ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አድረጉ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አድረጉ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አድረጉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስድስት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ ከዚህ ቀደም ሦስት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህም በላቲን ቋንቋ Evangelii Gaudium”  በአማሪኛ ሲተረጎም “በወንጌል የሚገኝ ደስታ”  በሚል አርእስት እ.አ.አ በኅዳር 24/2013 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁንም በላቲን ቋንቋ Amoris Laetitia”  በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የፍቅር ሐሴት” በሚል አርእስት እ.አ.አ. በመጋቢት 19/2016 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ በቤተሰብ ውስጥ ስለሚታዩ ተግዳሮቶች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተሰብ ማድረግ ሰለሚጠበቅባቸው ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያወሳ ድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእነዚህ ስድስት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እ.አ.አ በመጋቢት 19/2018 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ “Gaudete et Esultate” በአማርኛው “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” በሚል አርእስት ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን “በአሁኑ ዓለማችን ውስት የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ቅድስና መንገድ እንዲመለሱ የሚጋብዝ ጥሪ” የተካተተበት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሲሆን በአሁኑ ዘመን በሚገኘው ዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን፣ የተለያዩ የሕይወት ተግዳሮቶች እየገጠሙዋችሁ የምትገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም አሁን ባለው ዓለማችን ውስጥ ያለውን መልካም እድል መጠቀም ያልቻላችሁ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ልጆቻችሁን በታላቅ ፍቅር ተንከባክባችሁ እያስደጋችሁ የምትገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለቤተሰባችሁ የሚሆን እንጀራ በእየለቱ ለማግኘት የምትኳትኑ፣ የምትለፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ የምትሰሩ የማኅበረስብ ክፍሎች፣ በእድሜያችሁ ዘመኑ ሁሉ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰባችሁ ለአገራችሁ፣ በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ መልካም የሆነ ተግባር ያከናወናችሁ አረጋዊያን ሁላችሁ “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነስኮስ በአራተኛ ደረጃ ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ደግሞ ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 17/2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ሲካሄድ የነበረው 15ኛ የብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ ተካሂዶ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ጉባሄ ማጠቃለያ ሐሳብ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት የተዘጋጀ እና በመጋቢት 16/2011 ዓ. ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተፈርሞ እንዲታተም ፈቃድ የተሰጠው እና በዚህም መሰረት በመጋቢት 24/2011 ዓ. ም. ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቅዱስነታቸው በርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ለንባብ ያበቁት አራተኛው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ነው። የዚህን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አጠቃላይ ይዘት በአጭሩ እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን፣ ተከታተሉን።

ክርስቶስ ሕያው ነው

 “ክርስቶስ ሕያው ነው! እርሱ ተስፋችን ነው፣ በአስደናቂ መንገድ ወጣቶችን ወደ ዓለማችን ያመጣል።” በቅድሚያ ለእያንዳንዱ ክርስትያን ወጣቶች እነዚህን ቃላት ተጠቅሜ እንዲህ ለማለት እፈልጋለሁ፡ ክርስቶስ ሕያው ነው! እናንተም ሕያው እንድትሆኑ ይፈልጋል”። ይህ ቃል “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በቅርቡ ቅዱስነታቸው በጣሊያን ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የሎሬቶ ከተማ በጎበኙበት ወቅት ለወጣቱ እና ለአጠቃላይ የእግዚኣብሔር ሕዝብ ካስተላለፉት መልእክት የተወሰደ ነው።

ይህ “ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 9 ምዕራፎች እና 299 አንቀጾች የተካተቱበት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህንን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በተመለከተ ቀድም ሲል ይህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሎሬቶ ይፋ በሆነበት ወቅት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ይህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እ.አ.አ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ “ከተካሄደው ሲኖዶስ የመነሻ ሐሳብ ተወስዶ እና ዳብሮ የቀረበ” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑን በወቅቱ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ምዕራፍ አንድ

“የእግዚአብሔር ቃል ወጣቶች በተመለከተ ምን ይላል?"   

