ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ፋሲካ በእኛ ላይ ተጭነው የሚገኙ ድንጋዮችን የምናስወግድበት በዓል ነው”!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በትላንታናው እለት ማለትም በሚያዝያ 12/2011 ዓ.ም ምሽት ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት የትንሳሄ በዓል ዋዜማ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእርሳቸው መሪነት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ተከብሮ ማለፉን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅት ቅዱስነታቸው ባሰሙት ስብከት “ተስፋችሁን የሚያደናቅፉትን ድንጋዮችን ከሕይወታችሁ አስወግዱ” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደርጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ሴቶቹ ሽቶ ይዘው ወደ መቃብሩ ሥፍራ ሄዱ፣ ነገር ግን በመቃብሩ ላይ ተከድኖ የነበረው ድንጋይ ትልቅ በመሆኑ የተነሳ ወደ እዚያ ያደርጉት ጉዞ ምንም ፋይዳ የለውም የሚል ስጋት ገባቸው። እነዚያ ሴቶች ያደርጉት ጉዞ የእኛን ጉዞ ያመለክታል፡ ዛሬ ማታ ወደ ደህንነት መንገድ ካደረግነው ጉዞ ጋር ይመሳሰላል።

በእዚህ ውስጥ የሚገኙት የፍጥረት ውበት ከኀጢአት ድራማ ጋር፣ ከባርነት ቀንበር ውስጥ ነጻ መውጣት ለቃልኪዳን ታማኝ ካለመሆን ጋር፣ የነቢያት ተስፋዎች ሕዝቡ ከነበረው አሳዛኝ የግድዬለሽነት መንፈስ ጋር ተቃራኒ ሆኖ በመቅረብ በዚህ ድንጋይ ላይ ወድቀው ተሰባብሮ የሚቀሩ ይመስላሉ። እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያ ታሪክ እና በእያንዳንዳችን ታሪክ ውስጥ የታቀዱ እርምጃዎች በዚህ መልኩ ግባቸው ላይ የማይደርሱ ሊመስለን ይችል ይሆናል። ስለዚህ በዚህ መንፈስ የሚከስተው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ጨለማ የሆነ የሕይወት ሕግ ነው የሚል ሐሳብ ሊፈጥር ይችላል።

ፋሲካ በእኛ ላይ ተጭነው የሚገኙ ድንጋዮችን የምናስወግድበት በዓል ነው።

ይሁን እንጂ ዛሬ የእኛ መንገድ ከንቱ እንዳልሆነ እና በመቃብር ላይ ከነበረው ከአንድ ድንጋይ ጋር የምናደርገው ልትሚያ እንዳልሆነ እንረዳለን። “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? (ሉቃስ 24፡5) የሚለው አንድ ዓረፍተ ነገር ሴቶቹን በማንቀጥቀጥ ታሪካቸውን ይቀይራል፣ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፣ በእኛ ላይ ተጭኖ የሚገኘውን ድንጋይ ማንም ሰው ለማንሳት አይችልም ብለን የምናስበው ለምንድነው? በዚህ የተነሳ ለምንድነው ወደ ተስፋ መቁረጥ እና ወደ ውድቀት የምናመረው? ፋሲካ በእኛ ላይ ተጭነው የሚገኙ ድንጋዮችን የምናስወግድበት በዓል ነው። ተስፋዎቻችንን እና ለወደፊት የምንጠብቃቸውን ነገሮች የሚያኮላሹትን የሞት፣ የኃጢአት፣ የፍርሃት፣ የዓለማዊነት. . . ወዘተ የመሳሰሉ በጣም ጠንካራ የሚባሉትን ድንጋዮችን እግዚአብሔር ከእኛ ላይ አሽቅንጥሮ ያወርዳል።

