ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ኢየሱስ በትንሳኤው የሰላም፣ የደስታ እና የተልዕኮ ስጦታ አበርክቶልናል” አሉ።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የዳግማዊ ትንሳኤ በዓል  በሚያዝያ 20/2011 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ የዳግማዊ ትንሳኤ እለተ ሰንበት “የመለኮታዊ ምሕረት ሰንበት” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህንን እለተ ሰንበት ለማክበር በማሰብ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ባደርጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት “ከሙታን የተነሳው ጌታ ለእኛ ለደቀ-መዛሙርቱ የሰላም፣ የደስታ እና የተልዕኮ ስጦታ አበርክቶልናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 20/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በወቅቱ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት የተነበበል ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 20፡19-31) በፋሲካ እለት ምሽት ላይ በፍርሃት ተውጠው የሚኖሩበትን ቤት በር ቆልፈው በውስጡ ተቀምጠው ለነበሩ ለደቀ-መዛሙርቱ በተገለጸላቸው ወቅት ስጥቶዋቸው ስለነበረው ሦስት ሥጦታዎች ማለትም ሰላም፣ ደስታ እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ይተርካል።

በመጀመሪያ የተናገራቸው ቃላት "ሰላም ለእናንተ ይሁን" (ቁ .21) የሚለው ቃል ነበር። ከሞት የተነሳው ጌታ እውነተኛውን ሰላም ይሰጣል ምክንያቱም በመስቀል ላይ በመሰዋቱ እግዚኣብሔርን እና የሰው ልጆችን አስታርቁዋል፣ ኃጢአትን እና ሞትን ድል በማድረጉ የተነሳ ነው። ይህ ሰላማችን ነው። በቅድሚያ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ይህ ጸጋ በጣም ያስፈልጋቸው ነበር፣ ምክንያቱም ጌታ ተይዞ ከተወሰደ በኋላ እና የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ግራ ተጋብተው እና በፍርሃት ተውጠው ፈርተውም ሰለነበረ ነው። ኢየሱስ በመካከላቸው ሕያው ሆኖ ይቀርባል፣ ቁስሎቹን ለእነርሱ በማሳየት፣ በክብር የተሞላ ሰውነቱን በማሳየት፣ የድል አድርጊነቱ ፍሬ የሆነውን ሰላም ይሰጣቸዋል። በዚያ ምሽት ግን ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ስለዚህ አስደናቂ ክስተት በተነገረው ጊዜ በሌሎቹ ሐዋርያት ፊት አለማመኑን ገልጾ ማመን ይችል ዘንድ የሚረዱትን እውነታዎች እና ማረጋገጫዎችን በግልጽ ማየት እንደ ፈለገ ይናገራል። ከስምንት ቀናት በኋላ ልክ እንደ ዛሬው ማለት ነው ኢየሱስ እንደ ገና በአዲስ መልክ ይገለጽላቸዋል፡ የኢየሱስን ከሙታን መነሳት ማመን ተስኖት የነበረውን ቶማስን ያገኘዋል ቁስሉን እንዲነካ ይጋብዘዋል። እነዚህ ቁስሎች የሰላም ምንጭ ናቸው፣ ምክንያቱም የጠላት ኃይል የሆኑትን ማለትም ኃጢአት፣ ክፋትንና ሞትን ያሸነፈው የኢየሱስን ጥልቅ ፍቅር የሚያመለክቱ ናቸው። እነዚህን ቁስሎች እንዲነካ ይጋብዘዋል። ኢየሱስ ሁላችንንም "ሰላም የሌለህ ሰው ከሆንክ ቁስሎቼን ንካ” ብሎ መናገሩ በራሱ ለእኛም የሚሆን ትምህርት ነው።