ምዕራፍ አንድ፡ “የእግዚአብሔር ቃል ወጣቶች በተመለከተ ምን ይላል? “ወጣቶች አድገው እስኪበቁ ድረስ ያላቸውን እድሜ እግዚኣብሔር ለየት ባለ መልኩ እንደ ሚመለከተው አንዳንድ ጥቅሶች ያሳያሉ” በማለት ቅዱስነታቸው በአንቀጽ ስድስት ላይ የጠቀሱ ሲሆን ለምሳሌ ያህል ዮሴፍ የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የነበረ ሲሆን (ዘፍጥረት 37፡2-3) ነገር ግን እግዚአብሔር በሕልሙ ታላላቅ ነገሮችን አሳየው እናም ዕድሜው ወደ ሀያ ዓመት ገደማ ሲሞላ እጅግ በጣም አስፈላጊ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ለወንድሞቹ ማብራሪያ ይሰጥ እንደ ነበር ይገልጻሉ።

በተጨማሪም በጌዴዎን ታሪክ ውስጥ ደግሞ በግልጽ የሚናገሩ ወጣቶችን ሁኔታ እንመለከታለን። ጌታ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ሲነግረው ጌዴዎን መልሶ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ?” (መሳፍንት 6፡13) ብሎ ለጌታ በግልጽ መልስ ሰጥቶ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ ነቀፋ አልተቀየመም ነበር፣ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ ‘ሂድ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ነጻ እንድ ታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” (መሳፍንት 6፡14) በማለት በአንቀጽ ሰባት ላይ አስፍረዋል።

በተመሳሳይ መንገድ እግዚኣብሔር ሳሙኤልን የጠራው ገና ትንሽ ልጅ እያለ ነበር። እርሱም የአዋቂዎችን ምክር ሰምቶ የእግዚኣብሔርን ጥሪ ለመስማት ልቡን ከፈተ “ጌታ ሆይ አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር” (1 ሳሙኤል 3፡9-10) በማለት እግዚኣብሔርን ለማዳመጥ ያለውን ዝግጁነት ገለጸ። በዚህም አዎናትዊ ምላሽ የተነሳ በአገራቸው ታሪክ ውስጥ አስጨናቂ በተባለ ወቅት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ታላቅ ነቢይ ሆነ። ጌታ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ሲጠራው ንጉሥ ሳውል ገና ወጣት ነበር (1 ሳሙኤል 9፡2) አንቀጽ ስምንት ላይ እንደ ተጠቀሰው። ንጉሥ ዳዊት ገና ልጅ ሳለ ነበር የተመረጠው (አንቀጽ 9) ላይ እንደ ተጠቀሰው በማለት እግዚኣብሔር ገና በወጣትነት እድሜ ደረጃ ላይ እያሉ ለልዩ ዓላማ የጠራቸውን ሰዎች እንደ ነበሩ ይገልጻል። ሰለሞን እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም” (1 ነገሥት 3፡7) በማለት ገና ወጣት መሆኑን በመግለጽ የእግዚአብሔርን ጥበብ ጠይቆ የእርሱን ተልዕኮ ለመፈጸም ግን ዝግጁ እንደ ሆነ መግለጹ ይታወቃል (አንቀጽ 10)። በተመሳሳይም የናማንን እና ወጣት የነበረችሁን የሩትን ታሪክ በመግለጽ በዚህ ዓይነት በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱትን ወጣቶች በማስታወስ ወደ አዲስ ኪዳን ያመራሉ።

በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ወጣቶችን በተመለከተ የተገለጹትን ዋና ዋና ነጥቦች ከአንቀጽ 12 ጀምሮ የዳሰሱ ሲሆን “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው” (ሉቃስ 15፡11-32) በመባል የሚታወቀውን ጠፍቶ የተገኘውን ልጅ ታሪክ ቅዱስነታቸው ማንሳታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ኢየሱስ ራሱ ወጣት ስለነበረ ወጣት የሆነ ልብ ለዘለአለም ሊሰጠን መፈለጉን ደግሞ በአንቀጽ 13 ውስጥ በስፋት ገልጸዋል። በተጨማሪም “ኢየሱስ ወጣቶችን የሚንቁ ወይም በወጣቶች ላይ የበላይነትን መጎናጸፍ የሚፈልጉትን አዋቂ የሆኑ ሰዎችን እንደ ሚቃወማቸው ማስታወስ ይገባል” በማለት የገልጹ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ “እናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን” (ሉቃስ 22፡26) በማለት ምክረ ሐሳብ ይሰጣል። ለኢየሱስ የእድሜ ባለጸጋ መሆን በራሱ ልዩ የሆነ ክብር የሚያስገኝ ነገር አልነበረውም፣ በተቃራኒው ደግሞ በወጣትነት እድሜ ላይ መገኘት በራሱ ደግሞ ክብር የሚነሳ እና ዝቅተኛ የሚያስብል ነገር እንዳልሆነ በግልጽ የሰፈረበት አንቀጽ ነው (17)።

05 April 2019, 13:48