በልባችን ውስጥ የሚገኙትን ድንጋዮች አውጥተን መጣል ይኖርብናል

የሰው ልጅ ታሪክ በአንድ በመካነ መቃብር ሥፍራ ላይ በሚገኝ ድንጋይ ፊት ለፊት የሚጠናቀቅ ታሪክ አይደለም፡ ምክንያቱም ዛሬ “ሕያው የሆነውን ድንጋይ” (1 ጴጥሮስ 2፡4) አግኝቱዋልና። ኢየሱስ ከሙታን ተነስቱዋል። እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን በእርሱ ላይ ተመስርተናል፣ ምንም እንኳን ልቦናችንን ብናጣ፣ ውጤታማ ባለመሆናችን የተነሳ በሁሉም ነገር ላይ የመፍረድ ዝንባሌ እና ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት፣ እርሱ ነገሮችን በአዲስ መልክ ይለውጣል፣ ተስፋ የቆረጠውን ስሜታችንን መልሶ ያነሳሳል። ዛሬ ምሽት እያንዳንዳችን ሕያው በሆነው በእርሱ አማካይነት በልባችን ውስጥ የሚገኙትን ባጣም ከባድ የሚባሉትን ድንጋዮች አውጥተን መጣል ይኖርብናል። በቅድሚያ ግን ከእኔ ሊወገድ የሚገባው ድንጋይ የቱ ነው? ምንስ ተብሎ ይጠራል? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።

ተስፋችሁን በፍጹም አትቅበሩ!

ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርገንን ድንጋይ ከሕይወታችን ማስወገድ ይኖርብናል። ከዚህ በፊት የሰራናቸው ነገሮች ሁሉ ስህተት እንደነበሩ፣ ክፋት ምንም ዓይነት ማብቂያ የለውም የሚል የከፋ ሐሳብ ሲነሳ፣ ሞት ከሕይወት የላቀ ጉልበት አለው ብለን ወደ ማመን ላይ ስንደርስ፣ ስንኩሎች እና የሚሳለቁብን ስንሆን ጤናማ ያልሆነ ተስፋ መቁረጥ ያስከትላል። እርካታ በማጣታችን የተነሳ በውስጣችን ድንጋይ በድንጋይ ላይ በመገንባት በምንሰራው የመካነ መቃብር ስፍራ ውስጥ የተስፋችን መቀበሪያ ሥፍራ ይሆናል። ስለ ሕይወት ያለንን ቅሬታ በማሰማት ሕይወታችን በቅሬታችን ላይ መሰረቷን እዳደረገች አድርገን በምናስብበት ወቅት መንፈሳዊ የሆነ ሕመም ያጋጥመናል። ስለዚህም የመካነ መቃብር ሥፍራ ስነ-ልቦና የሚገነባው በዚሁ መልኩ ነው፣ ሁሉም ነገር በእዚያው ይጠናቀቃል፣ ከዚያ በሕይወት የመውጣት ተስፋ በዚያው ያበቃል። ነገር ግን በዚህ የፋሲካ በዓል ለእኛ የሚቀርብልን ጥያቄ፡ “ለምንድነው ህያውን ከሙታን መካከል የምትፈልጉት? የሚለው ሊሆን ይገባል። ጌታ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆኖ አልኖረም። ከሙታን ተነስቱዋል፣ በእዚያ ስፍራ የለም፣ እርሱ በፍጹም በማይገኝበት ሥፍራ እርሱን አትፈልጉት፣ እርሱ የሙታን አምላክ አይድለም ነገር ግን የሕያዋን አምላክ ነው። ተስፋችሁን በፍጹም አትቅበሩ!