የኢየሱስን ቁስሎች በብዙ ችግሮች ውስጥ፣ በመከራ ውስጥ፣ በስደት ውስጥ፣ በበሽታ ምክንያት የሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ ይህንን ቁስል ሊነኩ ይገባል። አንተ ሰላም የሌለህ ሰው ነህ? እንግዲያውስ የኢየሱስ ቁስል ምልክት የሆነውን አንድ ሰው ለመጎብኘት ሂድ። በዚያም የኢየሱስን ቁስል ንካ። ከእነዚያ ቁስሎች ውስጥ ምሕረት ይፈልቅልሃል። የዛሬው እለተ ሰንበት የምሕረት ሰንበት በመባል የሚታወቀው በዚሁ ምክንያት የተነሳ ነው። አንድ ቅዱስ የሆነ ሰው በመስቀል ላይ የተሰቀለው የኢየሱስ አካል በቆሰለው ቁስሉ አማካይነት ለሁሉም ሰዎች የሚዳረስ የምሕርተ መፍለቂያ ነው ይል ነበር። እንደ ሚታወቀው ሁላችንም የእግዚኣብሔር ምሕረት ያስፈልገናል። ወደ ኢየሱስ በመቅረብ በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንን ቁስል መንካት ይኖርብናል። የኢየሱስ ቁስሎች የተከበሩ ነገሮች ናቸው፦ ምክንያቱም ከእነርሱ ውስጥ ምሕረት ይፈልቃልና። የኢየሱስን ቁስሎች ለመንካት ብርታት ይኑረን። እነዚህን ቁስሎች ይዞ በአብ ፊት ቆሞ ለአባቱ "አባት ሆይ እነዚህ ቁስሎች ለወንድሞቼ ስል የከፈልኩት ዋጋ ነው” በማለት ኢየሱስ በአባቱ ፊት ያቀርባቸዋል። ኢየሱስ በቁስሎቹ አማካይነት በአብ ፊት ቆሞ ያማልዳል። ወደ እርሱ ብንቀርብ እርሱ ምሕረቱን ይሰጠናል፣ ለእኛ ያማልዳል። ስለዚህ የኢየሱስን ቁስሎች በፍጹም መርሳት አይኖርብንም።

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለደቀ-መዛሙርቱ ያመጣላቸው ሁለተኛ ስጦታ ደስታ ነው። ወንጌላዊው “ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በተመለከቱበት ወቅት እጅግ በጣም ተደሰቱ” ይለናል። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ “ደቀ መዛሙርቱ በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ይህንን ጉዳይ ማመን ተስኑዋቸው ነበር” የሚል ጥቅስ እናገኛለን። እኛ እኮ አንድ ድንቅ የሆነ ነገር ሲከሰት. . . ጥሩ ነገር ሲከሰት ማለት ነው . . . እኛም "እኔ ይህንን ማመን አልችልም፣ ይህ ነገር በእርግጥ እውነት ነው ወይ?!" በማለት እንናገራልን። ደቀ-መዛሙርቱም እጅግ በጣም በመደሰታቸው የተነሳ ይህንን ጉዳይ ለማመን ተቸግረው ነበር። ኢየሱስ የሚሰጠን ደስታ ይህንን ይመስላል። ጭንቀት ከተሰማችሁ፣ ሰላም ከሌላችሁ፣ ኢየሱስ የተሰቀለበትን መስቀል ተመልከቱ፣ ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ ተመልከቱ፣ የኢየሱስን ቁስል ተመልከቱ ከእዚያም ያንን ደስታ ታገኛላችሁ።

ከዚያም ከሠላም እና ከደስታ በተጨማሪ ኢየሱስ ለደቀ-መዛሙርቱ የሰጠው ስጦታ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ነው። “አባቴ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” በማለት ይናገራል። የኢየሱስ ትንሳኤ የፍቅር መነሻ ጅማሬ ሲሆን ዓለምን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመለወጥ ችሎታ አለው።

በዚህ በዳግማዊ ትንሳኤ ሰንበት በእምነት መንፈስ ተሞልተን ልባችንን ለሰላም፣ ለደስታ እና ለተልዕኮ እንድናቀርብ ተጋብዘናል። ነገር ግን የኢየሱስን ቁስሎች በፍጹም መርሳት አይኖርብንም፣ ምክንያቱም ለተልዕኮ፣ ለሰላም እና ለደስታ የሚሆን ጥንካሬ የሚመጣው ከእዚያ ነውና። ይህንን ጸሎት የሰማይ እና የምድር ንግሥት በሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እናቅርብ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

28 April 2019, 15:22