ፈልግ

ቅዱስነታቸው ከስፖርት ማሕበራት ተወካዮች መካከል አንዱ ጋር፣ ቅዱስነታቸው ከስፖርት ማሕበራት ተወካዮች መካከል አንዱ ጋር፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የስፖርት ማሕበራት በመካከላቸው የሕብረት መንፈስ እንዲያሳድጉ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 7/2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቄለሜንጦስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ 120 ለሚደርሱ የኢጣሊያ ብሔራዊ ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ከዚህ በታች የሠፈረው ጽሑፍ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስፖርት ማሕበራት ተወካዮች ያደረጉት ንግግር ሙሉ ትርጉም ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ወድ ወዳጆቼ!

ከፕሬዚደንታችሁ ጀምሮ ለሁላችሁም እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሰላምታዬን እያቀረብኩ ላደረጋችሁልኝ ንግግር ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እዚህ የተገኛችሁት የኢጣሊያ ብሔራዊ የአትሌቲክስ ስፖርት ማሕበራትን በመወከል ነው። ከክፍለ ሀገር የአትሌቲክስ ማሕበራት ጀምሮ በሚገኙት ልዩ ልዩ አሥራ አንድ የእግር ኳስ ዲቪዚዮኖች መካከል አምስቱ የልጃ ገረዶች እግር ኳስ ማሕበራት እና የባሕር ዳርቻ እግር ኳስ ማሕበራት ናቸው። ከዚህም በላይ ሊጉ አሥራ ሁለት ሺህ ንዑስ ማሕበራትን የሚገኙበት እና አንድ ሚሊዮን አባላት ያሉበት ነው። ይህም ማሕበራችሁ ለእግር ኳስ ስፖርት ያለውን ፍቅር እና በዚህ ስፖርት አማካይነት የእርስ በእርስ ግንኙነትን እና ትውውቅ በማሳደግ እንዲሁም የመዝናኛ መንገድ በመፍጠር እያንዳንዱ ሰው እድገትን እንዲያመጣ ትልቅ አስተዋጽዖ የሚደረግበት ነው።       

ማሕበራችሁ የተመሠረትበትን 60ኛ ዓመት በምታከብሩበት በአሁኑ ወቅት፣ እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ ልምዶችን እንደሰበሰባችሁ፣ ብዙ ትምህርቶችን እንደወሰዳችሁባቸው እያረጋገጣችሁ፣ በርካታ ውድድሮችን በመሳተፍ፣ እነዚህን ውድድሮች ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅቶችን እንዳደረጋችሁ፣ በዚህም ለኢጣሊያ የስፖርት ማሕበራት ለማሳደግ የተጣለባችሁትን የሃላፊነት ሚና በመወጣት በተለይም ወጣቶችን በማሰልጠን በኩል ያደረጋችሁት ሚና በመሆኑ ሊደነቅ እና ሊበረታታ ይገባል።

የምንገኝበትን የባሕል እና የማሕበራዊ ፈጣን ለውጥን የተመለከትን እንደሆነ ስፖርት በእያንዳንዱ የማሕበረሰብ አባላት በተለይም በወጣቱ ሕይወት ላይ ያሳየው ከፍተኛ ለውጥ መኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል። ስፖርት በመሠረቱ የተጀመረው ጉዞ ሳይቋረጥ እስከ ፍጻሜው ማድረስን እና የሚገኝበትን እርካታ ለመካፈል የሚያስችል ግልጽ ዓላማ ያለው መሆን አለበት እንጂ ዓላማ የሌለው ከሆነ ግን ያለ ግብ ከንቱ ልፋት ሆኖ ይቀራል። በየዕለቱ ጥረት እንድናደርግ እና እንድንለፋ የሚያደርገን ዓላማ ሊኖር ይገባል። ሁል ጊዜ አመርቂ ውጤትን ማስመዝገብ ባይቻልም በየዕለቱ የምናደርጋቸው ጥረቶች ወደ የት እንደሚያደርሱን በግልጽ ማወቅ ያስፈልጋል። የያዝነው ዓላማ ከመጀመሪያው አንስቶ በየቀኑ ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ምን እየሠራን እንዳለ በሚገባ ለማወቅ እና መልካም ውጤትን ለማስመዝገብ የሚረዱ መንገዶችን ለይተን እንድናውቅ ያደረገናል።  

ብዙ ጊዜ እና ጉልበት የሚፈስበት የስፖርት ጨዋታ ቴክኒካዊ ችሎታን ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለውን ልምምድ፣ ቆራጥነትን፣ ትዕግስትን፣ ሽንፈትን በደስታ መቀበልን፣ ዝግጁ መሆንን፣ የቡድን መንፈስን፣ ተግባብቶ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። አንድ ጎበዝ ተጫዋች እነዚህ እሴቶች በሙሉ ሊኖረው ይገባል። አለበለዚይ በጨዋታ ወይም በውድድር ጊዜ የሚያጋጥሙትን በርካታ ችግሮችን በቀላሉ መሻገር አይችልምና።