ኃጥያት ያማልላል

ብዙን ጊዜ ልባችን የተዘጋ ሆኖ እንዲኖር የሚያደርግ ሁለተኛ ድንጋይ አለ፡ ይህም ኃጢአት ነው። ኃጥያት ያማልላል፣ ቀላል እና ዝግጁ የሆኑ ነገሮችን ያቀርብልናል፣ ደህንነትን እና ስኬትን እንደሚያመጣ ቃል ከገባልን በኋላ ግን በውስጡ ብቸኝነትን እና ሞት ይዞልን ከተፍ ይላል። ኃጥያት ማለት በሞት መካከል ሕይወትን መፈለግ ማለት ነው፣ በሚያልፉ ነገሮች ውስጥ ሕይወትን መፈለግ ማለት ነው። ለምንድነው ሕያው የሆነውን በሙታን መካከል የምትፈልጉት? በልባችን አፋፍ ላይ የተቀመጠውን እና መለኮታዊ የሆነ ብርሃን እንዳይገባ የሚከለክለውን የኃጥአት ድንጋይ ለመተው ለምን አትወስንም? ገንዘብ በሚያወጣው ነበልባል የተነሳ የሚያንጸባርቁ ነገሮችን፣ ኩራትን እና ጊዜያዊ ደስታን የሚሰጡ አጓጊ ነገሮችን አስወግድህ በምትኩ እውነተኛ ብርሃን የሆነውን ኢየሱስን ልምን አትይዘውም? ዓለማዊ ለሆኑ ኩራቶች መኖር ሳያሆን ነገር ግን ለኢየሱስ ብቻ ነው የምኖረው ብለህ የማትናግረው ለምንድነው?

በሐዘናችን ወቅት ጌታ በውስጣችን እንዲገብ ልንፈቅድለት የገባል

ወደ ኢየሱስ መካነ መቃብር እየሄዱ ወደ ነበሩ ሴቶች እንመለስ። በመቃብሩ ስፍራ ላይ የነበረው ድንጋይ ተነስቶ በማየታቸው ተገረሙ፣ መልአክቱን በተመለከቱበት ወቅት “በፍርሃት ተዋጡ” ይለናል ቅዱስ ወንጌል፣ በዚህም የተነሳ በመሬት ላይ አቀርቅረው ነበር። እነርሱ ቀና ብለው ወደ ላይ ለመመልከት ድፍረቱ አልናበራቸው። በእኛ ሕይወት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንዲህ ተከስቶ ይሆን! ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር በሚገጥመን ወቅት ወደ ታች ማቀርቀር እንመርጣለን፣ በፍርሀት ለመደበቅ እንሞክራለን፣ በፍርሃት አቀርቅረን መደበቅ እንመርጣለን። እንግዳ የሆነ ነገር ነው፣ ታዲያ ለምንድነው እርሱ እንዲህ የምናደርገው? ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ራሳችንን በራሳችን ዝግ ስናደርግ እና በሐዘናችን ወቅት ብቸኛው ተዋንያን የምንሆነው እኛ ራሳችን ብቻ በመሆኑ የተነሳ ሲሆን በውስጣችን ጌታ ይገባ ዘንድ ከመፍቀድ ይልቅ በጨለማ ክፍሎች ውስጥ ሆነን ብቻችንን መቆየት ስለሚቀለን ነው። እርሱ ብቻ ነው ይህንን የሚያውቀው። አንድ ገጣሚ “ተነስተን እስከ ምንቆም ድረስ የቁመታችንን ትክክለኛ ርዝመት አናውቅም” ትል ነበር። ቃሉ ላይ ተመርኩዘን ወደ ላይ በመመልከት እኛ የተፈጠርነው ለሰማይ እንጂ ለምድር እንዳልሆነ እንድንገነዘብ፣ ጌታ ካለንበት ቦታ እንድንነሳ ይጠራናል፣ ለሕይወት ሕልውና እንድንቆም እንጂ ለሞት እንድንበረከክ አይፈልግም፣ ለምንድነው ሕያው የሆነውን በሙታን መካከል የምትፈልጉት? ይለናል።

