜ ወጣት ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ኢየሱስ ሕያው በመሆኑ እርሱ የመሠረታት ቤተክርስቲያንም ወጣት ሆና እንድትጓዝ የሚፈልግ መሆኑን አስረድተው አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ቤተክርስቲያን ወጣት መሆኗን መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸው ይህም ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ከማዳመጥ ይልቅ የምትፈርድባቸው ሆና ስለምትገኝ ነው ብለዋል።

ምዕራፍ ሦስት፦ እግዚአብሔር ወጣቶችን ለዛሬም ጭምር እንዲሆኑ ጠርቶአቸዋል፣

ወጣቶች የነገ ብቻ ሳይሆኑ የዛሬም ተስፋ ናቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ዛሬ በማበርከት ላይ የሚገኙት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ብለው ወጣቶች የነገ ተስፋ ናቸው እየተባለ መጠቀሱ ወጣቶችን እንደማያስደስታቸው ገልጸዋል። ወጣቶችን የሚያጋጥሟቸው በርካታ ማሕበራዊ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው ከእነዚህም መካከል ስደት፣ ጭቆና፣ የጾታ ጥቃት እና የዲጂታል ዓለም አወንታዊ እና አሉታዊ ገጽታዎች እንደሆኑ ተናገረው የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ጥረታቸው ቢታከልበት የጨለማ ጊዜ ተወግዶ ብርሃን ሊመጣ እንደሚችል አስረድተዋል።

ምዕራፍ አራት፦ ሦስት ዋና ዋና እውነቶች፣

ሦስት እውነቶች እንዳሉ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር ወጣቶችን እንደሚወድ፣ በምህረቱ ብዛት ለድነት እንደሚያበቃቸው እና ሕያው በመሆኑ ከወጣቶች ጋር አብሮ በመጓዝ በሕይወታቸው የሚረዳቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ምዕራፍ አምስት፦ ምርጫ የሚደረገበት ዕድሜ፣

የወጣትነት ሕይወት የሕይወት ምርጫ የሚደረግበት ጊዜ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው ወጣቶች ስህተትን መፍራት እንደሌለባቸው ተናግረው፣ ለጋራ ጥቅም ወይም እድገት ዛሬ በርትተው መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ወጣቶች ለውጥን የሚያመጡ ቆራጥ መልዕክተኞች ናቸው ብለዋል።

ምዕራፍ ስድስት፦ የወጣቶች እና የአዛውንት ግንኙነት፣

ወጣቶች ከአዛውንት ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ወጣቶች ከዕድሜ ባለጸጎች ሊቅስሙ  የሚችሉት በርካታ ልምዶች እንዳሉ ገልጸው አዛውንት በተግባር እንዲተረጎምላቸው የሚፈልጉትን ነገር ወጣቶች እውን የማድረግ አቅም እንዳላቸው አስረድተዋል።

ምዕራፍ ሰባት፦ የወጣቶች አገልግሎት፣

ለወጣቶች የሚሰጥ አገልግሎት የወጣቶችን ተሳትፎ እና ከወጣቶች ጋር መጓዝን የሚጠይቅ እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ አዳዲስ መንገዶችን ለይቶ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ወጣቶች በስነ ጥበብ፣ በስፖርት እና በአካባቢ ጥበቃን እና በሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፍም በንቃት መሳተፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ምዕራፍ ስምንት፦ ጥሪ

ወጣቶች ለተጠሩበት የሕይወት መንገድ ትክክለኛ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ቅዱስነታቸው ወጣቶችን ከሚደርሳቸው ጥሪዎች መካከል አንዱ የጋብቻ ሕይወት እንደሆነ ገልጸው የጋብቻ ሕይወት ፍቅር የሚገለጥበት የሰው ልጅ ሕይወት የሚባዛበት እንደሆነ ገልጸው ሌላው የሕይወት ጥሪ ራስን ለእግዚአብሔር እና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ማዋል እንደሆነ ገልጸዋል።

ምዕራፍ ዘጠኝ፦ በጥበብ ማስተዋል፣

ወጣቶች የማስተዋል ጥበብ እንዲኖራቸው ያሳስሰቡት ቅዱስነታቸው፣ ጥሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ ስጦታ እንደሆነ ገልጸው በጥበብ እና በማስተዋል ቆራጥ ውሳኔ የሚደረግበተ እንደሆነ አስረድተው ወጣቶች የሕይወት ጉዞአቸውን ሳያቋርጡ በርትተው እንዲጓዙ እና ወደ ኋላ የሚሉም ካሉ እንዲያበረታቱ አደራ ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
02 April 2019, 18:15