እነዚህን ሕጎች በሚገባ የተገነዘበ፣ የሚያከብር እና ለማሳደግም ጥረት የሚያደርግ ብሔራዊ የስፖርት ሊግ የስፖርት እሴቶችን የራሱ አድርጎ በመቁጠር ደንቦችን በማክበር፣ የጨዋታ ስርዓቶችን በትክክል በመከተል፣ ስፖርታዊ ጨዋነትን በማስመስከር እና ለሚገጥመው ወገንም አክብሮትን መስጠት ይችላል። በውድድር ወቅት እነዚህን ደንቦች ማክበር እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ ግን ቀላል አይሆንም።           ከአካላዊ ስልጠና በተጨማሪ የመንፈሳዊ ሕይወት ልምምድ መኖርን ይጠይቃል። ምክንያቱም እያንዳንዳችን የአካል እና የአዕምሮ አንድነት ስላለብን፣ አንዱ የሌላውን ፍላጎቶች ችላ ማለት ስለማይችል ነው።

የአንድ ስፖርት ሰልጣኞች አንድ ቀን ፕሮፌሽናል ተጫዋች በሚሆንበት ጊዜ ልቡ ውስጥ የሚፈጥረው ደስታ ለሚያዘወትረው የስፖርት ዓይነት ሕይወትን የሚሰጥ ይሆናል። በዚህ ውስጣዊ ደስታ በመነሳሳት ለመልካም ውጤት ሊበቃ ይችላል። የመልካም ስኬት ምኞት ወደ ደስታ የሚለወጥ ከሆነ ወይም በተቃራኒው ተጋጣሚውን በመናቅ ጤናማ የፉክክር መንፈስ ማሳየት ያቆሙ ከሆነ ትክክለኛ የውድድር መንገድን አልተከተሉም ማለት ነው።

በዛሬው ዕለት ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ከስፖርታዊ ጨዋታ የሚገኘውን ደስታ ተንከባክባችሁ በመያዝ ለደጋፊዎቻችሁ እንድታስተላልፉ አደራ እላለሁ። የምትከተሉት ስፖርታዊ ጨዋነት ለሚከተሏችሁ  ደጋፊዎች መልካም ምስሌ እንደሚሆን በማወቅ አዎንታዊ ተጽዕኖን እንዲያስከት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በመሆኑም ከደጋፊዎቻችሁ ጋር ባላችሁ ስፖርታዊ ግንኙነት አማካይነት በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ መልካም እና ሰላማዊ ግንኙነትን በመፍጠር ለሰዎችም ትኩረትን የሚሰጥ መሆን ይስፈልጋል።

ማሕበራዊ እና ባሕላዊ እድገትን ያማከለ እና መተሳሰብ ያለበት የአንድነት መንፈስ መኖር ማለት ሽንፈት ላጋጠመው አስፈላጊ ድጋፍን ማድረግ፣ የሚያነክስ ካለ አደጋ እንዳጋጠመው በመገንዘብ እርዳታን ማድረግ ማለት እንደሆነ፣ ሌላው ቀርቶ የአሸናፊነት ሽልማት ለመቀበል የበቃም ቢሆን ብቻውን መጓዝ እንደማይችል መገንዘብ ማለት ነው።

“እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና” (ማቴ. 20፤16) ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ እንደሚያስተምረን ኢየሱስ ማንም ሰው ሊያገኝ የሚገባውን ሽልማት እንዲያጣ አይፈልግም ነገር ግን ማድረግ ያለበትን ጥረት በሙሉ ፍልጎት እንዲያከናውኑ ይፈልጋል። ይህ ማለት በጥቃቅን ነገሮችም እንኳን ሳይቀር ውበቱን እና የራሳችን ውስንነት ለመቀበል መሞከር ማለት እንደሆነ ይነግረናል።

በስፖርታዊ አቋማችሁ ወይም ሥራችሁ ውስጥ እውነተኛ ዓላማችሁ ምን እንደሆነ፣ ግባችሁም የት ላይ እንደሆነ በግልጽ ለይታችሁ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህን ካወቃችሁ ዘወትር ብርቱዎች፣ ይበልጥ ታማኞች እና የሌሎች ሰዎች ወዳጅ መሆን ትችላላችሁ። እያንዳንዳችሁ በግል ሆነ በማሕበር ሆናችሁ የምታደርጉትን ጉዞ እግዚአብሔር እንዲያግዝ በጸሎቴ እጠይቀዋለሁ። እናንተም በጸሎታችሁ እንድታስታውሳችሁ አደራ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ"።       

15 April 2019, 18:38