ኢየሱስ ሞታችንን በሕይወት ለወጠ

እግዚአብሔር እርሱ ሕይወትን በሚመለከትበት መልኩ እኛም ሕይወትን እንድንመለከት ይፈልጋል፣ እርሱ ሁል ጊዜ በእያንዳንዳችን ውስጥ በጣም ውብ የሆነ ነገር ይመለከታል። ኃጢአት በምንሰራበት ወቅት ዳግመኛ መነሳታችንን ይመለከታል፣ ከሙታን መካከል ደግሞ የሚነሱ ወንድሞቹ እንደ ሆንን አድርጎ ይመለከታል፣ ታዛዥ በማንሆንበት ወቅቶች ደግሞ ሊያጽናናን ይፈልጋል። እንግዲያውስ አትጨነቁ፡ ጌታ የአንተን ሕይወት ይወዳል፣ ምንም እንኳን አንተ ሕይወትህን መመልከት ቢከብድህ በእጅህ ሕይወትህን ማቆየት ቢከብድህም እርሱ ሕይወትህን ይወዳል። በፋሲካ በዓል ምን ያህል እንደ ሚወድህ አሳይቶኃል፣ ሁሉንም መከራ በማለፍ፣ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ውስጥ በመግባት፣ በብቸኝነት ስሜት ውስጥ በማለፍ፣ በመሞት እና በድል ለመነሳት ወደ መቃብር ውስጥ በመግባት “አንተ ብቻህን አይደለህምና በእኔ ተማመን!” ሊልህ ፈለገ። ኢየሱስ ሞታችንን በሕይወት፣ ስቆቃችንን ደግሞ በደስታ የመለወጥ ችሎታ ተክኑዋል። ከእርሱ ጋር በመሆን እኛም ፋሲካን ማለትም መሸጋገርን እውን ማደርግ እንችላለን፣ ከብቸኝነት ወደ ኅበረት፣ ከመጥፋት ወደ መዳን፣ ከፍርሃት ወደ መተማመን እንሸጋገራለን። በፍራሃት እና በትካዜ መንፈስ ወደ ምድር አቀርቅርን መቆየት የለብንም፣ በአንጻሩ ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ ቀና ብለን እንመልከት፣ የእርሱ እይታ ተስፋችን እንዲለመልም ያደርጋል፣ ምክንያቱም እኛ ሁል ጊዜ በእርሱ የተወደድን መሆናችንን እና እኛ እንኳን ይህንን የእርሱን ፍቅር በሌላ ለመቀየር ብንሞክርም የእርሱ ፍቅር ግን ፈጽሞ እንደ ማይቀር ይነግረናል። ይህም ለድርድር የማይቀርብ የሕይወታችን ክፍል ነው፣ የእርሱ ፍቅር መቼም ቢሆን አይቀየርም። በሕይወታችን ውስጥ “ወደ የት ነው የምመለከተው?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። በመቃብር ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ላይ ነው የማሰላስለው ወይስ ደግሞ ሕያው የሆኑ ነገሮችን ነው?

እምነታችን የቤተ መዘክር እምነት ሆኖ እንዳይቀር መጠንቀቅ ይኖርብናል

ሕያውን ስለምን ከሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? ሴቶቹ የመላእክቱን ጥሪ ያዳምጣሉ፡ እርሱም “እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ” (ሉቅስ 24፡6) አላቸው። እነዚያ ሴቶች ተስፋቸውን የቆረጡበት ምክንያት ኢየሱስ በገሊላ የተናግረውን ቃል ባለማስታወሳቸው ነበር። ይህንን በመዘንጋታቸው የተነሳ ነበር ባዶ የሆነውን የኢየሱስን መቃብር በመመልከት እያዘኑ የነበሩት። እምነት ግን ወደ ገሊላ መመለስን ይጠይቅ ነበር፣ ኢየሱስ በመጀመሪያ ደረጃ ያሳየው ፍቅር እንዲያንሰራራ ማድረግን ይጠይቅ ነበር፡ ይህም በግርድፉ እምነት ወደ ገሊላ ተመልሶ መሄድን ይጠይቅ ነበር፣ ኢየሱስ በመጀመሪያ ደረጃ ወደ አሳየው ፍቅር መመለስን ይጠይቃል፣ ይህም በግርድፉ በሙሉ ልብ ወደ እርሱ መመለስ እንዳለብን ማስታወስ ማለት ነው። ከጌታ ጋር በመሆን ወደ እርሱ ፍቅር መመለስ መሰረታዊ የሆነ ነገር ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን እምነታችን የፋሲካ እምነት ሳይሆን የቤተ መዘክር እምነት ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። ኢየሱስ ግን ባለፈው ዘመን የነበረ ስብዕና ሳይሆን ዛሬ በዛሬ ዘመን ሕያው ሆኖ የሚገኝ ነው፣ እርሱን በሚገባ ማወቅ የምንችለው በታሪክ መጽሐፍት ውስጥ ሳይሆን ነገር ግን እለታዊ በሆነ ሕይወት ውስጥ ነው። ኢየሱስ በጠራን ወቅት የነበረንን እውነታ እናስታውስ፣ በጨለማችን ላይ፣ በትዕቢተኛነታችን ላይ፣ በኃጢአታችን ላይ ድል በተጎናጸፈበት ወቅት በቃሉ አማካይነት እንዴት ልባችንን ነክቶ እንደ ነበረ እናስታውስ።

ሴቶቹ ቀደም ሲል ኢየሱስ የተናገራቸውን ነገሮች ያስታወሱት መቃብሩን ትተው እየሄዱ በነበሩበት ወቅት ነበር። አማኞች ከፋሲካ በዓል መማር የሚኖርባቸው ነገር ቢኖር በመካነ መቃብር ስፍራ ለአፍታ ቆም ማለትን ነው፡ ምክንያቱም ይህ ድርጊት ሕያው ወደ ሆነ ጎዳና የሚወስደንን መንገድ እንድንከተል ስለሚረዳን ነው። በሕይወቴ ውስጥ ወደ የት እየተጉዝኩኝ ነው? ብለን እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ። አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም መቼም ቢሆን ወይም ፈጽሞ ከእኛ ወደ ማይሉ ችግሮቻችን የምንጓዝ ሲሆን ወደ ጌታ የምንሄደው ደግሞ በዚህ መንገድ እንዲያግዘን ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ላይ የምንጓዝ ከሆንን ግን ወደ ኢየሱስ የመሩን ችግሮቻችን ናቸው እንጂ እኛ ራሳችን በገዛ ፈቃዳችን ወደ እርሱ ለመሄድ አልተነሳንም ማለት ነው። ይህም ሕያው የሆነውን በሙታን መካከል ሁልጊዜ እንደ መፈለግ ይቆጠራል። ጌታን ከተገናኘነውም በኋላ በሐዘን ውስጥ፣ በፀፀት ውስጥ፣ በቁስል ውስጥ በምንኖርበት ወቅት እና እርካታ ባጣንባቸው ጊዜያት ሁሉ እነዚህን ነገሮች እንዲለውጣቸው ለእርሱ ከመተው ይልቅ በሙታን መካከል እርሱን በመፈለግ የተመላለስነው ምን ያህል ጊዜ ይሆን! በኃጢአት ድንጋዮች ላይ ወድቀን እንዳንፈጠፈጥ፣ እምነታችንን እንድናጣ እና በፍርሃት ጎድና ላይ እንዳንመላለስ እንዲረዳን፣ በተጨማሪም በችግሮች ማዕበል እንዳንወሰድ እንዲረዳን የእርሱን ጸጋ እንጠይቅ።

በሁሉም ነገር እና ከሁሉም በላይ እርሱን እንፈልገው። ከእርሱ ጋር ከሞት እንነሳለንና!

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 April 2019, 12:30